/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የሶማሊያ የፓርላማ ኮሚሽን ባለፈው ነሐሴ ወር ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው የተሰጡት የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴና ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር አቶ አብዲከሪም ሙሴ በህገ-ወጥ መንገድ መሆኑን ዛሬ አስታወቀ።
ፓርላማው ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በሗላ አቶ አብዲከሪምን የሶማሊያ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ከህግ ውጭ አሳልፎ እንደሰጣቸው ዛሬ የወጣው መግለጫ አመላክቷል።
ፓርላማው በተጨማሪም አብነግ ሽብርተኛ ድርጅት አለመሆኑንም ገልጿል። አቶ አብዲከሪም ሙሴን በህገ-ወጥ መንገድ ለኢትዮጵያ መንግሰት አሳልፎ የሰጠው የሶማሊያ ብሄራዊ መረጃና የደህንነት ኤጀንሲውን ጥፋተኛ አድርጓል።
የብሄራዊ ደህንነት መስሪያ ቤቱ መተሳሳተ መረጃ ተመርኩዞ ሰውየውን አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግስት ከመስጠቱ በፊትም ለፍትህ አካላት ጉዳዩን ማሳወቅ እንደነበረበት ፓርላማው በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ፌርማጆ የሶሚሊያ ዜጋቸውን የጦስ ዶሮ ያደረጉት ከኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ድጋፍ በመሻት ነው የሚሉ አስተያየቶች በርካታ ናቸው። ኦብነግ በ1973 ዓ.ም አካባቢ እንደተመሰረተና ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚታገል ቡድን ነው። የኦብነግ ከፍተኛ የአመራር አባል ባለፈው ነሐሴ ወር በኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላን ከሶማሊያ እንዲመጡ ከተደረገ በሗላ በደብረ ዘይት አየር ሀይል ግቢ ውስጥ መታሰራቸው ይታወቃል።በወቅቱ ኢትዮጵያም ከሁለት መቶ በላይ ሶማሊያዊያን እስረኞችን አሳልፋ መስጠቷም መዘገቡ ይታወሳል።