የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ነባር መንደሮችን አሁንም አፈርሳለሁ አለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ነባር መንደሮችን አሁንም አፈርሳለሁ አለ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል በገጠመው ሰፊ ተቃውሞ ምክንያት አቁሞት የነበረውን የከተመዋን ጥንታዊ መንደሮችን አሁንም ለማፍረስ መዘጋጀቱን ገለጸ።

በአዲሱ እቅድ ለመፍረስ በስፋት ከተካተቱት ውስጥ ካዛንቺስና ልደታ እንደሆኑ ታውቋል። አስተዳድሩ በከተማዋ በነዋሪዎች በተደጋጋሚ በቀረበ ቅሬታ ምክንያት በጊዜያዊነት ለሁለት ዓመታት ያቋረጠውን የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት በድጋሚ ለመጀመር መዘጋጀቱንና 78 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ አምስት ነባር መንደሮችን እንደሚያፈርስ ሪፖርተር ዘግቧል።

የከተማው አስተዳደር ነባር መንደሮቹን በተያዘው በጀት ዓመት በማፍረስ ለመልሶ ማልማት ሥራዎች እንዲመች ከነዋሪዎች ንክኪ ነፃ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ አምስት ወራት ቢቆጠሩም፣ በቀጣዮቹ ወራት በመሀል አዲስ አበባ የሚገኙትን አምስት ነባር መንደሮችን እንደሚያፈርስ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ፈራሽ የሆኑ መንደሮች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ ቁጥር ሦስት (ከቶታል ማደያ ፊት ለፊት)፣ አራዳ ክፍለ ከተማ አሜሪካ ግቢ ቁጥር ሁለትና ገዳም ሠፈር፣ የካ ክፍለ ከተማ ሾላና መገናኛ፣ ልደታ ክፍለ ከተማ ደግሞ ጌጃ ሠፈር መሆናቸውን ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የመልሶ ማልማት ሂደት ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታዎችን በማንሳታቸው የከተማ አስረዳድሩ “መልሶ ማልማቱን” ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉ ወስኖ ነበር፡፡

አስተዳድሩ መልሶ ለማልማት ያቀደው እቅድ አለመሳካቱንም ተገልጿል። ለዕቅዱ አለመሳካት ምክንያት የሆኑት የቀበሌ ቤት እጥረት፣ ምትክ ኮንዶሚኒየም ቦታ አለማቅረብ፣ በአመራሮችና በሠራተኞች የሚታየው የማስፈጸም አቅም ብቃት ማነስ፣ እንዲሁም የካሳ ግምት አነስተኛ መሆንና የይገባኛል ክርክር ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት በአራት ኪሎና ልደታ አካባቢዎች በርካታ መንደሮች ፈርሰዋል። ተነሸዎችም ተገቢውን ካሳ እንደማያገኙ የሚታወቅ ሲሆን ቦታውንም ለስርዓቱ ባለሟሎች ህጋዊ ባልሆነ መልኩ እንደሚሰጥ በርካታ መረጃዎች በተለያየ ጊዜ እንደወጣ ይታወቃል።

LEAVE A REPLY