ሰሞኑን በቡኖ በደሌ ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመለሱ...

ሰሞኑን በቡኖ በደሌ ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመለሱ ተባለ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ከበደሌ ወረዳ ተፈናቅለው በበደሌ ከተማ የተጠለሉ ሙሉ በሙሉ ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደተመለሱ የተገለጸ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎችም ያሉ ተፈናቃዮች በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት እንደሚመለሱ ተጠቆመ።

ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሀይማኖት አባቶች በውይይት ላይ ተገኝተዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች ፣አባ ገዳዎች እና የሀይማኖት አባቶች የተፈናቀሉ ወገኖቻቸውን ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም እንደሚሰሩ ቃል እንደገቡ ተገልጿል።

የአካባቢው ህዝብም የምግብና አልባሳት አቅርቦት በተጨማሪ “በእናንተ የመጣ በእኛ የመጣ ነው፤ የእናንተ ችግር የኛ ችግር ነው፤ አብረናችሁ የመጣውን እንመክታለን፤ የፈረሰውን እንጠግናለን፤ የተዘረፈውን እናስመልሳለንና አብረን እንዘልቃለን” በማለት እንዳበረቷቸው ተጠቅሷል።

የአማራ ተፈናቃዮችም ህዝቡ ህይወታቸውን እንዳተረፈላቸው በመግለጽ አመስግነዋል። የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ በበኩላቸው በጉዳዩ እጃቸው አለበት የተባሉ 43 ሰዎችን በቁጥጥር እንደዋሉ ገልጸዋል።

የአማራና ኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊዎች ሰሞኑን ግጭት ተፈጥሮበት በነበረው በቡኖ በደሌ ዞን ገቺ ወረዳ የተፈናቀሉ ወገኖችን መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት በበደኖ፣ አርሲ፣ጉራ ፋርዳ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝና ሌሎች ቦታዎች አማራ ሲፈናቀል “ከአማራ ክልል ውጭ ላለ አማራ አያገባንም” ከማለት አልፎ ሁኔታዎችን በዝምታ በማለፍ የሚታወቀው የአማራ ክልል መንግስት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁንን በግፍ የተሰደዱ አማሮች ወደአሉበት ስፍራ ቡኖ በደሌ ዞን አቅንተው መመልከታቸው ትኩረትን የሳበ ሲሆን በአሁኑ ሰአት በኦሮምያ አንዳንድ አካባቢዎች መጤዎች ባሏቸው ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን ያመላክታል ተብሏል፡፡

LEAVE A REPLY