/ክንፉ አሰፋ/
“ሃፍታም የምትሆነው ህወሃት ወይንም ኤፈርት ሲለቅቀኝ ብቻ ነው!” ብላ ከነገረችን ገና መንፈቅ እንኳ አልሞላም። ከጥልቅ ተሃድሶ እና ከመተካካት ቀጥሎ የተመሰከረለት የአዜብ ጎላ መሪ ቃል ነበረች። የመልቀቁን ጨዋታ ለኛ ተየት አድርጊያትና መሪርዋን ጽዋ ተጎንጪ ሲሉ እነሆ መርዶውን ነግረዋታል። ሂስዋን አልውጥም ብላ ከመቀሌ እንደፈረጠጠች በዚያው ቀርታለች። መቼም “መለስ የሞተው አሁን ነው!” ሳትል አትቀርም በልብዋ። የዛሚዋ ደላሊት እድል አትሰጣትም እንጂ፣ ይህንኑ የልብዋን ሃሳብ “ለሚወዳት ሕዝብ” ትተነፍሰው ነበር። ግን ምን ያደርጋል? የወደቀ ፈላጊ አይኖረውም። ቀልደኛይቱ የጎላ ልጅ ፣ “ድሮስ ቢሆን ድሃን ማን ይወደዋል” ማለትዋ በፌዝ ቡክ ላይ አነበብን።
አዎ! አዜብ መስፍን ከታሰረችበት የህወሃት ጎራ አሁን ተለቅቃለች። ቃል እንደገባችውም የድህነትን በሽታ ከራስዋ ላይ የምታባርርበት ግዜ አሁን ነው። ጉልት ቁጭ ብላ ቸርችራ ሃብታም እንደምትሆን ታሳየናለች። ይህንን ስታደርግ ታዲያ የባለ ራዕዩን “ታላቁ መሪ” ፎቶ ከአጠገብዋ ማራቅዋን እንዳትዘነጋ። አንዲት ድሃ እናት ጉልት ተቀምጣ ውላ ልጆችዋን እንዴት እንደምታሳድግ በቃል ሳይሆን በተግባር ስታሳየን – ያኔ እናምናታለን። እርግጥ የፖለቲካ ሀ-ሁ በውል ሳይገባትና ከአመራር እውቀት ነጻ ሆና እስካሁን መርታለች። የመኖርዋ ትርጉም የተቋጨው የመልስ ሚስት በመሆንዋ ብቻ ባገኘችው በዚሁ እድል ፈንታዋ ነበር። የአርባ ቀን እድልዋን በዜሮ እስካባዙባት እስከዛሬዋ ሰዓት በርግጥም ቀልዳብን ነበር።
ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መባረርዋ የባንክ ሂሳቧ ላይ አንዳች ሃሳብ አያመጣባትም። ከህወሃት የገንዘብ ክምችት ከሆነው ኤፈርት ያስወገድዋት ቀን ግን የተመኘችው ጉልትዋ ተቀምጣ ስትቸረችር እናያት ይሆናል። ለዚያም እድል ከሰጥዋት! ሰዎቹ ወገብዋ ላይ መቆማቸው እርግጥ መሆኑ የታወቀው የአድዋው ጸረ-ሙስና ቡድን የአዜብ ፋይሎችን አዋራ እያራገፈ መሆኑ ሲሰማ ነው። በነገራችን ላይ ከ 16 ዓመት በፊት መለስ ዜናዊ፣ ስብሰባ ረግጠው በወጡት በእነ አቶ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ፣ ስዬ አብርሃ፣ ጀነራል ፃድቃን ገ/ተንሳኤ ላይ የወሰደው እርምጃ ነው አሁን በአዜብ ላይ የደረሰው። እነ ስዬ በወቅቱ አብዛኛ ድምጽ ቢኖራቸውም እንደወጡ በዚያው ቀሩ። ከጸረ-ሙስናው በትርም ሊያመልጡ አልትቻላቸውም ነበር። የሚገርመው፣ ያ ታሪክ መደገሙ ሳይሆን የቅጣት ዱላው በበቀጭዋ አዜብ ላይ መዞሩ ነው።
ጎናቸው እየተመታ ያለው እነ ሳሞራ የኑስ አውቆ እንደተኛ ዝም ብለው አድፍጠዋል። እንደ መርዘኛ እባብ ራሱን ቀብሮ የመቀሌውን ድራማ መጨረሻ የሚጠብቀው ቡድን ዝምታም የአድዋውን ቡድን ስጋት ውስጥ መጣሉ ግልጽ ነው።
“የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።” የሚለውን ዜና ሲያሰሙን ትልቅ ለውጥ የመጣ መስሎን ነበር። በሕዝብ ጫንቃ ላይ ለየ27 አመታት ሸክም የሆኑት ታሰሩ የሚል ዝርዝር ስንጠብቅ ይልቁንም ሰለ አዜብ እና ስለ ቦታ መቀያየር ይነግሩናል።
አድዋዎች ከመቀሌ፣ መቀሌዎች ከአዲግራት፣ አዲግራቶች ከኤርትራዎች… የሚያደርጉት የፍትጊያ ድራማ አሁንም መስመር አልያዘም። የድራማው ዣነር ኮሜዲም ትራጀዲም ነው። በታንክ እና መትረየስ መታጀቡ ድግሞ ጦርነትም አስመስሎታል። በሴራ፤ ሽብር እና ብቀላ ዙርያ ባጠነጠነው በዚህ ማራቶን የአድዋዎቹ ጡንቻ ለግዜውም ቢሆን ፈርጥሞ፣ ሌሎቹን ሲያብጠለጥል፣ ያሻውን ሲያወርድና ያሸውን ደግሞ ሲሰቅል ከርሟል። የተነካው ወገንም የተኛ መስሎ ሹክሹክታውን እያደመጠ ነው። ምን ይታወቃል የስብሃት ቡድን ገና የአሸናፊነት ድሉን ሳያጣጥም ሃዘን ይቀመጥ ይሆናል።
ሰሞናዊው የመቀሌ ፉክቻ፤ በሰባዎቹ የነበረውን የኡጋንዳ ድራማ ያስታውሰናል። ሚልተን ኦቦቴ እና ኢድ አሚን ዳዳ፤ ተባብረው፣ ተሰባብረው፣ በለስም ቀንቷቸው የስልጣን ማማ ላይ ጉብ እንዳሉ፣ ከበድ ያለ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ነበር የተሰማሩ። የሃገሪቷን ወርቅና የዝሆን ጥርስ ሁለት ሆነው ጋጡት። ዘረፋው ላይ ምንም ጸብ አልነበረም። ችግሩ የመጣው የሃብት ክፍፍሉ ላይ እንደደረሱ ነው። ከዚያ በኋላ አብረው መብላት አልቻሉምና ተለያዩ። ብሄራዊውን ጉዳይ ረሱትና። ግዜያቸውን የሚያጠፉት አንዱ ሌላውን ማጥፋት ላይ ሆነ። የታሪክ መዛግብት እንደሚለን ሁለቱ የሰው ጅቦች በመፈንቅለ መንግስት እየተገለባበጡ ሃገሪቱን በፈረቃ መግዛትን ያዙ። መተካካት!
“የኢትዮጵያን ችግር ሊፈቱ” መቀሌ ላይ የተሰበሰቡት ዱዶች ነገር እንደ አዲስ ማስገረሙ አልቀረም። የሚዘርፉት እነሱ፣ የሚገድሉት እነሱ፣ የሚተካኩት እነሱ፣ የሚታደሱት እነሱ፣ የሚገመግሙት እነሱ፣ የሚገመገሙትም እነሱ! ስለሆኑ የኢትዮጵያ ጉዳይ የትግራይ ብሄረተኞች ጉዳይ ብቻ ነው ብለው ከደመደሙ ሰነባበቱ። የመቀሌውን ክስተት መተካካት እንበለው ወይንም መክካካት ግና ሃገሪቱ ለገባችበት ቀውስ ምንም ፋይዳ የለውም። የህወሀት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ኘሬዝደንት የሆኑትን አቶ አባይ ወልዱን ከዚያ አንስቶ እዚያ ማስቀመጥ ለውጥ አይደለም። የኤፈርት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ በየነ ምክሩ፣ ከፓርቲው ሥራ አስፈፃሚነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴነት አባልነት ማዛወር እርምጃ ሊሆን አይችልም። ባልዋ በህይወት እያለ የቀለደችባቸው አዜብን መገፍተርም እንዲያው ከአህዮች እርግጫ አያልፍም። አህያ ለአህያ ቢራገጥ ደግሞ ጥርስ አይዋለቅም።
በዚህ ሁሉ መሃል ግን ቀረብ ብሎ የሚታይ ነገር አለ። መፍትሄ ያልተገኘለት ችግር፣ የማይታረቅ ቅራኔ፣ የማያባራ ሽኩቻ። ….