የሚወራውን ነገር ወንድሟ ሊያደርገው እንደማይችል እርግጠኛ ነበረች….. ሽኩር ገና እኮ የ13 አመት ልጅ ነው….‹ ሳልማ› በ20ዎቹ እድሜ ውስጥ ያለች ሴት ናት…..ሽኩር በምን አቅሙ ያስገድዳታል?!
ሰኔ 22 , 2002 ዓ.ም (እኤአ) ምሽት የሙክታራን ቢቢ (ማይ) ቤተሰብ በጭንቀት ተውጧል…. ተወዳጁ ወንድሟ የ13 ዓመቱ ሽኩር በአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑት የማስቶዊ ጎሳዎች እጅ ወድቋል….. ብዙ ድብደባ እና ስቃይም እንደደረሰበት እየተወራ ነው፡፡ ጉዳዩን በእርቅ ለመፍታት የተደረገው የአባቷ እና የአጎቷ ሙከራ ምንም የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡
አካባቢው ላይ አንዳች ችግር በገጠመ ቁጥር የሚሰበሰበው እና ውሳኔ የሚያስተላልፈው ሸንጎ በአብዛኛው በማስቶዊ ጎሳ አባላቶች የተሞላ ነው…..እውነተኛ ፍርድ እንዴት ማግኘት ይቻላል? መሃል ከተማ ኢዝላማባድ ውስጥ በከፍተኛ የመንግስት ማዕረግ ላይ የሚገኙ ሰዎች ዘመዶቻቸው ናቸው….. ማስቶዊዎች እጃቸው ረጅም ነው፡፡
አሁን ደግሞ በሸንጎ ላይ ከሽኩር አባት እና አጎት ውጭ ሌላ ከቤተሰቡ ውስጥ አንዲት ሴት መገኘት አለባት…..ይህ ካልሆነ ሽኩር አይለቀቅም ተብሏል….. ያቺ መገኘት ያለባት ሴት ደግሞ ሙክታራን ማይ ናት፡፡
‹‹ለምን ግን እኔ በሸንጎ ቦታ እንደገኝ ፈለጉ? ›› አባቷም ሆኑ አጎቷ በቦታው ብትገኝ አደጋ ሊኖረው እንደሚችል ከመግለፅ ያለፈ ሌላ መልስ አልነበራቸውም……. ግን ደግሞ በቦታው ባትገኝ የታናሽ ወንድሟ እጣፈንታ ምን ይሆናል?
ደግሞም እሷ የሰፈር ልጆችን ሰብስባ ቁርአን በማስቀራት ምስጋና የተቸራት ፈጣሪዎን የምታከብር የምትፈራ ሴት ናት…..ብትሄድ ምን ሊያደርጓት ይችላሉ?
‹‹ቁርአኔን በደረቴ አቅፌ እሄዳለሁ…..ሌላ ነገር እናድርግሽ ቢሉም በአላህ ስም እለምናቸዋለሁ…. ይህን አልፈው ምንም አያደርጉኝም›› የሚል እምነት ነበራት……..
ሸንጎው የግራ እና የቀኙን በማድመጥ ጊዜ አላጠፋም…..ቀድሞውኑ ተዘጋጅቶ የነበረው ውሳኔ የሙክታራን በቦታው መገኘት ተከትሎ ተደመጠ…….
‹‹ታናሽ ወንድም አጠፋው ለተባለው ጥፋት እህቱ ሙክታራን እንድትቀጣ ተወሰነ!!!››
ቅጣቱም ‹‹የማስቶዊ ጎሳ አባላት በሆኑ ሰዎች በቡድን እንድትደፈር ነበር……..››
አባቷ እና አጎቷ ከእነዚህ አውሬዎች ሊያስጥሏት የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም……. አንደኛ፡ ማስቶዊዎች መሳሪያ ታጥቀዋል….ብዛት አላቸው፡፡ ሁለተኛ፡ ይህ የአካባቢው ወግ ነው…. ወንድም ሲያጠፋ የምትቀጣው እህት ናት…… እንደ ጦስ ዶሮ፤ እንደ መስዋዕት በግ፤ እንደ አዛዜል ፍየል….የወንድምን ሀጥያት ተሸክማ የምትባዝነው እህት ናት!!!
በደረቷ የታቀፈችውን ቅዱስ ቁርአን ነጥቀው….. ‹‹በአላህ›› ‹‹በአላህ›› የሚለውን ልመናዋን እና ጩኸቷን ከቁብ ሳይቆጥሩ መሬት ለመሬት እየጎተቱ ወስደው ለአራት ‹‹ጨፈሩባት›› እየተደጋገሙ እየተደጋገሙ……እየተደጋገሙ……በመጨረሻም ራሷን ሳተች
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ….. የከተማው ሰው አደባባይ ወጥቶ እያያት እርቃኗን ወደ ቤቷ እንድትሄድ ተደረገ……..
እንዲህ ያለ ነገር በአካባቢው ሲፈፀም ሙክታራን ላይ የመጀመሪያው አልነበረም……. በእንዲህ አይነት ሁኔታ እንዲዋረዱ የተደረጉ ሴቶች ከቀናት በኋላ ራሳቸውን ያጠፋሉ….
ሙክታራንም ራሷን ለማጥፋት በተደጋጋሚ አስባለች….. እንባ እና ሳግ እየተናነቃት ይህን ውርደት ተሸክማ እንዴት ዳግም በሰው ፊት ቆማ ልትራመድ እንደምትችል አስባለች…….
ግን ከሁሉም በላይ እልህ … ንዴት እና በቀል የህይወቷን አቅጣጫ ቀየሩት…..
በእሷ ላይ የተደረገውን የሰሙ ጋዜጠኞች ወደ ትንሽዋ የሙክታራን መንደር ሚርዋላ ተመሙ….. ሙክታራንም እነዚህን አውሬዎች በህግ ፊት የምትፋለምበት እድል አገኘች….. ከእሷ በፊት ማንም ያልሄደበትንም መንገድ ወገቧን ታጥቃ ሄደችው፡፡
በታላላቅ መገናኛ ብዙሀን ላይ የሀገሪቱ ስም መጥፋት ያሳሰበው የፓኪስታን መንግስት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አደረገላት…..ካናዳን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሊያስጠልሏት ፍቃደኛ መሆናቸውን ገለፁ…..
ሙክታራን ግን አላደረገችውም…….ከሀገሬ የትም ንቅንቅ አልልም…… ልትረዱኝ የምትፈልጉ ካላችሁ እዚሁ በትውልድ መንደሬ ትልቅ ትምህርት ቤት መክፈት እፈልጋለሁ እና አግዙኝ …..ችግራችን መሀይምነታችን ነው አለች፡፡
አሁን በሚርዋላ ግዛት ሙክታራን ትልቅ ትምህርት ቤት አላት…… ሙክታራን በአካባቢው በወንዶች ለተጎዱ ሴቶች ሁሉ መጠለያ ሆናለች….. የሙክታራን ቤት ውስጥ ብዙ ከባላቸው ሸሽተው የመጡ ሴቶች ይኖራሉ…..ገሚሶቹ አፍንጫቸው በባሎቻቸው የተቆረጠ….ገሚሶቹ በአሲድ ፊታቸው የተበላሸ…..ገሚሶቹ…….. ናቸው፡፡ ሙክታራን ተስፋ ሆናቸው አብረዋት ይኖራሉ፡፡
በ2017 መግቢያ ላይ ደፋሪዎቿ በቂ ምስክር ስላልቀረበባቸው በሚል ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጥተዋል…..አሁንም ይዝቱባታል…. እሷ ግን…ሀገሯን….ህፃናት ተማሪዎቿን….. እነዛን ሁሉ ሴቶች ትቼ መሄድ እንዴት ይሆንልኛል ብላ አሁንም በገዳዮቿ መንደር ትኖራለች፡፡
በዚሁ በያዝነው በ2017 ዓ.ም በወንድሟ ጥፋት ማካካሻነት በቡድን የ12 አመት ሴት መደፈሯን ተከትሎ ሙክታራን በፃፈችው ፅሁፍ ላይ
‹‹የ15 አመት ትግሌ ከንቱ ቀረ ማለት ነውን? ፍሬስ አላፈራሁምን?›› ስትል በተስፋ መቁረጥ በተሞላ ድምፅ ራሷን ትጠይቃለች……ፓኪስታን ለሴቶች እጅግ በጣም አስቸጋሪ ከሚባሉ ሀገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች……..
ሙክታራን አሁንም ኑሮዋንና ትግሏን በፓኪስታን ቀጥላለች!!!
/የሙክታራን ማይን ሙሉ ታሪክ ማንበብ የሚሻ ካለ ከላይ በምስሉ ላይ የሚታየውን In THE NAME OF HONOUR የተሰኘውን መፅሀፍ እንዲያነብ እጋብዛለሁ/