ልደቱና ጆሲ በJTV – ቅንጅትን ማን አፈረሰው? /መሐመድ አሊ መሐመድ – የቀድሞው...

ልደቱና ጆሲ በJTV – ቅንጅትን ማን አፈረሰው? /መሐመድ አሊ መሐመድ – የቀድሞው ቅንጅት ላዕላይ ም/ቤት አባል/

ይህ ጽሁፍ የንባብ ልምድ ላላቸውና ስለቀድሞው “ቅንጅት” መረጃ የማግኘት ፍላጎት ላላቸው ብቻ የቀረበ ነው፡፡ በርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ የግል አስተያየቴን ማቅረብ አለብኝ/የለብኝም በሚል ከራሴ ጋር ስሟገት ትንሽ ዘግይቻለሁ
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፤፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፤፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
አንድ የፌስቡክ ወዳጄ በውስጥ መስመር ልደቱና ጆሲ በJTV ቃለ ምልልስ እንደሚያደርጉ በመጠቆም እንድከታተለው ጋብዞኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ቃለ-ምልልሱ በተላለፈበት ምሽት በግል ምክንያት ሳልከታተለው ቀረሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ግን YouTube ውስጥ ስገባ ቃለ-ምልልሱን አገኘሁትና በጥሞና ተከታተልኩት፡፡ እውነት ለመናገር የጆሲን ፈታ ያለ የጥያቄ አቀራረብም ሆነ የልደቱን ከወትሮው የተለዬ መረጋጋት ወድጄው ነበር፡፡ ልደቱ በአስተዳደጉ፣ በትምህርቱ፣ ወደ ሥራና ኋላም ወደ ፖለቲካ ስለገባበት መንገድና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጣቸው መረጃዎች “ሰውኛ” ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡

ከዚህም በመነሳት የቃለ-ምልልሱን ቀጣይ ክፍል በጉጉት ጠብቄው ነበር፡፡ በዚህኛው ክፍል በተለይ በአቶ ልደቱ የፖለቲካ ተሳትፎና ሰብዕና ዙሪያ በሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ አቶ ልደቱ በግልፅነትና በሐቅን ላይ የተመሠረተ መረጃ ይሰጣል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ይሁንና እኔ እንደጠበቅሁት ሊሆን አልቻለም፡፡ በቃለ-ምልልሱ ላይ ተመስርቼ ትዝብቴን እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡፡

፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፤፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፤፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
1. ቅንጅትን ማን አፈረሰው? በሚለው ዙሪያ፣

አቶ ልደቱ ለቅንጅት መፍረስ የነበረውን ድርሻ ከማመልከት ይልቅ ከነጭራሹ “ቅንጅት አልተፈጠረም” በሚል ከኃላፊነት ለመሸሽ ሞከረ፡፡ አቶ ልደቱ “በውህደት ሰነዱ” ላይ የኢዴፓ-መዲኅንን ማህተም ለማድረግ “አሻፈረኝ” በማለቱ ቅንጅቱ ህጋዊ ዕውቅና ለማግኘት ላለመቻሉና በዚህም ሳቢያ ለመፍረሱ ተጠያቂ ነው መባሉን ለመከላከል ይመስላል – የቅንጅትን ህልውና መካዱ፡፡ የአቶ ልደቱ አቀራረብ “የቅንጅቱ ውህደት ሊጠናቀቅ የሚችለው ከላይ እስከታች በየደረጃው ያሉ አባሎቻችንና መዋቅሮቻችን ተዋህደው ሲያበቁ ነው” የሚል ሙግትን የተመረኮዘ ነው፡፡

ይህ ሙግት ከውጭ ሲያዩት ትክክለኛና አመንክኗዊ ይመስላል፡፡ አቶ ልደቱም በውህደት ሰነዱ ላይ የኢዴፓ-መዲኅንን ማህተም ለማድረግ “አሻፈረኝ” ካለ በኋላ ከቅንጅቱ ላዕላይ ም/ቤት ተመርጠው በተላኩ ሽማግሌዎች አማካኝነት በም/ቤቱ ስብሰባ ላይ ይህንኑ ሙግት አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከኢዴፓ-መዲህን ተወክለው የቅንጅቱ ላዕላይ ም/ቤት አባላት ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ (ከ2/3ኛ በላይ የሚሆኑት) ከእሱ በተቃራኒ በመቆም ተሟግተዋል፡፡

ይህ ስብስብ ዶ/ር አድማሱ ገበየሁን፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያን፣ ዶ/ር ሚኪያስን፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህን፣ አቶ አንዷለም አራጌን፣ አቶ ታምራት ታረቀኝን … ጨምሮ ብዙሃኑን ያቀፈ ነው፡፡ ስብስቡ እንዳስረዳው መስከረም 11 ቀን 1998 ዓ.ም የተካሄደው የኢዴፓ-መዲኅን ጉባኤ የፓርቲውን ህልውና ለማክሰም የተጠራና ውህደቱን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የተቀበለ ነው፡፡ ሆኖም ግን አቶ ልደቱ የራሱን አቋም ከገለፀና ከእሱ በተቃራኒ የቀረበውን ክርክር ከሰማ በኋላ የም/ቤቱን ስብሰባና የነወ/ሮ ላቀች ደገፉን (ከኢዴፓ-መዲህን የተወከሉና አሁን በህይወት የሌሉ) ተማፅኖ ረግጦ በመውጣት የቅንጅቱን ህልውና ጥያቄ ላይ ጥሎታል፡፡

በላዕላይ ም/ቤቱ ከግራ ቀኙ የቀረቡትን ክርክሮች ወደጎን ብንተዋቸው እንኳ ከአጠቃላይ ሂደቱና ከነበሩት ተጨባጭ ክንውኖች አንፃር ሲታይ የአቶ ልደቱ ሙግት ውሀ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ከአራቱ ፓርቲዎች በተወከሉ አባላት የተዋቀረውና መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም የተካሄደው የቅንጅት መሥራች ጉባኤ፣

1.1. የአራቱን ፓርቲዎች ውህደት ተቀብሎ አፅድቋል፡፡
1.2. የውህዱን ፓርቲ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ረቂቆች ተቀብሎ አፅድቋል፡፡ በጉባኤው አባላት የቀረቡ አንዳንድ የማሻሻያ ሀሳቦችን/አስተያየቶችን መርምሮ እንዲያካትት ለላዕላይ ም/ቤቱ የውክልና ሥልጣን ሰጥቷል፡፡
1.3. በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት 60 አባላት ያሉትን የቅንጅቱን ላዕላይ ም/ቤት አቋቁሟል፡፡
1.4. በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በላዕላይ ም/ቤቱ የተከናወነውን የቅንጅቱን ፕሬዝዴንት፣ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝዴንት፣ ም/ፕሬዝዴንትና ዋና ፀሐፊ ምርጫን ተቀብሎ አፅድቋል፡፡

ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ሲጠናቀቅ በርካታ ታዋቂና የተከበሩ ዜጎች፣ የሌሎች ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞችም ተገኝተው ነበር፡፡ አራቱ ፓርቲዎች “ቅንጅት” የተሰኘ ውህድ ፓርቲ መፍጠራቸውን መሪዎቹ (የኢዴፓ-መዲህን ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አዲማሱ ገበየሁን ጨምሮ) በጉባኤተኛውና በተጋባዥ እንግዶች ፊት በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡ ይሁን እንጅ የውህደት ስምምነቱ በወቅቱ የፓርቲዎቹ ማህተሞች ስላላረፉበት ከጉባኤው በኋላ ትንሽ ዘግይቶ ሌሎች ፓርቲዎች በስምምነቱ ፊርማ ላይ ማህተማቸውን ሲያሣርፉ የኢዴፓ-መዲህን ማህተም በእጁ/በቁጥጥሩ ሥር የነበረው አቶ ልደቱ ማህተም ለማድረግ “አሻፈረኝ” ብሏል፡፡

አቶ ልደቱ በውህደት ስምምነቱ ላይ ማህተም ለማሳረፍ አሻፈረኝ በማለቱ በገዥው ፓርቲ የተቋቋመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅንጅትን የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ለመከልከል ምክንያት አግኝቷል፡፡ አቶ ልደቱና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወሰዱት እርምጃ ቀደም ብሎ የተቀነባበረ ይሁን ወይም በድንገት የተፈጠረ ግጥምጥሞሽ ለመናገር የሚያስችል ማስረጃ የለኝም፡፡

የሆነ ሆኖ አቶ ልደቱ ከመጀመሪያውም “ቅንጅት” አልተፈጠረም በሚል “ቅንጅትን ማን አፈረሰው?” የሚለውን አንገብጋቢ (crucial) ጥያቄ አዳፍኖ ለማለፍ መሞከሩ ይበልጥ አነጋጋሪና አስተዛዛቢ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ሐቁን እንደወረደ አስቀምጦ ለቅንጅት መፍረስ የተለያዩ ወገኖች የነበራቸውን ድርሻ በማመልከት ረገድ የተሻለ ሙግት ማቅረብ ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ግን አቶ ልደቱ ከእሱ በተቃራኒው የቆሙ ወገኖች ክርክራቸውን ሊያቀርቡ የሚችሉበት ተመሳሳይ መድረክ/ዕድል አያገኙም በሚል ስሌት ሐቁን ሸፋፍኖና ረግጦ ማለፍን መርጧል፡፡ ሐቅን ረግጠኸው ስታልፍ ደግሞ ጩኸቱ አንተን ራስህን ጭምር መረበሹ አይቀርም፡፡ እነሆ ሐቁ ተሸፋፍኖ ሲረገጥ በጩኸቱ ከተረበሹት አንዱ እኔ ሆኛለሁ፡፡

2. የሥልጣን ፍላጎትን በተመለከተ፣

የፖለቲካ ተሳትፎ ዓላማና ግቡ የፖለቲካ ሥልጣንን መያዝ/መቆጣጠር ነው፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጅ በሁሉም ፖለቲከኞች ውስጥ የሥልጣን ፍላጎት መኖሩ የማይካሄድ ሐቅ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝን/መቆጣጠርን እንደግብ አስቀምጦ መንቀሳቀስ ስህተት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ግቡ ሥልጣን ይዞ ዓላማን ማስፈፀም በመሆኑ የሥልጣን ፍላጎት እንደነውር ሊታይ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ ነውር የሚሆነው ሌሎችን በአሉባልታ ጥላሸት በመቀባት፣ በሀሰት በመወንጀልና ጠልፎ በመጣል ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ መሞከርና የቆሙለትን ዓላማ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተለዬ ለጽድቅ የሚሠራና ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የሚከፍል ፖለቲከኛ ሊኖር አይችልም፡፡ አለሁ ቢልም እንኳ ሊታመን አይችልም፡፡

ወደ አቶ ልደቱ ስንመጣ በአንድ በኩል ከፖለቲካ ውጭ ህይወት የለኝም እያለ በሌላ በኩል “የሥልጣን ፍላጎት አልነበረኝም/የለኝም” የሚለው “አጉል ጨዋታ” ለአደባባይ የሚመጥን አይደለም፡፡ ይልቁንስ ይህን ለጆሲ ብቻ በግሉ (of the record) ቢያጫውተው ኖሮ የትዝብቱን አድማስ ማጥበብ በቻለ ነበር፡፡

እርግጥ ነው የኢዴፓ መሥራቾች በወቅቱ (1992 ዓ.ም) በዕድሜና በትምህርት ያልገፉና ብዙም የማይታወቁ ስለነበሩ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ላናገኝ እንችላለን ከሚል ሥጋት በመነጨ የተማሩና ታዋቂ ሰዎችን ለማሰባሰብና ኃላፊነት ላይ ለማስቀመጥ የነበራቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው፡፡ ይሁንና ይህ እውነታ የአቶ ልደቱን “የሥልጣን ፍላጎት አለመኖር” ማረጋገጫ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ አቶ ልደቱን ከፍተኛ የሥልጣን ፍላጎት እንደነበራቸው/እንዳላቸው ለማረጋገጥ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

2.1. ኢዴፓ ውስጥ ዶ/ር አድማሱና ዶ/ር ኃይሉ በቅደም ተከተል ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር ተብለው ለይስሙላ ቢቀመጡም የሁሉ ነገር አድራጊና ፈጣሪ ልደቱ ነበር፡፡ በፓርቲው ውስጥ የእሱ ተቀናቃኝ የሆኑ/ለሥልጣኑ የሚያሰጉ ሰዎችን ሥም ጥላሸት ለመቀባትና ለማባረር ወደኋላ አይልም ነበር፡፡ አሁን በወያኔ እሥር ቤት የሚማቅቀው አበበ ቀስቶ (ክንፈ ሚካኤል አበበ፣ የግንቦት 7 አባል የሆነው ዘለሌ ፀጋስላሴ፣ ካሳዊ አዲሱና ሌሎችም በነአቶ ልደቱ “በሰርጎ ገብነት” ተፈርጀው ከአባልነት እስከመሰረዝ መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡ የዛሬን አያድርገውና በወቅቱ እነአንዷለም አራጌና ታምራት ታረቀኝም የልደቱ ቀኝ እጆች ነበሩ፡፡ እንዳውም “በልደቱ ሳንባ የሚተነፍሱ” እየተባሉም ይታሙ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ልደቱ ዶክተሮቹና ሌሎች አንጋፋ ሰዎች በነበሩበት ፓርቲ ውስጥ ያን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን መቻሉ በራሱ አስደናቂ ነው፡፡

2.2. በመኢአድና ኢዴፓ-መዲህን መካከል ተጀምሮ የነበረው የውህደት ድርድር የከሸፈው በሥልጣን ክፍፍል ላይ መግባባት ባለመቻሉ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥም የአቶ ልደቱ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ውህደቱን የሚፈልጉ የኢዴፓ-መዲህን አባላት ይናገሩ ነበር፡፡ እንዳውም ውህደቱ ሲከሽፍ እንደ ታዲወስ ታንቱን የመሳሰሉ ሰዎች ኢዴፓ-መዲህንን ለቅቀው የመኢአድ አባል ሆነው ነበር፡፡ እኔ በወቅቱ የመኢአድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነበርኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የመኢአድ ሰዎችም በፊናችን የነበረንን አጉል የጠቅላይነት ዝንባሌ መግለፅ ይኖርብኛል፡፡
2.3. በምርጫ 97 ምርጫ ዋዜማ የተፈጠረው የአራት ፓርቲዎች ቅንጅት ገና በለጋ ዕድሜው ህልውናውን የተፈታተነው በልደቱና በኢ/ር ኃይሉ ሻውል (አፈር ይቅለላቸውና) መካከል የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑን ልደቱ በእማኝነት የሚጠራቸው ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ደጋግመው ገልፀውታል፡፡ በተለይ በሁለቱ ሰዎች መካከል የነበረው የሥልጣን ሽኩቻና ውጥረት ለጊዜውም ቢሆን ሊረግብ የቻለው እነፕ/ር መስፍን ከምርጫው በኋላ ሥልጣኑ ለልደቱ እንደሚሰጠው ቃል ከገቡለት በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ አንፃራዊ የሞራል የበላይነት የነበራቸው የቀስተ-ደመና ሰዎች (በተለይ ፕ/ር መስፍንና ዶ/ር ብርሃኑ) በቅንጅቱ ውስጥ አንተም ተው፣ አንተም ብለው ከመኮርኮም ባለፈ ኮስተር ብለው የሚያስፈራሩና፣ እንደሁኔታው ተስፋን የሚሰጡ ነበሩ፡፡

2.4. ከ97 ምርጫ ማግሥት ውህዱ ፓርቲ ቅንጅት ከተፈጠረ በኋላም የልደቱ ከሥልጣን ማዕከሉ ትንሽ መገፋት ትልቅ ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም፡፡ ለዚህ መነሻ ምክንያቶች ቢኖሩም ልደቱ ተፅኖ ፈጣሪ መሆን ከሚችልበት የሥልጣን ክልል መገፋቱ አይካድም፡፡ በእኔ እይታ/እምነት የተገፋበት መንገድም ፍትሃዊ አልነበረም፡፡ ይህን ተከትሎ ቂም ቢቋጥር አይፈረድበትም፡፡ ልደቱ ቅንጅቱ ሲዋሃድ ለፕሬዝዴንትነት፣ ቀጥሎም ለተቀዳሚ ም/ፕሬዝዴንትነት ለመመረጥ ተወዳድሮ ሳይመረጥ ቀረ፡፡

ትርጉም ያለው የሥራ ድርሻ/ሥልጣን በሌለው የም/ፕሬዝዴንት ቦታ ኢዴፓ-መዲህንን ወክለህ መወዳደር አለብህ ሲባል እሱ የሚፈልገው በፀሐፊነት መመረጥ መሆኑን ገለፀ፡፡ ሆኖም ግን ባትፈልገውም ለቦታው መወዳደር አለብህ ተብሎ ያለፍላጎቱ በከፍተኛ ድምፅ ተመረጠ፡፡ የቀረው የዋና ፀሐፊነት ቦታ ያለተወዳዳሪ ለሙሉነህ እዩኤል ተሰጠ፡፡ ልደቱ ቀደም ብሎ በመኢአድና ቀስተ-ደመና ሰዎች (የኢዴአፓ-መዲህንን አንጋፋ ሰዎች ጨምሮ) የተሠራውን ድርጅታዊ ሥራ/ሴራ በጣጥሶ ማለፍ አልቻለም፡፡ ከውህደት ጉባኤው በኋላም በቀሩት የሥራ አስፈፃሚ ቦታዎች ላይ በተደረገው ድልድል ስምምነት ላይ ባለመደረሱ (እነአቶ ልደቱ የፈለጓቸውን የድርጅት ጉዳይ/የህዝብ ግንኙነት ቦታዎች ባለማግኘታቸው) ክፍተቱ ይበልጥ ሊሰፋ መቻሉን መደበቅ አይቻልም፡፡

2.5. ልደቱ በውህደት ስምምነት ሰነዱ ላይ ማህተም አላደርግም በማለቱ ከላዕላይ ም/ቤቱ በተላኩ ሽማግሌዎች አማካኝነት በላዕላይ ም/ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ምክንያቱን ሲጠየቅ ኢዴአፓ-መዲኅን ቁልፍ ከሆኑ የሥልጣን ቦታዎች ሆን ተብሎ መገፋቱንና ቀደም ሲል ፕ/ር መስፍንና ዶ/ር ብርሃኑ “ከምርጫ በኋላ ኢ/ር ኃይሉን አንስተን አንተን የቅንጅቱ ፕሬዝዳንት እናደርግሃለን” የሚል ቃል ገብተውልኝ ነበር የሚል ወቀሳ አቅርቦ ነበር፡፡ ኢ/ር ኃይሉም በስሜት ተነሳስተው “ከፈለክ አሁንም ፕሬዝዴንትነቱን ላስረክብህ እችላለሁ” ብለውት ነበር፡፡ ግን ይህን ያሉት ከረፈደና ልደቱ የሆነ አቋም (no point of return) ላይ ከደረሰ በኋላ ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ ቀስተ-ደመና ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱ “የመኢአድን እብጠት ማስተንፈስና ኃይሉ ሻወልን ከሥልጣን ማስወገድ” የሚል እንደነበር በግላጭ ሲነገር እንሰማ ነበር፡፡ በኋላ ግን በተለይ በአቶ ልደቱና ዶ/ር ብርሃኑ መካከል በተፈጠረው ሽኩቻና መገፋፋት ኃይሉ ሻወልና መኢአድ የቀስተ ደመና ሁነኛ አጋር ሆነው ተገኙ፡፡

በኃይሉ ሻወል ይሁንታና በመኢአድ አባላት ርብርብ (እንዲሁም በዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ቅንነት) ባይሆን ኖሮ ዶ/ር ብርሃኑ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነት አይመረጥም ነበር፡፡ የቀስተ ደመና ሙሉ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ኢ/ር ኃይሉ ሻወልም የቅንጅቱ ፕሬዝዴንት ሆነው መመረጥ አይችሉም ነበር፡፡ የመኢአድና ቀስተ-ደመና መመሳጠርና ድርጅታዊ ሥራ/ሴራ ባይኖር ኖሮ አቶ ልደቱም የፈለገውን ሥልጣን አያጣም ነበር፡፡ አቶ ልደቱ ከሥልጣን ማዕከሉ ባይገፋ ኖሮ ደግሞ የውህዱ ፓርቲ “ቅንጅት” ህልውና አደጋ ላይ አይወድቅም ነበር፡፡ ከቅንጅት መፍረስ ጋር በተያያዘ የነገሩ አስኳልና (core issue) ቋጠሮ ያለው እዚህ አካባቢ ነው፡፡

አቶ ልደቱ ግን ይህን ሐቅ ይዞና መሬት ረግጦ ከመከራከር ይልቅ “የሥልጣን ፍላጎት አልነበረኝም/የለኝም” የሚል ጭንብል አጥልቆ ንፅህናውን ማወጅ መርጧል፡፡ ይህም ሆኖ ብዙው ሰው ንፅህናውን (ሥልጣን አለመፈለግ እንደንጽህና ከተወሰደ) ሊቀበለው አልቻለም፡፡ አቶ ልደቱ እውነቱን ይዞ ከመጣና በበኩሉ ኃላፊነቱን/ተጠያቂነቱን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ካረጋገጠ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀላሉ ይቅር ሊለውና ሊቀበለው እንደሚችል ማወቅ ነበረበት፡፡ ህዝቡ በሐቀኝነት፣ በታማኝነት፣ በቅንነት፣ በጨዋነትና በትህትና ከመጣህበት እንኳን የፖለቲካ ሥልጣን ልቡን ሊሰጥህ ይችላል፡፡

3. ፓርላማ የመግባት/ያለመግባት ጉዳይ፣

የ97 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ፓርላማ የመግባትና ያለመግባት ጉዳይ “የአርበኝነትና” “የከሃዲነት” መለኪያ ሆኖ ቀረበ፡፡ “ምርጫው በተጭበረበረበት ሁኔታ ፓርላማ መግባት የህዝብ ድጋፍ ያሳጣናል” የሚል አቋም መያዝ እንደ #አርበኝነት$ ሲያስቆጥር “የምርጫው መጭበርበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያገኘነውን ውጤት ይዘን ፓርላማ በመግባት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን ማስቀጠልና መድረኩን መጠቀም ይገባል” ማለት ደግሞ “በካሃዲነት” የሚያስፈርጅ ሆነ፡፡

በወቅቱ ህዝቡ ከነበረው ምሬትና የለውጥ ፍላጎት አንፃር ወያኔ/ኢህአዴግን ከሥልጣን ከማስወገድ በመለስ የሚያረካው ነገር አልነበረም፡፡ ስለሆነም ፓርላማ መግባትን ደግፎ መከራከር ከህዝብ መነጠልን የሚያህል ከፍተኛ ፖለቲካዊ ዋጋ/መስዋዕትነትን ሊያስከፍል ይችል ነበር፡፡ በመሆኑም እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ልደቱ አያሌውን የመሳሰሉ አንደበተ-ርቱዕና የህዝብ ስሜትን የሚከተሉ (populist) ሰዎች ቅንጅት ያገኘውን ድምፅ ይዞ ፓርላማ መግባትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን መረከብ እንዳለበት ቢያምኑም ይህን አቋማቸውን በይፋ ለማራመድ አልደፈሩም ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶችን በግል እየጠሩ ለማሳመን መሞከርን (lobbying) የተሻለ ስልት አድርገው ይወስዱ ነበር፡፡

የቅንጅት ላዕላይ ም/ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ቀናት የፈጀ ውይይት ሲያደርግም አቶ ልደቱ በነአቶ ሞሼ ሰሙና አብዱሮህማን ጀርባ ተጠልለው ካልሆነ በስተቀር በዚህ ጉዳይ ላይ አጥብቀው ሲከራከሩ አልተሰሙም፡፡ አቶ ልደቱ በቃለ-ምልልሱ ፓርላማ በመግባት/ባለመግባት ዙሪያ አይቤክስና ግሎባል ሆቴሎች የተደረጉ የምክክር መድረኮችን ጠቅሶ የቅንጅት ላዕላይ ም/ቤትን ስብሰባና ያሳለፈውን ውሳኔ እንደዋዛ ሲያልፈው ታዝቤያለሁ፡፡ ይልቁንም ዐይኑን በጨው ታጥቦ “እኔ ፓርላማ የገባሁት በፓርቲዬ ውሳኔ ነው” በማለት ሲናገር ትንሽ ህሊናውን አይሰቀጥጣቸውም፡፡ ይህን እውነት ፈታ አድርገን ስናየው፣

3.1. ኢዴፓ-መዲህን እንደፓርቲ መስከረም 11 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ህልውናውን አክስሟል፡፡ አቶ ልደቱን ጨምሮ በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡት 18 ሰዎች የተላኩት በውህዱ ቅንጅት ላዕላይ ም/ቤት በአባልነት እንዲሳተፉ እንጅ የኢዴፓ-መዲህን አመራር ተብለው አልነበረም፡፡ በኢዴአፓ-መዲኅን መተዳደሪያ ደንብና ድርጅታዊ መዋቅር መሠረት 18 ሰዎችን የያዘ የአመራር አካል አይታወቅም፡፡ በደንቡ መሠረት የኢዴፓ-መዲህን አመራር በዶ/ር አድማሱ ገበየሁ የሚመራው አካል ነበር፡፡ በውህደት ስምምነቱም ላይ ኢዴአፓ-መዲኀንን ወክለው የፈርሙት ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ እንጅ አቶ ልደቱ አልነበሩም፡፡ አቶ ልደቱ በኢዴአፓ-መዲኅን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተመረጡ ህጋዊ መሪ ቢሆኑ ኖሮ በውህደት ስምምነቱ ላይ መፈረም የነበረባቸው እሳቸው ነበሩ፡፡ ግን አልነበሩም፡፡

3.2. ኢዴአፓ-መዲኅን በውህደቱ ለመቀጠልም ሆነ ውህደቱን አፍርሶ ለመውጣት፣ እንዲሁም ፓርላማ መግባት/አለመግባትን በሚመለከት መወሰን የነበረበት/የሚችለው (ለዚያውም የፓርቲው ህልውና አልከሰመም ከተባለ) በዶ/ር አድማሱ ገበየሁ የሚመራው መዋቅራዊ አካል እንጅ በአቶ ልደቱ የሚመራው “የእንቢተኞች ስብስብ” አልነበረም፡፡ ኢዴአፓ-መዲኅንን ወክለው በውህዱ ፓርቲ “ቅንጅት” ላዕላይ ም/ቤት ከሚሳተፉት 18 በሰዎች ውስጥም አብዛኞቹ ከአቶ ልደቱ በተቃራኒው የቆሙና የቅንጅቱን ህልውና ለማስቀጠል ብዙ ጥረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ስለሆነም አቶ ልደቱ የ18ቱን ሰዎች ድጋፍ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን “ባለቤቷን የተማመነች በግ …” እንዲሉ በወቅቱ እነአቶ ልደቱ ደንብና ህግ ከመጣስ የሚያግዳቸው ኃይል አልነበረም፡፡ ስለዚህ ቅንጅቱን አፍርሰው ለመውጣትም ሆነ ፓርላማ ለመግባት በግላቸው እንጅ በፓርቲ ደረጃ የተወሰነ አልነበረም፡፡

3.3. እነአቶ ልደቱ ፓርላማ ከገቡም በኋላ በኢዴፓ መዲኅን ሥም ለህግና ለመርህ ተቃራኒ የሆኑ አካሄዶችን ተከትለዋል/ተጠቅመዋል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያህል፣ ቀደም ሲል የኢዴአፓ-መዲኅን አባል የነበሩና በቅንጅት ሥም ተወዳድረው የተመረጡ ሰዎችን የኢዴአፓ-መዲኅን አባላት ናቸው ብለው ድርቅ አሉ፡፡ ሰዎቹ ደግሞ “የለም፣ እኛ የውህዱ ቅንጅት አባላት ነን፤ የተመረጥነውም በቅንጅት ሥም ስለሆነ በፓርላማም ውስጥ የቅንጅትን ውክልና ይዘን እንቀጥላለን” አሉ፡፡ በኋላ በአሜሪካን ኤምባሲ (ቬኪ ሀልደትሰን) አደራዳሪነት (አቶ ተመስገን ዘውዴን በማሳሳት) ሰዎቹ ድምፃቸውን ለፈለጉት ቡድን (ለቅንጅት) እንዲሰጡና ለእሳቸው የሚሰጠው የአየር ሠዓት ግን ለነአቶ ልደቱ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በወቅቱ የፓርላማው አፈ-ጉኤ የነበሩት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ጋር ቀርበን ይህን ማድረግ አግባብ እንዳልሆነ ለማስረዳት ብንሞክርም “አሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የተደረገ ስምምነት ስለሆነ እኔ በዚህ ውስጥ አልገባም” በሚል ቢሮክራሲያዊ ቋንቋ አስተዳደራዊ ፍትህ ነፈጉን፡፡ ጉዳዩን ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወስደን አቤት ብንልም “በፓርላማ አሠራር ጣልቃ አንገባም” በሚል “የተቋማዊ ገለልተኝነት” መርህ ሽፋን ተባባሪነታቸውን አረጋገጡልን፡፡ በዚህ ሁኔታ እነአቶ ልደቱ “ቅንጅት ነን” የሚሉ ሰዎች አንደበት ነን ብለው አምስት አመት አውርተው ወጡ፡፡ ዛሬ ላይ አቶ ልደቱ በፓርቲዬ ህግና ውሳኔ መሠረት ሲሉ እነብሩ ብርመጂ በህይወት የሉም፣ እነአግባው ሰጠኝ፣ እነአንዷለም አያሌው በአደባባይ ሊሞግቱኝ አይችሉም ብለው ይሆን? ሌላው ቢቀር እነተመስገን ዘውዴ፣ እንዳልካቸው ሞላ ትንሽ ይታዘቡኛል ብለው አይፈሩም?

4. የህዝብን ስሜትና እሴቶች መጠበቅ፣

አቶ ልደቱ አያሌው የታዋቂነቱን ያህል አወዛጋቢ ፖለቲከኛ መሆኑን ራሱም ያምናል፡፡ እንደ እሱ እምነት ምናልባት የውዝግቡ መንስኤ አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም እሱ የውዝግቡ ማዕከል ሆኖ ሳለ ለችግሩ ሌሎችን ተጠያቂ (externalize) ለማድረግ ሲሞክር ማየት ፈገግ ያሰኛል፡፡ በዚህ መንፈስ እንዴት ነው ፖለቲከኛ መሆን የሚቻለው?

ፖለቲካ በጥሬው የህዝብ ጉዳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ፋይዳም የህዝብን ፍላጎት፣ ጥቅምና መብት ማስጠበቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝብ ይሁንታና ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ለአቶ ልደቱ ግን የህዝብ ይሁንታና ድጋፍ ብዙም ደንታ የሚሰጠው አይመስልም፡፡ ስለሆነም የህዝቡን ልብና በጎ ፈቃድ ለማግኘት አልሞከረም፡፡

እንደ እውነቱማ፣ የሂደቱ አካል እንደነበረና የውዝግቡ ማዕከል እንደሆነ ሰው ቢያንስ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረው ግርታና አሉታዊ ስሜት ሊያስጨንቀውና የጥፋተኝነት ስሜት ሊፈጥርበት በተገባ ነበር፡፡ ከዚህም ተነስቶ ቢያንስ ጠቅለል ባለ አነጋገር በሂደቱ በግሉ የነበረውን ድርሻ ማሳየትና በዚህ ሳቢያ ለተፈጠረው ሁሉ በበኩሉ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ነበረበት፡፡

አቶ ልደቱ ለህዝብ ስሜትና እሴቶች የማይጨነቅ ያስመሰለበት ሌላው ነገር በትዳር አስፈላጊነትና በአኗኗር ዘይቤው (life style) ዙሪያ ለማስረዳትና ሌሎችንም ለማሳመን ያደረገው ሙከራ ነው፡፡ በርግጥ የግል እምነቱና የአኗኗር ዘይቤው የራሱ ነው፤ ሊከበርለትም ይገባል፡፡ ነገር ግን ከሞራል አንፃር ስሱ የሆነን ጉዳይ (sensitive issue) እንዴት ነው በአደባባይ መግለፅ የነበረበት? በተለይ ለሌሎች (ለትውልዱ) አርኣያ መሆን መሆን እንዳለበት ታዋቂ ሰው/ፖለቲከኛ አቀራረቡ ምን ያህል ርቀት ያስኬደዋል?

፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፤፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፤፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
እንደማጠቃለያ፣

ከዚህ በፊት “ልደቱ እንደገና” በሚል ርዕስ አሁን ካለንበት ሁኔታ አንፃር እንደሱ ዓይነት ትንታግ ፖለቲከኛ ያስፈልገናል በሚል ዕድሉ ቢሰጠው የሚል ሀሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ እኔ በሂደቱ ውስጥ እንደነበረ ሰው የእያንዳንዳችንን ድክመትና ጥንካሬ፣ እንዲሁም ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ የነበረንን ድርሻ በቅርብ አውቃለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ልደቱ በሂደቱ ስለተጫወተው አዎንታዊም አሉታዊ ሚና ለማወቅ የተሻለ ዕድል ነበረኝ፡፡ ያም ሆኖ ከፍፁም ቅንነትና የሀገር ተቆርቋሪነት በመነጨ የህዝቡን ይቅርባይነትና በጎ ምላሽ መጠየቄ አልቀረም፡፡ ለዚህም አቶ ልደቱ በሂደቱ ስለነበረው ድርሻ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድና በዚህ ሳቢያ ስሜቱ የተጎዳውን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ነበረበት፡፡ አሁንም የረፈደ አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብኮ በ97 ምርጫ ዋዜማ አቶ ልደቱ በቢሮው በደህንነት ኃይሎች ታገተ ተብሎ በፆም በፀሎት መቆራመዱ መዘንጋት የለበትም፡፡

ጆሲን በተመለከተ፣

ይህ ወጣት አርቲስትና የበጎ አድራጎት ሰው በርካታ የሚደነቁ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ አሁንም ከተለመደው አቀራረቡ ወጣ ብሎ እንደአቶ ልደቱ ዓይነት የፓለቲካ ሰዎችን መጋበዙ የሚበረታታ ነው፡፡ ሆኖም ግን እንደልደቱ ካለ አወዛጋቢ ፖለቲከኛ ጋር ቃለ-ምልልስ ለማድረግ አስፈላጊውን መረጃ/ማስረጃ ማሰባሰብና በወጉ መሞገት ነበረበት፡፡ ይህን ሳያደርግ አቶ ልደቱን አቅርቦ ህዝቡን ለማዝናናት አስቦ ከሆነ ግን እሱም ሆነ ፕሮግራሙ ኢላማውን ስቷል ማለት ይቻላል፡፡

LEAVE A REPLY