የኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ባህር ዳር ተገኝተው ከተናገሩት መካከል ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው የሚለው አስደማሚ ቃል የሚገኝበትን ክፍል በጨረፍታ የሰማሁት ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛው ክፍል ነው፡፡ ሰምቼ ሳላጨርስ ስሜቴ ተለዋወጠ፣ለራሴም ልረዳው ባልቻልኩ ሁኔታ የለቅሶ ስሜትም ተሰማኝ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ፈጥነው ወደ አእምሮየ የመጡት አይታክቴው አባት ምሁር ፕ/ር መስፍን ናቸው
ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በጀነራል ጃገማ ኬሎ ይመራ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ይባል የነበረ ድርጅት በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት አዳራሽ በጠራው ህዘባዊ ሰብሰባ ላይ በተናጋሪነት ከተገኙት ሶስት ሰዎች አንዱ የነበሩት ፕ/ር መስፍን አይዞአችሁ ስጋት አይግባችሁ ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት አይደለም ማንም ታግሎ ሊያሸንፈው አይችልም እያሉ በልበ ሙሉነት ሲናገሩ አሁን የሆነ ያህል ታየኝ፡፡
አዎ፣ ራሱን ከአደጋ የመከላከል ትልቅ አቅም ያለው ኢትዮጵያዊነት ብዙ አሳይቶናል፣ የማንማር ሆነን እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ብሎ መጥራት ሀፍረት ይሁን ውርደት ሆኖበት ሀገራችን፣ ሀገሪቱ እንዳለ፤ የኢትጵያ ህዝብ ለማለት ህሊናው አልፈቅድ አንደበቱምም ቃል አላወጣ ብሎት የሀገራችን ህዝቦች እንዳለ ለማይቀረው ሞት የተዳረገው ሰው ይመራው በነበረና ከርሱው ሞት በኋላም የእኛ የሆነ ምንም ነገር የለንም በማለት ሌጋሲውን እናስቀጥላል ብለው ምለው ተማምለው በሙት መንፈስ ህዝብ የሚያምሱ ከሞሉበት ደርጅት ሰፈር ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው የሚል ቃል መስማት የፈጣሪ ተአምር የኢትጵያዊነትም ሀያልነት እንጂ ምን ሊባል ይችላል፤
ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ያሉት አቶ ለማ ርቀው ተጉዘው አድዋ ላይ ተነባብርን የሞትነው፣ በሶማሌ ጦርነት ተደጋግፈን የወደቅነው ባድመ ላይ ደማችን ተቀላቅሎ የፈሰሰው ለአንዲት ኢትዮጰያ ተብሎ አንጂ በቅጥረኝነት አልነበረም እያሉ ሲናገሩ ከቃላቶቹ ጋር የሚወጣው ድምጸታቸው በእምነት እንጂ በስሜት፣ በእውነት እንጂ ከአጣብቂኝ ለመውጣት ለብልሀት፣ ያደረጉት ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አልነበረም፡፡ በዛውም መጠን የሚያምኑትን፣ ተግባራዊ ሊያደርጉትም የተዘጋጁበትን ነው የተናገሩት ብሎ ሙሉ ለሙሉ አምኖ መነጋር አያስደፍርም፡፡ምነው ቢባል ብዙ ሰምተን ቃል የእምነት ዕዳ ሳይሆን ቀርቶ አይተን ታዝበናልና ነው፡፡ ለመወቃቀሻነት ሳይሆን ለመማማሪያነት ሂሳብ ለማወራረድ ሳይሆን ስህተቱን አስወግዶ ጠንካራውን ለማስቀጠል ትናንትን መለስ ብሎ መቃኘት ጠቃሚ ነው፡፡ የኋላው ከሌላ የለም የፊቱ አይደልስ ነገሩ፡፡
አባ ዱላ እንደ ለማ፡፡ በ2006 ዓም የመጀሪያው ወር ላይ ነው፡ የኢትዮጵያ ሀይማኖቶች ህብረት ጉባኤ ላይ በአፈ ጉባኤ ሥልጣናቸው የተገኙት አባ ዱላ ያለችን አንድ ሀገር ነች እሷም ኢትዮጵያ ናት እያሉ ሲናገሩ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሰማሁና ጆሮዬን ተጠራጥሬ ሰዎች ጠየቅሁ፡፡ እነርሱም በሰሙት ነገር መገረማቸውን እየገለጹ አረጋገጡልኝ፡፡ልክ እንዳሁኑ ያኔም የተሰማኝን ወዲያውኑ በአንዱ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ አሰፈርኩ፡፡ እንዲህ የሚል ይገኝበት ነበር፡፡
አንዲህ ለመናገር ያበቃቸው ምንድን ነው በርግጥስ አምነውበት ወይንስ ለመድረክ ጠቀሜታ፣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ወዘተ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ምንም ይባል ምን ከአፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ አንደበት የወጣው ቃል በእጅጉ የሚያስደስትና ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው፡፡ በአንጻሩም ኢትዮጵያዊነት ራሱን የማስከበር ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ በማለት በዚህ ጽሁፍ የጠቀስኳቸውን ፕ/ር መስፍን ወልደማረያምን በአብነት ጠቅሼ የኢትዮጵያዊነትን ኃያልነት በማሳየት ኢትዮጵያዊነትን የተፈታተኑ የደረሳባቸውን ክስረት የገጠማቸውን ውርደት በማውቀው መጠን በማስረጃ ለማሳየት ሞከርኩ፡፡ አከልኩና፣
በተከበሩ አቶ አባ ዱላ አንደበት የተነገረው ቃል በተግባር ይገለጥ፣ እምነቱ ከግለሰብ ወደ ተቋም ይሸጋገር፣ እናም አንድነታችን ይጠንክር ኢትዮጰያዊነታችን ያብብ ያፍራ፡፡
ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በላይ ከፍ ሲል ሰው መሆናችን ዝቅ ሲል ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችን በብዙ መጠን ሚዛን ይደፋልና፡፡ (ይህ ዛሬም የአቶ ለማን ንግግር ተከትሎ ቢጠቀስ የሚሆን ይመስለኛል) ወደ ማጠቃለያው ደግሞ
እንደ አለመታደል ሆኖ ገዢው ከተፎካካሪ፣ ተፎካካሪዎቹም ርስ በርስ ቃላት እየሰነጠቁ ህጸጹን ብቻ እየፈለጉ ቸግር ስህተቶችን እያበዙና እያባዙ መወጋገዝ እንጂ በጎ ተግባራትን እያወጡ ማድነቅ መልካም ጅምሮችን ማበረታት አይታይባቸውም፡፡ይህም የአንድነታችንን መሰረት ከሚያናጉትና የኢትዮጵያዊነታችንን ማተብ ከሚያላሉት ምክንያቶች አንዱ ነውና ልናርመው ልናስወግደው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ትግላችን ለሀገራዊ ለውጥ ነው እንላለንና፣ ሀገራችን ደግሞ አንድ እሷም ኢትዮጵያ ናትና፡፡ ይህን በአቶ ለማ አነጋገር ተሀድሶ ብንሰጠው ኢትዮጵያዊንት ሱስ ነውና አድዋ ኦጋዴን ባድመ ተቃቅፎ የወደቀ አጽም፣ ተቀላቅሎ የፈሰሰ ደም ነውና ደበረኛ ወይም ከበደኝ ብለው አውልቀው የሚጥሉት የተሸለ አገኘሁ ብለው የሚቀይሩት አይደለምና፡፡ ( በርግጥ ሌላ ዜጋ መሆን መቻሉ ሳይዘነጋ ነው)
አቶ ለማ አንደ አባ ዱላ ወይንስ..? ትውስታ ማንሳቴ እንዲህ ብዬ ነበር ለማለት ወይንም አቶ አባ ዱላን ለማሳጣት አይደለም፡፡በነገራችን ላይ የተናገሩትን መተግበር ያልቻሉት አባ ዱላ አሁንም መልቀቂያቸውን ማስከበር የቻሉ አይመስሉም፡፡የንጽጽሩ ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ አባ ዱላ ያለችን አንድ ሀገር እሷም ኢትዮጵያ ነች ሲሉ ባለሥልጣን ነበሩ፣ከዛ በኋላ ግን ይህ ቃላቸው እምነታቸው መሆኑን የሚያሳይ ተግባር ቢያንስ እኔ አላየሁባቸውም፡፡ እናም ለዚህ ነው አንድም በርእሴ አቶ ለማን ያናገራቸው እምነት ወይንስ ስሜት በሚል መጠይቅ የጀመርኩትና እዚህ ላይ ደግሞ ለማ አንደ አባ ዱላ ወይንስ ለማለት የበቃሁት፡፡
ሁለቱም ለለማ ፈተና ያለበት ይመስለኛል፡፡በአንዳንድ ወገኖች እንደሚነገረው በወያኔ የተጻፈ ትያትር መሪ ተዋናይ ሆነው በእውነት ሳይሆን ከአጣብቂኝ ለመውጣት ሲሉ እየተወኑ ከሆነ ትልቁን ነገር ህዝቡን ያጡታል፡፡ህዝብ ደግሞ በቁም አክብሮ የሚያኖር፣ ሲሞቱ አልቅሶ ቀብሮ ወግ ማዕረግ የሚያሳይ ነው፡፡ ከህዝብ ፍላጎት የተቃረነ ተግባር መፈጸም ዳፋው ለራስ ብቻ አይደለም፣ለልጅ ይተርፋል ሲከፋም ወደ የልጅ ልጅ ይሸጋገራል፡፡ አቶ ለማ የባህር ዳሩ መድረክ ላይ የተናገሩት እምነታቸውን ከሆነና ለዚህ ተግባራዊነትም ራሳቸውን አዘጋጅተው ከሆነ የዝግጅታቸው እንዴትነትና የተከታዮቻቸው ማንነት ውጤቱን በእጅጉ ይወስነዋል፡፡ምክንያት ከወያኔ ጋር ፍልሚያ ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ በመሆኑ፡፡
በተግባር እንደምናውቀው በእንዲህ አይነት ወቅት ከዋናው ተፋላሚ በላይ አስቸጋሪውና ለሽንፈት የሚያበቃው በሥልጣን የሚደለለው በፍርፋሪ የሚገዛው፣ ህሊናውን ለሆዱ ለማስገዛት ቅንጣትም የማይቸገረው ነውና ውስጥን ማጥራት የግድ ይላል፡፡ ሌላው ቢቀር በ1992 የወያኔ መከፋፈል ወቅት ብቻውን ቀርቶ የነበረው መለስ እንዴት በአሸናፊነት እንደወጣ መርሳት ራስን ለችግር አሳልፎ በፈቃድ መስጠት ይሆናል፡፡ ዛሬም ብዙ አባይ ጸሀዬዎች፣ ኩማ ደመቅሳዎች ካሱ ኢላላዎች ወዘተ ራሱ ኦህዴድ ውስጥ እንደሚኖሩ ለመጠርጠር የተለየ ጥናት አይጠይቅም፡፡
አምቦ ላይ የህገ ወጥ ነጋዴዎችን መኪናዎች አናሳልፍም ባሉ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ግድያ ያንገሸገሻቸው የአካባቢው አስተዳደር ቃል አቀባይ ለአሜሪካ ድመጽ ራዲዮ የገዳዮቹን ማንነት ከገለጹ በኋላ ከእንግዲህ የምንደብቀው ነገር የለም እውነቱን ለሚመለከተው እናገልጻለን በአሉ ማግስት ከጎናቸው ያሉ ሌላ ባለሥልጣን በመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩትን የሰማ ሰው የወያኔ ጀንበር መቸም አትጠልቅ ብሎ ያመነና በዚህ ግርግር የሥልጣን ጥማቱንም ሆነ የንዋይ ፍላጎቱን ለማርካት በወያኔ ሰፈር ጅራቱን ሚቆላ ከኦህዴድም ከብአዴንም ከሌላ ሌላውም ለመኖሩ በቂ መሳያ ነው፡፡
ስለሆነም ለአቶ ለማ ሁለቱም በአበባ ምንጣፍ ላይ መረማመድ አይደለም እንደውም በሊማሊሞ የማቋረጠ ያህል ነው፡፡ግና አንደኛው ያስከብራል ሌላኛው ለውርደት ያበቃል፡፡ ደሞ እኮ ቃል የእምነት እዳ እንጂ የእናተ አባት አይደለም ይባላል፡፡ እናም አቶ ለማ ኢትዮጵያዊነትን በተለየ በሚያስደምም ኃይለ ቃል ለመግለጽ የበቁት ሌላ የጀርባ ምክንያት ሳይኖር ከውስጥ ፈንቅሎ በወጣ ስሜት ከሆነ በወያኔ እንዳይበለጡ መሰረትዎን በማጥበቅ ቃልዎን በተግባር ለማሳየት የጣጣሩ፣ ያኔ ፈጣሪም ይረዳዎታል ህዝቡም ይተባበረዎታል፡፡ ጉዳዩን የለማ የግል ከመሰለበት ሁኔታም ወደ ኦህዴድነት መቀየር ነው፡፡ ለኦህዴዶችም ሀያ ስድስት አመት አሽከርነነት በጣም በዛ፤ ያውም በራስ ቀለብ በራስ ልብስ አረ አንደውም ከራስ አልፎ ጌታውን እያበሉና እያለበሱ አሽከርነት መግባት ከሰውነትም መውረድ ነው፡፡
የኦህዴድ አመራርም ሆነ አባልና ደጋፊ በየመገናኛ ብዙኃኑ ማድነቅ ብቻውን ፋይዳ የለውም፣ በአዳራሽ ተገኝቶ ማጨብጨቡም እንዲሁ፣ ማገዝ ነው፣ መደገፍ መደጋገፍ ነው ለውጤት የሚያበቃው፤ ወያኔዎቹ እንደሆነ ውስጡ ውስጡን መሸርሸሩን ማከዳዳቱን ማባላቱን ያውቁበታል፡፡ ታምራት ላይኔ በመለስ ሴራ ራሱን ኣውርዶና አዋርዶ ወደ ወህኒ ሲሸኝ ብአዴኖች በጭብጨባ መሸኘታቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡ በልጦ መገኘት ይጠይቃል፡፡ የሰማነውን በተግባር ለማየት ያብቃን።
የወያኔ ደቀ መዝሙሮች፣፣በስም ተቀዋሚ በተግባር ግን የወያኔን ዘረኝነት የሚያራምዱ ብዙዎቸ እናውቃለን፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ወያኔ ለመተውም ለመቀጠልም ተቸግሮ በሚያንገራግርበት ወቅት በቅርቡ ነው ይህን ጎራ የተቀላቀሉትና በአጭር ግዜ ከጳጳሱ ቁሱ ሊባል የሚበቃ ሁኔታ ውስጥ የገቡት፡፡ አንዳንዶቹ በአደባባይ ባይናገሩቱም ምክንያታቸው ወያኔ ለምንይልክ ቤተ መንግስት የበቃው በዘር በመደራጀቱ ነው የሚሉ ይመስላሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በጎሳ መደራጀት የጎሳውን አባላት ገንዘብ ለማግኘት ቀላሉና አቋራጩ መንገድ መስሎ ታይቷቸው የገቡበት ይመስላሉ፡፤ በርግጥ አንዳንዶቹ የሰመረላቸው ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ ነብሳቸውን ይማረውና አቶ አሰፋ ጫቦን ላስገባቸው፡፡ “ያጋራ ቤታችንን” ጨርሼ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አዋጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል Facebook ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ባልተነበበ ጹሁፍና አስተያየት ላይ ነበር።ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማንውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን ? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ሰውረን ነው? አውቀን የካንደነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን? ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ በተለየ አንዳንድ ዲያስፖራው ኗዋሪዎች መተደዳደሪያም ወደ መሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ ሆነን፤አገር አውቆን ፣ፀሐይ ሞቆን፤ አንቱ የተባልንበትን ልታፈርስብን ነው የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል። ” (ይህን ደጋግሜ ያነሳሁት ይመስለኛል፡፡ በተለይ የተባለው ጽሁፍ ለንባብ ሳይበቃ ቅጽበታዊና ምስጢራዊ የሆነው ሞታችን ሁሌ ይከነክነኛል፡፡)
የቀደሙት ገና በሽግግሩ ዘመን ጀምረው እስካሁን ሳይፋቱ እየተቀደሙ ያሉት ደግሞ ወያኔ በቀደደላቸው ቦይ ፈሳሽ ሆነው ነው ፡፡ ምን አልባት አሁንም ተገልብጠው በተቀደዳለቸው ቦይ ይፈሱ ይሆናል፡፡ አለያም የጎሳ ጥብቋቸውን እንደለበሱ ባሉበት ይረሳሉ፡፡ ሁሉም ግን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ ፡፡ደረጃው፣ ይዘቱና አተገባበሩ ይለያይ እንጂ ለኢትጵያዊነት ሲበዛ ጥፋት ሲያንስ እንቅፋት ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ሊሉ ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ለማትየና ለመስማት ያጓጓል፡፡ ይሄ በእነ ኦቦ ለማ ሰፈር የምንሰማው ኢትዮጵያዊነት የእምነት ሆኖ ወደ ተግባር ከተሸጋገር የትኛውም በጎሳ የተደራጀ መጫወቻ ካርድ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ መቼም የእኛ ነገር ሁሉ እንቆቅልሽ ነውና በተቃራኒው በዛኛው ጎራ ኢትዮጵያዊነት በዚህ በእኛ ሰፈር ደግሞ ጎሰኝነት ሲቀነቀን እንሰማ ይሆናል፡፡ እድሜ መለመን ነው፡፡