“ሌሎችን ነጻነት የሚከለክሉ እነሱም አይገባቸውም…” – የሊቢያው የባርያ ንግድ /ኤፍሬም እንዳለ/

“ሌሎችን ነጻነት የሚከለክሉ እነሱም አይገባቸውም…” – የሊቢያው የባርያ ንግድ /ኤፍሬም እንዳለ/

“እኔ 800 ዲናር!”

“እኔ 1‚000 ዲናር!”

“እኔ 100 ጨመሬ 1‚100 ዲናር!”

“1200 ዲናር!”

አለቀ፡፡ በ1‚200 ዲናር የጨረታው አሸናፊ ታወቋል፡፡ ያሸነፈበትን እቃ ወይም ነገር ይቀበላል፡፡ ለጨረታ የቀረበው ጂ ፕላስ ምናምን ቤት አልነበረም፡፡ የአንድ አውራጃ በጀት ጭጭ የምታደርገው ቪ ምናመን መኪና አልነበረችም፡፡ እንደዛ አየተጯጯሁ የተጫረቱበት ሰው ነበር፡፡ በባርነት እየተሸጠ የነበረ ጥቁር አፍሪካዊ፡፡

“እናስ ምን ይሁን ! የአፍሪካውያን በባርነት መሸጥ ድሮም የምናወቀው አይደለም እንዴ! ለምንድነው እንደ አዲስ የሚወራልን ?” ሊባል ይችላል፡፡ እንደ አዲስ የሚወራልንማ ይህኛው አዲስ ስለሆነ ነው፡፡ አዲስ የባሪያ ፍንገላ ዘመን … ሊቢያ በምትባል አገር በአደባባይ እየተካሄደ ያለ ጥቁር አፍሪካውያን የሚሸጡበት፣ የሚለወጡበት የባሪያ ንግድ!

አፍሪካውያኑ እዛ ስፍራ የተገኙት ለአንድና ለአንድ ምክንያት ብቻ ነው … የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አውሮፓ ለመሻገር፡፡ አገሮቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ለእነሱ አልሆኑላቸውም፡፡

ገሚሶቹ በፖለቲካ አመለካከታቸው መንግሥቶቻቸው ያሳድዷቸዋል፣ ገሚሶቹ ቢሉ፣ ቢሉ ኑሮና ብልሀቱ አልሳካ ሲላቸው፡ “እስቲ ሌላ ቦታ ሄጄ እድሌን ልሞክር፣” ያሉ ናቸው፡፡ አንድ ትልቅ እርግማን የሆነው ግን ሊቢያ የምትባል አገር እዚህ መንገዳቸው ላይ መኖሯ ነው፡፡

“ሌሎችን ነጻነት የሚከለክሉ እነሱም አይገባቸውም…” ብሏል አሉ አብረሀም ሊንከን፡፡

በእርግጥ በሊቢያም ሆነ በሌሎች የዓረብ ሀገራት ያለው የቀለም ልዩነት አዲስ ዜና አይደለም፡፡ ዘመናት ያሰቆጠረ ነው፡፡ ሰዎቹ ድሮም ባሪያ ፍንገላ ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ናቸው፡፡ በተለይ የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ያልፉ ነበር፡፡ በበዙ ሀገራት በአደባባይ ማጫረት ደረጃ ላይ ባይደርስም አሁንም ድረስ ሁኔታው የባሰበት ነው፡፡

ነገሮች “ምንም ቢሆን አገር ይሻላል፣ ቆሎ እየቆረጠሙ በጣሳ ውሀ እያወራረዱ መኖር ይቻላል፣” እንደሚባለው አይነት ከመሆን አልፈዋል፡፡ ቆሎም ቢሆን በቀላሉ የሚገኝ አልሆነም፣ ጣሳ ውሀ ቢሆንም እንደተፈለገው የሚገኝ አይደለም፡፡ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት፣ እኛንም ጨምሮ፣ ኑሮ፣ “ወተቱ ከጓዳ እሸቱ ከጓሮ” የሚባለበት አልሆነም፡፡ ስለሆነም ስደቱ ይቀጥላል፣ እንደውም መሬት ላይ ያሉት ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት እየጨመረ የሚሄድ ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡

ስለሆነም የሊቢያው የባሪያ ንግድ ከአሁኑ ወሳኝ እርምጃ የሚወሰድበት ካለሆነ ወደ ሌሎች ሀገራት ላለመስፋፋቱ ምንም ማረጋገጫ አይኖርም፡፡ ምናልባትም እንደ ሊቢያ በግልጽ ባይሆንም አሁንም አለ የሚባለው የስውር የባሪያ ንግድ ሊሰፋፋ ይችላል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ‘ውጉዝ ከመአረዮስ’ ከማለት አልፈው ክንዳቸውን የሚያነሱ ሆነው አልተገኙማ ! ስለሆነም ስደተኞቹ ጠባቂ፣ ተሟጋች አይኖራቸውማ!

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ ከሰባት መቶ ሺህ እስከ አንደ ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች አሉ፡፡ እንደምንም ተሳከቶላቸው አወሮፓ የሚደርሱ የሰቆቃ ታሪኮቻቸውን ለሚሰማቸው ይተርካሉ፡፡ “ሊቢያ ገሀነም ነበረች፡፡

አንድ የሚለሽያ ቡድን ይይዘኛል ወይም በባርነት ይሸጡኛል እያልኩ በስጋት ነበር የምኖረው፣” ብሏል አንድ የአይቮሪኮስት ስደተኛ፡፡ የ22 ዓመቱ ሳኖጎ የተባለ ስደተኛ ፖሊሶች ነን ያሉ ሰዎች ከያዙት በኋላ ለባሪያ ነጋዴ እንደሸጡትና ከዛም ተገዶ ቲማቲም እርሻ ላይ ይሠራ እንደነበር ተናግሯል፡፡

ሊቢያ ውስጥ ያለው ከሰብአዊነት በእጅጉ ያፈነገጠ ጭካኔ ለዓለም አዲስ አይደለም፡፡ ግን ማንም እንደዚህ በአደባባይ የሰው ልጅ በባርነት የሚሸጥበት፣ የሚለወጥበት ደረጃ ይደርሳል ብሎ አላሰበም፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ማለትም ከናይጄሪያ፣ ከጊኒ፣ ከቡርኪና ፋሶ ወይም ከአይቮሪኮሰት የሄዱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የኤርትራውያንና ሶማሊያውያን ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡ የአገራችን ልጆች ብዛትም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ ሊቢያ ውስጥ የባሪያ ንግድ ይካሄድ እንደነበር መወራት ከጀመረ ዓመት አልፏል፡፡ ግን ወሬ ብቻ ሆኖ ከርሞ በቀደም ሲ.ኤን.ኤን. ባስተላለፈው ጥናታዊ ዘገባ ሁሉንም ነገር አፈረጠው፡፡

የፈረንጆቹ ዓመት ከገባ ወዲሀ 160‚000 ስደተኞች ሜዲቴራኒያንን አቋርጠው አውሮፓ ደርሰዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ጊዜ ወደ 3‚000 የሚጠጉት ባህር ላይ አልቀዋል፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ የአፍሪካውያን ስደት ነገር፡፡

የሊቢያው አመጽ የተነሳ ጊዜ ምዕራባውያኑ ሀገራት “ይበል! ይበል!” አሉ፡፡ “ውረድ በለው፣ ግፋ በለው” እንዳሉትም ሆነላቸውና ጋዳፊ በአስቀያሚ ሁኔታ ወንበራቸውንም፣ ዓለምንም ተሰናበቱ፡፡ ሊቢያም ወደ ትርምስምሱ ገባች፡፡ ይሄን ጊዜ “አይዟችሁ፣ አንበሶቻችን!” ይሉ የነበሩት ሁሉ ምስቅልቅሉን ማርገቢያ መላ አልነበራቸውም፡፡

አገሪቷ ከደጡ ወደ ማጡ እየተንሸራተተች፣ አንድ ሳይሆን ሁለት ትልልቅ መንግሥታትና፣ የመሳፍንት በሚመስሉ በርካታ ታናናሽ ኦፊሴላዊ ያልሆኑ ግዛቶች ተከፋፈለች፡፡

ለአንዳንድ ተንታኞች የሰሞኑ የባሪያ ንግድ ወሬ ያላሰደነቃቸው አገሪቱ ከጋዳፊ በኋላ እየሄደችበት ያለውን ሰርዓተ አልበኝነት በመንተራስ ነው፡፡ የታጠቁ የወንጀል ቡድኖች እንደፈለጉ የሚያሾሯት አገር ሆናለችና !

የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዴቪድ ካሜሮን በ2011 ቤንጋዚ ላይ ለተሰበሰበ ህዝብ፣ “አንድ አምባገነን አሽቀንጥራችሁ ነጻነትን በመምረጣችሁ፣ ከተማችሁ የዓለምን ስሜት አነቃቅታለች፡፡” ብሎ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ሊቢያ የዓለምን ስሜት በበጎ ጎኑ በማነቃቃት ረገድ የመጀመሪያም፣ የመጨረሻም መሆን የማትችል ከጨዋታው ወጪ የሆነች አገር ሆናለች፡፡

ደግሞ ሌላ ነገር አለ… የአፍሪካ አገሮች ጉዳይ፡፡ “በአገራችን ያለውን የሊቢያ አምባሳደር ጠርተን ተቃውሟችንን ነግረነዋል…” “የእንትን አገር ፕሬዝደንት ደርጊቱን አውገዘዋል፡፡” ይባልልኛል፡፡

እነሱ ከሐገራቸው ዋና ከተሞች በተመቻቸ ቢሮዎቻቸው ተቀምጠው እንዲህ በሚሉበት ጊዜ ግን ዜጎቻችው አየተሸጡ ነው…በግልጽ ጨረታ፤ ሰዎቻችው እንደ ዶሮ ማነቂያ ሽንጥና ሳልገኝ በጭንቅላታቸው ተዘቅዝቀው ታስረው በየማህበራዊ ሚዲያው እየታዩ ነው፡፡ ባሪያ ፈንጋዮቹ ዜጎቻቻውን በዳዴ አስጎንብሰው ጀርባቸው ላይ ቆመው ከሰውም፣ ከእንሳትም በታች ሲያደረጓቸው በምስል እየታዩ ነው፡፡

በነገራችን ላይ እንደው ቢሆን ኖሮ እንበልና እንደዛ በጨረታ የሚሸጡት ነጮች ቢሆኑ ኖሮስ! “አራት መቶ ዲናር!” “አንድ ሺህ ዲናር” እየተባለ የሚጮህባቸው ነጮች ቢሆኑ ኖሮስ ! እነኛ ተዘቅዝቀው የተንጠለጠሉት፣ ጀርባዎቻቸው ላይ የተቆመባቸው ነጮች ቢሆኑ ኖሮስ ! ግልጽ ነው፡፡ ምናለባትም እስካሁን ራሷ ሊቢያ የምትባል አገር አሁን ባለችበት መልኳ መቀጠሏ ያጠራጥር ነበር፡፡

አንድ ሁለት አገር በተናጥል “ጦሬን አዘምታለሁ” ምናምን ሳይሆን የአፍሪካ ሀገራት ተሰብስበው ጉዳዩን የሚኮንን መግለጫ ከማውጣት አልፈው “ሲበቃ በቃ ነው፣” ብለው የራሳቸውን ዜጎች ለማዳን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የሚጀመሩት መቼ ነው! አፍሪካ ውስጥ ባረነት አየተሸጡ ያሉ አፍሪካውያንን ለማዳን የኔቶ አወሮፕላኖች በትሪፖሊ ላይ መገለባበጥ አለባቸው እንዴ! ይሄን፣ ይሄን ስናይ ነው ምንጊዜም “አይ አፍሪካ!” ለማለት የምንገደደው፡፡

በነገራችን ላይ ይህን ጊዜ “እኛስ! እኛስ ጉድ የለብንም እንዴ!” ማለት አለብን፡፡ የእውነትስ እኛ ዘንድስ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ሰዎች በቆዳ ቀለማቸው የተነሳ የሚገባቸውን ሳያገኙ አልቀሩም እንዴ ! ኢፍትሀዊ የፊት ለፊት ሳይሆን የጎንዮሽ መገለል አልደረሳባቸውም እንዴ ! ቁንጅና ከፍርንጅናና ቀይ ከመሆን ጋር እየተያየዘ ጠየም፣ ጠቆር በማለታቸው የተነሳ የተጎዱ የሉም እንዴ !

በአንድ ወቅት ስለ ሲኒማችን ሲወራ የሰማነው ነው፡፡ ለምንድነው ሲኒማ ውስጥ ቆዳቸው ጠቆር ያሉ ሴቶች በብዛት የሌሉት ለሚለው ጥያቄ መልሱ አስደንጋጭም አሳሳቢም ነበር፡፡ ዳይሬክተሮቹ በሲኒማው ቋንቋ ለመጠቀም፣ ካስት ስለማያደርጓቸው ነው ተብሏል፡፡ ቆዳቸው ጠቆር ብሎ የሆነ ስፍራ ከተሰጣቸው እንኳን የሚጫወቱት እኩይ፣ ምቀኛ፣ መተተኛ ገጸ ባህሪይ፣ ምናልባትም ቀይ በሆነችው ቆንጆ የምትቀና የመሳሰለ ነገር ነው፡፡

ማስታወቂያዎቻችንም ለዚሀ ነገር ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እስቲ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ምን ያህል ቆዳቸው ጠቆር ያሉ ማስታወቂያ ሠሪዎች ታያላችሁ ! የሴቶቹማ የባሰበት ነው፡፡ “ማስታወቂያ ሲሠራ በተቻለ መጠን ቆዳዋ ፈገግ ያለች ሴት፣” ምናምን የሚል የውስጥ ሰርኩላር ነገር ያለ ነው የሚመስለው፡፡

ስለዚህም ሰለ ሊብያዎቹ የድንጋይ ዘመን የሰሞኑን ሥራ ሰናይ እግረ መንገድ “የእኛስ ነገረ ሥራ እንዴት ነው ?” ማለት አለብን፡፡

ለነገሩ ሲኒማ ላይ ወንዶቹንም ብትመለከቱ ብዙ ጊዜ የክፋትና የጭካኔ ገጸ ባህሪያትን የሚጫወቱት እንደዛው ክፉና ጨካኝ የሚመስሉ ሰዎች ነው፡፡ ክፉና ጨካኝ የሚመስሉ ሰዎች ሲባል ደግሞ ቆዳቸው ጠቆር ያሉ ሰዎች ማለት ሆኗል፡፡

ወደድንም ጠላንም ተቋማዊ እንኳን ባይሆን ችግር አለብን፡፡

“ስማ ባሪያው፣ ሰሞኑን የት ነው የጠፋኸው?” እንባባላለን፡፡ በእርግጥ “ባሪያው” “ባሪቾ” ምናምን እያለን የምንጠራራው በጥሬው ሲመነዘር የቅርበት፣ የወዳጅነት መግለጫና እንደ ማቆላመጫም ነገር ነው፡፡ ግን መካድ የሌለበት ዋንኛው እየተጠቀሰ የሰውየው የቆዳ ቀለም ነው፡፡

ከተለያዩ ነገሮች ጋር “ዘመን ያለፈባቸው ናቸው” ተብለው ተጥለው ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ በሚባሉ ቃላት እንደተተኩት መጠሪያዎች ሁሉ “ባሪያው” “ባሪቾ” የሚሏቸውን ነገሮች ለምን አሽቀንጥረን እንዳልጣልን መናገሩ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት ለወርክሾፕና ለ‘ቦትልድ ወተር’ የሚመች አጄንዳ ስላልሆነ ይሆን እንዴ…

እግረ መንገድ … ባለፈው ስርአት ጊዜ ከዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ጋር በነበረው ጦርነት፣ የሞቃዲሾ ሬደዮ ጣቢያ የአማርኛው ክፍል በነበረው የፕሮፓጋንዳ ስርጭት … የወቅቱን መሪያችንን ከፍ ዝቅ እያደረገ “ምን የነካው እንጨት” የሚያስመሰላቸው በቆዳ ቀለማቸው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ለማስፈር በማይቻሉ ቃላት፡፡

እግረ መንገድ፣ ባርነትን የመቃወም ነገር ካነሳን እንደ መረጃ … “በሉዊዝቪል ኔግሮ የሚባሉ ሰዎች እንደ ውሾች መሰረታዊ መብቶች እየተነፈጉ ዩኒፎርም ለብሼ ከአገር 10‚000 ማይል ርቄ በቬየትናም ጠያይም ሰዎች ላይ ቦምብ እና ጥይት እንዳዘንብ የሚጠይቁኝ ለምንድነው ?

“በዓለም ዙሪያ ጥቁር ባሪያ ፈንጋይ ነጮች የበላይነት እንዲቀጥል ከአገር 10‚000 ማይል በሚርቅ ቦታ ሌሎች ደሀ ሀገራትን ለመጨረስ አልተባበርም፡፡ እንዲህ አይነት ክፉ ድርጊቶች ሊቆሙ ይገባል፡፡ ይህን አቋም መያዜ በርካታ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሳጣኝ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል፡፡ ግን አንዴ ብየዋለሁ፣ እደግመዋለሁም፡፡

የወገኖቼ እውነተኛ ጠላት ያለው እዚህ ነው፡፡ ለራሳቸው ፍትህ፣ ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉትን በባርነት ለመያዘ መሳሪያ በመሆን ሀይማኖቴን፣ ወገኖቼንና ራሴን አላረክስም፣” ነበር ያለው መሀመድ አሊ ወይም ካስየስ ክሌይ ቬትናም ሄዶ ለመዋጋት አሻፈረኝ ባለ ጊዜ፡፡

አፍሪካ እንዲህ ያሉ ጀግኖች በብዛት ያሰፈልጓታል፡፡

በመጨረሻም በማርቲን ሉተር ኪንግ አባባል እንሰናበት…“አእምሮ በባርነት እስከተያዘ ድረስ፣ አካል መቼም ነጻ መሆን አይችልም፡፡ የአእምሮ ነጻነትና የራስን ክብር ማስጠበቅ ጽኑ ስሜት፣ በአካላዊ ባርነት ረጅም ጽልመት ላይ እጅግ ሀይለኞቹ መሣሪያዎች ናቸው፡፡”

“ሌሎችን ነጻነት የሚከለክሉ እነሱም አይገባቸውም…”

LEAVE A REPLY