“ዶ/ር ኣበራ ሞላ ፲፱፻፵ ዓ.ም. በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ሰንዳፋ ከተማ የተወለዱ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በ5 ዓመታቸው ትምህርት ጀምረው በ16 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል። ከ8 ዓመታት ኮሌጅ በኋላ በ25 ዓመታቸው የእንስሳት ሕክምና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀበሉ። እ.ኤ.ኣ. በ1974 ከሠናይት ከተማ ጋር የጋብቻ ስነሥርዓት ከፈጸሙ በኋላ በ1975 በኮሎራዶ እስቴት ዩኒቨርሲቲ ለድሕረ-ዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ወደ ዩናይትድ እስቴትስ ኣመሩ። ኣመጣጣቸውም የኣሜሪካ መንግሥት የመጀመሪያውን የእንስሳት ሓኪሞች ማሰልጠኛ ለኢትዮጵያ መሥራት ስለወሰነ ነበር። በመካከሉ ኢትዮጵያ የኮምዩኒስት ጎራን ስለተቀላቀለች ባልና ሚስቱ ኣሜሪካ በመቆየት ወሰኑ። በኣሁኑ ጊዜ ሦስት ልጆችና ኣራት የልጅ ልጆች ኣሏችው።
ዶክተሩ የኣበረከቷቸው የተለያዩ ቁምነገሮች ስለኣሉ የታወቁባቸውን ሁሉ በተሰጠኝ ጊዜ ማቅረብ ስለማልችል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው። ዶክተሩ የመድንን ማነስ በማስወገድ ከዓለም የእንስሳት ሓኪሞች ኣንዱ ታዋቂ ምሁር ናቸው። የግዕዝ ፊደል በኮምፕዩተርና የእጅ ስልክ ውስጥ በኣለውም መጠቀም እንዲቻል የፈጠሩ ሊቅና የኣክሱም ሓውልት ከሮም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ጣልያንን በማስፈራራት ወሳኙን እርምጃ የወሰዱ ኣርበኛ ናቸው።”
ከእዚህ በላይ የቀረበውን የተናገሩት የኢትዮጵያ ቅርስና ውርስ ማሕበረሰብ በሰሜን ኣሜሪካ ፕሬዚደንት ኣቶ የሺጥላ ኣርኣያ ድርጅቱ ሰባተኛውን ዓመታዊ በዓል ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. ሲልቨር እስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ ሲያከብር ስለዶክተሩ የተናገሩት ነበር።
ዶ/ር ኣበራም ንግግር ሲያኣደርጉ ከጠቀሷቸው መካከል ግዕዝን በኣንድና ሁለት መርገጫዎች መክተብና ፊደሉን በእራሱ ፊደልና ገበታ መጠቀም ስለተቻለ በሦስት መርገጫዎች መክተብ እንደማያስፈልግ፣ የፊደል ሞክሼ እንደሌለው፣ ዓማርኛ ንግግር ውስጥ እንግሊዝኛ መቀላቀል ኣልኣስፈላጊነት፣ የብዙ ቍጥሮችን ኣጠቃቀምና ሰዋስው ማክበር ኣስፈላጊነት ይገኙበታል። ፊደላችን ድምጻዊ ስለሆነ የኦሮምኛውንና የሌሎች ቋንቋዎችንም ድምጾች ሊወክል ስለሚችል ሌላ ዓለም ልንወስደው እንችላለን ብለዋል። ሕብረተሰቡ ግዕዝኤዲትን ገዝቶ በተለያዩ ቋንቋዎቻችን መጻፍ ከኣልጀመረ ትውልዱ ወርቃማ ጊዜውን እየኣባከነና ሳያስፈልግ ግዕዝን እያዳከመ መሆኑን ኣስጠንቅቀዋል። ሶፍትዌር የሚ¿ገዛ እንጂ የሚሰረቅ ኣይደለም ብለዋል።
ከእዚያም በዶ/ር ሞገስ ወልደማርያም ኣስተዋዋቂነት “የኢትዮጵያ የመማር ባሕል ዕድሎቹና ችግሮቹ” በሚል ርዕስ ንግግርና ውይይት በዶ/ር ኣክሊሉ ሃብቴ፣ ፕሮፌሰር ኣቻምየለህ ደበላ፣ ዶ/ር ኣበባ ፈቃደ እና ኣቶ ቴዎድሮስ ኣበበ ቀርበው ዝግጅቱ በጥያቄና መልስ ተጠናቋል።
በዕለቱ ለተጋባዡ የቀረበው ጽሑፍ ውስጥ ስለ ዶክተሩ የተጻፈው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ትርጕም እንደሚከተለው ነበር።
“ዶ/ር ኣበራ የግዕዝ ፊደል ኣባት የሚል ስም የተሰጣቸው ኣዳዲስ ነገሮችን የፈጠሩ ሳይንቲስት ናቸው። ከ፳፱ ዓመታት በፊት ግዕዝ በኮምፕዩተር እንዲከተብ ሲፈጥሩ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ የተወለዱትን የኢንጅነር ኣያና ብሩን የዓማርኛ የጽሕፈት መኪና ፈጠራ በምሳሌነት ተጠቅመዋል። ቢሆንም በላቲን ቀለሞች ምትክ የተሠሩት ቍርጥራጮች ትክክለኛ የዓማርኛ ፊደላት ስለኣልሆኑና መርገጫዎቹ እንደፊደላቱ ብዙ ስለኣልነበሩ ለግዕዝ ፊደል የሚያስፈልጉትን ዶክተሩ ፈጥረዋል። ኮምፕዩተራይዝ የኣደረጉት ፊደላቸውም የዩኒኮድ ፊደል ሆኗል።
ከእዚሁ ጋር የተያያዘ በኮምፕዩተር ኣዳዲስ ኣከታተቦችን፣ የፊደል ኣመዳደቦችና ገበታዎች ፈጥረዋል። ይህ ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ በፊደላቸው በኮምፕዩተር እንዲጠቀሙ ኣስችሏቸዋል። እንዲህም ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የኣዕምሮኣዊ ፈጠራ ጥበቃ ሕግ (ፓተንት) በጊዜው ስለኣልነበረ የፈጠራቸውን መብት ኢትዮጵያ ውስጥ ማስጠበቅ ኣልቻሉም። ዋናው የዶክተሩ ዓላማም መብቱን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመጋራት ሁሉም ኣዕምሮኣዊ ፈጠራዎችን ማክበር እንዲጀምር ለማበረታታት ነበር።
በቅርቡም እየኣንድኣንዱ የግዕዝ ቀለም ከሁለት መርገጫዎች በኣልበለጡ ለመክተብ ለኣስቻሉት የተሻሻሉ ዘዴዎቻቸው ዩናይትድ እስቴትስና ኢትዮጵያ ማመልከቻዎች ኣስገብተዋል። በዘዴዎቻችውም ኢትዮጵያውያን በነፃ በዓማርኛ ኢንተርኔት ውስጥ እንዲጽፉና እንዲፈልጉ ኣበርክተዋል። ዶ/ር ኣበራ በሰለጠኑብት የእንስሳት ሕክምንናና እንዲሁም ግዕዝን ኮምፕዩተራይዝ ሲያደርጉ የኣእምሮኣዊ የፈጠራ ባለቤትነት ተሰጥተዋቸዋል። ሲልቨር እስፕሪንግ ሜሪላንድ ሰባተኛውን ዓመታዊ በዓል ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. የኣከበረው የኢትዮጵያ ቅርስና ውርስ ማሕበረሰብ በሰሜን ኣሜሪካ ዶክተሩን የበዓሉ የክብር እንግዳ ኣድርጓል።”
ለዶክተሩ የተሰጠው የዕውቅና ሽልማት የዓማርኛ ትርጕም እንደሚከተለው ነው።
“የኢትዮጵያ ቅርስና ውርስ ማሕበረሰብ በሰሜን ኣሜሪካ ለዶክተር ኣበራ ሞላ ዕውቅና በመስጠት ይኸንን ትልቅ ሽልማት የሚያበረክትላቸው በሠሩት በጣም ጠቃሚ ሥራ የግዕዝ የእስክሪንና የማተሚያ ፈደላት ስለፈጠሩ ነው። ይህ ፈጠራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቃላት ማተሚያ በመሆኑ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ቋንቋ በሆነው ዓማርኛ ሕዝቡ በሚገባ በኮምፕዩተርና ተመሳሳይ መሣሪያዎች እንዲጠቀም ሆኗል። በተጨማሪም በሳይንቲስትነት፣ ተመራማሪነትና ሥራ ፈጣሪነት ለኣበረከቱት ዕውቅና የምንሰጠው በታላቅ ኩራት ነው።
የኣበረከትነውም ዕውቅና በማሕበረሰቡ የዲሬክተሮች ቦርድና በሁሉም ኢትዮጵያውያን ስም ወሰን ከሌለው ምስጋና፣ ፍቅርና ኣድናቆት ጋር ነው።
በቦርዱ ዲሬክተሮች ውክልና ስም የሕብረተሰቡ ፕሬዚደንት፣ የሺጥላ ኣርኣያ።” ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. November 19, 2017.
ዶ/ር ኣበራ ሞላ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሠናይት ከተማ ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ጀምሮ የኮሎራዶ እስቴት ነዋሪ ናቸው። የኢትዮጵያ ኮምፕዩተሮችና ሶፍትዌር ኩባንያ ባለቤቶችም ናቸው።
የዶክተሩ ኢሜይል ኣድራሻ geezedit@aol.com ነው።