በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ /በጌታቸው ሺፈራው/

በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ /በጌታቸው ሺፈራው/

የፌደራል አቃቤ ህግ በኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ዛሬ ጥቅምት 24/2010 ዓም ሁለት ምስክሮች አሰምቷል። ሁለቱም ምስክሮች ታህሳስ 14/2009 ዶር መረራ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከኮምፒውተር የወጣን ፅሁፍ የእራሴ ነው ብለው ሲፈርሙ ተገኝተን ታዝበናል ያሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። ስማቸው ደራራ እና ጌታቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ያስመዘገቡት ምስክሮች በአንድ ቀን የታዘቡ እና የሚተዋወቁ ጓደኛሞች እንደሆኑ ገልፀዋል።

ደራራ (አንደኛ ምስክር) ወደ ማዕከላዊ የሄደበትን ምክንያት ሲጠየቅ ቶሎሳ የሚባል ዘመዱን ሊጠይቅ መሄዱን፣ ብቻዬን ከምሄድ በሚል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አብሮት እንዲሄድ ጠይቆት ከሚሰሩበት መስርያቤት አስፈቅደው አብረው እንደሄዱ እና ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ጠይቋቸው እንደተስማሙ ገልፆአል።

በሌላ በኩል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አንደኛ ምስክር (ደራራ) ጋር አንድ ክፍለ ከተማ እንጅ አንድ መስርያ ቤት እንደማይሰሩ፣ ብቻውን በመስርያ ቤት ትዕዛዝ ለመርማሪዎች ሰነድ ለመስጠት እንደሄደ፣ ስራውን ጨርሶ ከመርማሪው ቢሮ ሲወጣ ኮማንደር አሰፋ በተባለ የምርመራ ክፍል ሀላፊ እማኝ እንዲሆን መጠየቁን፣ እሱ ስራዉን ጨርሶ ከወጣ እና እማኝ ለመሆን ፈቃደኛ ከሆነ በኋላ ደራራን እንዳገኘው እንዲሁም አንደኛ ምስክር (ደራራ) ወደ ማዕከላዊ የመጣበትን ጉዳይ የነገረው እማኝ ከሆነ በኋላ እንደሆነ አንደኛ ምስክር ከመሰከረው የተለየ ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።

በተጨማሪም አንደኛ ምስክር በወቅቱ ዶ/ር መረራ ሹራብ ለብሰው ነበር ሲል ሁለተኛ ምስክር ጅንስ ሱሪና ጅንስ ሸሚዝ ለብሰው ነበር ብሏል። አንደኛ ምስክር (ደራራ) ዶ/ር መረራ በኮማንደር አሰፋ ብቻ ታጅበው ምስክሮቹ ወደነበሩበት ምርመራ ቢሮ እንደገቡ ሲመሰክር፣ ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) ከኮማንደር አሰፋ በተጨማሪ ሁለት ፖሊሶች ነበሩ ብሏል።

አንደኛ ምስክር ዶ/ር መረራ ወደ ምርመራ ቢሮ እስኪመጡ በግምት ለአንድ ሰዓት ያህል መጠበቃቸውን ሲገልፅ፣ ሁለተኛ ምስክር ( ጌታቸው) በግምት ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ያህል ብቻ እንደጠበቁ ገልፆአል። አንደኛ ምስክር የዶ/ር መረራ ነው ከተባለ ኮምፒውተር ፕሪንት ተደርገው የወጡ ፅሁፎችን በከፊል እንዳነበበ ሲመሰክር ሁለተኛ ምስክር የፅሁፎችን ይዘት ብቻ ሳይሆን ርዕሶችንም አለማንበባቸውን፣ ዶ/ር መረራ አንብበው ሲፈርሙ ታዝበው መፈረማቸውን ገልፀዋል።

በዶ/ር መረራ ላይ ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ሌሎች ሁለት ምስክሮችን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳላገኛቸው የገለፀ ሲሆን ሁለቱን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 21/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

LEAVE A REPLY