በወልዲያ ዪኒቨርሲቲ ሦስት ተማሪዎች በአጋዚ ወታደሮች ተገለዋል።
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፦ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሌላ አካባቢ ተማሪዎች ላይ የተጀመረው ግድያና ጭፍጨፋ ተጠናክሮ ቀጥሏል። አራተኛ ቀኑን የያዘው የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጭፍጨፋ እስካሁን አራት ተማሪዎች እንደሞቱ በቦታው የሚገኙ ተማሪዎች አረጋግጠዋል። ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ተማሪዎች ከዩኒቨርሲው ቅጥር ግቢ ውጭ እንዳይወጡ በአጋዚ ወታደሮች በጥብቅ ጥበቃ ስር ይገኛል። በግቢው ውስጥ በአማራና ኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ ሀይ የሚል አካል እንደሌለ እየተገለጸ ነው። ዛሬ ማምሸውን በአክሱም የኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ግጭት መነሳቱንም ከቦታው የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።
ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ተማሮዎች በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ አማራ ተማሪዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ በመቃወም ዛሬ ጠዋት ለዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጥያቄ ለማቅረብ ሲሞክሩ ችላ በመባላቸው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የመከላከያ ሰራዊት በመግባት ሦስት ተማሪዎችን ገድሏል። በርካታ ተማሪዎችም በጽኑ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎችቬ ተናግረዋል። ማንም ሰው ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ መውጣትም ሆነ መግባት አይችልም። ከትግራይ የመጡ ተማሪዎች በአጋዚ ወታደሮች በአላሙዲ ስታዲየም ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴዎድሮስና ማራኪ ግቢ ከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተካሄደ ሲሆን የአጋዚ ወታደር ወደ ግቢዎቹ ዘልቆ በመግባት ድብደባ ፈጽሟል። በጎንደር ከተማም የተቃውሞ መንፈስ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል። ሱቆች በከፊል ተዘግተዋል፣ የትራንስፖርት አገልግሎትም ቀንሶ ውሏል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ግቢ ውጥረት ነግሶ የዋለ ሲሆን ስርዓቱ ወታደሮች ሲጠበቅ እንደዋለ ተማሪዎች ተናግረዋል። በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የትምህርት ማቆም አድማ እንዲደረግ ተማሪዎች ጥሪ እያቀረቡ ነው።