በጥንቃቄ የተመረጡትን ለቅመን ስንመረምራቸው የሚሰጡን ምስል የህወሀት ፍጻሜ ከሚጠበቀው በላይ ፈጣንና ቅርብ መሆኑን ነው። በቀናት የሚጠብቅ ሳይሆን በሰዓታት የሚለዋወጥ የፖለቲካ ንፋስ ከወዲህ ወዲያ እያጎነን ነው። ህወሀት ጥርሱ ወላልቆ ማየት የሚናፍቀው ኢትዮጵያዊ መሽቶ በነጋ ቁጥር አዲስ ነገር እየሰማ ነው።
በፓርላማው የኦህዴድና ብአዴን አባላት አቶ ሃይለማርያም ለጥያቄዎቻችን መልስ ካልሰጡን መደበኛ ስብሰባ አንሳተፍም ማለታቸው ዛሬ ተሰምቷል። ይህ ቀላል ለውጥ አይደለም። ቤቱ ታሪክ ሊሰራበት ከሆነ እሰየው ነው። ባለፈው የህወሀት ጄነራሎች መጦሪያ የሆነውን ሜቴክን የተመለከተ የፓርላማ ስብሰባ ላይ አባላቱ በድፍረት የተናገሩት ያልተጠበቀ ነበር። ”አሁንስ የፓርላማ አባል መሆን አሳፈረን” ነበር ያሉት። ይሄው አሁን ደግሞ በሰፊው ደገሙት። ያለፈው ሳምንት ሁለት የፓርላማ ስብሰባዎች ያልተካሄዱት በአባላቱ አድማ መሆኑን ሰማን። ጥሩ ነው። ህወሀት በቁሙ ተስካሩን ሊበላ መድረሱን የሚያሳይ ነው።
በሰራዊቱ ውስጥ ከትግራይ ተወላጆች በቀር ሌላው አባል ከማጉረምረም እየተሻገረ ነው። በተለይ የታችኛው የመከላከያ ክፍል የልብ ትርታው ወደ ሌላ ቦታ እየመታ መሆኑን በስፋት እየተነገረ ነው። ለህወሀት የሞት ጥሪ ያህል የሚያስፈራው ምልክት ነው። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ጭፍግግ ያለ የፖለቲካ ድባብ መጪው ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የህወሀት ጡንቻ መሟሸሹ የአደባባይ ዕውነት ሆኗል። የመንግስት መዋቅር የፈረሰባቸው አከባቢዎች እንዳሉ፡ ህብረተሰቡ የመንግስትን ሹሞች እየሻረ የራሱን እየሰየመ መሆኑን የሚያሳይ የፌደራል ፖሊስ አንድ ሪፖርት ሰሞኑን ወጥቷል። በቅርቡ የህወሀትን አቅምና አቋም ያጋለጠው የብሄራዊ ደህንነት ዕቅድም ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ ታውቋል። አንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ተናገሩ እንደተባለው የህወሀት ስርዓት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። በአስቸኳይ አዋጅ ማስቆም ያልቻለው፡ በብሄራዊ ደህንነት ዕቅድ ያልተገታው የህዝብ ማዕበል ክፉኛ እየናጠው ነው ይላሉ አመራሩ።
ህወሀት ለትግራይ ህዝብ ከወዲሁ እህል በገፍ እየሸመተ ነው። ከአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከገበሬው በርካሽ ዋጋ እህል ገዝቶ ወደ ትግራይ እያጓጓዘ መሆኑ ተረጋግጧል። በርካታ ግዙፍ ጎተራዎች ተዘጋጅተው እህል እየተጠቀጠቀባቸው ሲሆን ምናልባት አንዳች ነገር ቢመጣ ለክፉ ጊዜ የሚሆን ቀለብ ከወዲሁ እንዲጠራቀም በህወሀት አመራር ውሳኔ ላይ መደረሱ ይነገራል። ይህ የሚያመለክተው ህወሀት የመቃብር ጉዞውን መጀመሩን ነው።
የኢህአዴግ ስብሰባ
የህውሀት የባህርማዶ ልሳን የሆነው አይጋ ፎረም እምባ ያራጨ ስብሰባ እየተካሄደ ነው ይላል። ስጋት ያጠላበት፡ የመፈራረስ ደመና የተጋረጠበት ኢህአዴግ አንዳንድ መሪዎቹ በጸጸት ተዘፍቀው እምባቸውን በስብሰባው መደረክ ማፍሰሳቸውን ተከትሎ መረጋጋት መስፈኑን ከመሸ ነግሮናል። በእርግጥ ስብሰባው ገና ነው። ሳይጠናቀቅ መግለጫ ወጥቷል። ህዝብ ውስጥ እየተመላለሰ ያለው ነገር ያላማራቸው ህወሀቶች ”የማረጋጊያ” መግለጫ በመስጠት ፍጥጫቸውን ቀጥለዋል። መግለጫው አዲስ ነገር የለውም። ስብሰባው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቢሆንም ባልተለመደ መልኩ የህወሀት የነፍስ አድን ሃይሎች ተጠራርገው ገብተዋል። የደህንነት ሃላፊዎች በሰልፍ የታደሙበት፡ የህወሀት የጡት አባቶች ወንበር ተሰጥቷቸው የተሳተፉበት፡ የማይመለከተውም የሚመለከተውም በእኩል ድምጽ የተገኙበት ስብሰባ መቼ እንደተጀመረ እንጂ መቼ እንደሚጠናቀቅ ሰብሳቢውም ተሰብሳቢውም የሚያውቁት አይደለም። እንዴት እንደሚጠናቀቅም ከወዲሁ መገመት ይከብዳል።
የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቅ ውሳኔ የሚተላለፍበት የተለየ ስብሰባ ይሆናል ማለታቸው ከመነሻው ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል። በኋላም እየሾለኩ የሚወጡት መረጃዎች ስብሰባው አንዳች ነገር ሊያሳየን ይችል ይሆን ብለን እንድንጠብቅ ያደረገን ይመስላል። የስርዓቱ ደጋፊዎች ”የኢህአዴግን ጡንቻ የሚያፈረጥም፡ የጸረ ሰላም ሃይሎችን ምኞት የሚያከሽፍ” ስብሰባ ይሆናል ይሉታል። በተቃራኒው ያለው ሃይል ደግሞ ”የህወሀት ጥርስ የሚወላልቅበት፡ የውድቀቱን መጨረሻ የሚጀምርበት” በሚል ይገልጹታል።
ያም ሆነ ይህ ህወሀት ከኦህዴድና በተወሰነ መልኩ ከብአዴን ጋር ተፋጧል። ”ከኦነግ በላይ ህወሀት” ለኦሮሞ ህዝብ ቅርብ ነው በሚለው አወዛጋቢ ንግግሩ የሚታወቀው የህወሀት የበኩር ልጅ አቶ አባዱላ ገመዳ ያፍረጠረጠው ነገር ለህወሀት ጭንቀት፡ ለስብሰባ ውጥረት፡ ለተመልካቾች ትኩረት ሰጥቷል። የትግራይ የበላይነት አለ የሚለው የአባዱላ ያልተጠበቀ ድፍረት የህወሀትን አቅም መዳከም፡ ማርጀት፡ መገርጀፍ፡ መጃጀት ብሎም ውድቀት ያመላክታል የሚል እምነት አለኝ።
ይህ የበላይነት የኢትዮጵያ ቁልፉ አደጋ ነው። የችግሮቹ ሁሉ እናት የሆነ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን አዘቅት ውስጥ የከተታት፡ የሀገሮች ጭራ ያደረጋት፡ ልጆቿን ከሰው በታች አድርጎ ያዋረዳቸው ዋናው ካንሰር የትግራይ የበላይነት ስር ሰዶ መዝለቁ ነው። ያን ጉዳይ መንካት ለህወሀት የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው። ያን በድፈረት ማንሳት ለህወሀት ህልውናውን መፈታተን ነው። ጦር ሰብቆ ከሚመጣበት ግዙፍ ጠላት በእኩል ደረጃ የሚያጠፋው የ’በላይነት’ ላይ የቆመውን መንግስታዊ መዋቅሩን የሚጋፈጥና የሚገዳደር ሃይል ከውስጡ ሲነሳ ነው። አባዱላ ያንን ደፈረው። ኦህዴድ ይህን አጀንዳ ሊጋፈጠው ቆረጦ ተነሳ። ብአዴን በመካከለኛና በታች አመራሩ ሲንተከተክ የነበረውን ጉዳይ ጊዜ ጠብቆ አፈነዳው። ህወሀት ተርበተበተች።
ሜ/ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ(ኢንሳ)
የትግራይ የበላይነት የህወሀት ደምና አጥንት ነው። የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መረብ ኢንሳ ሃላፊ ሰሞኑን የሰጠው ቃለመጠይቅ በአጭሩ ሲቀመጥ ‘የትግራይን የበላይነት ያልተቀበለች ኢትዮጵያ ገደል ትግባ’ ነው። ምርጥ ምርጡን ለህጻናት የሚለውን መፈክር ገልብጦ ‘ለትግራይ’ የሚል አጀንዳን በአደባባይ ይዞ የተነሳው ይህ ሰው እነጌታቸው ረዳ ነጋ ጠባ የሚያላዝኑትን ”የትግራይ የበላይነት የለም” ዲስኩር ውሃ ቸልሶበታል። ሰውዬው የጆርጅ ኦርዌልን All animals are equal, but some animals are more equal than others ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው አንዳንዶቹ ግን ከሌላው ይበልጣሉ የሚለውን ተረት ተረት ኮፒ አድርጎ በ21ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ምድር ላይ እውን ይሆን ዘንድ ምኞቱን የገለጸበት ቃለመጠይቅ አስገራሚ ነው። በሁሉም ነገሮች እንበልጣለን፡ ልንበልጥም ይገባል የሚለው የድፈረት ንግግር ድንቁርናውን ያሳያል ብለን የምንተወው አይደለም። የህወሀት መስመር ነው። የመኖር ወይም የመጥፋት ጉዳይ ነው።
በ80ዓመታቸው ያለፉት አንጋፋው የታሪክ ጸሃፊ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ አንድ ወቅት ላይ መለስ ዜናዊ ያነጋገራቸውን ከመሞታቸው በፊት ተንፍሰውት ነበር። መለስ ዜናዊ እሳቸውን ጠርቶ ”ትግራይን እንደእስራዔል ለማድረግ ህልም እንዳለው፡ በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ ጡንቻ በማፈርጠም የአፍሪካ እስራዔል ለመሆን እንደሚቻል፡ ይህን ለማድረግ የትግራይ ምሁራንን ድጋፍ እንደሚፈልግ’ አጫወታቸው። ኢትዮጵያዊ ሆነው ተወልደው ኢትዮጵያዊ ሆነው የሞቱት የትግራዩ ተወላጅ ደጃዝማች ዘውዴ የሰሙትን ነገር ማመን እንዳቃታቸው ለወዳጆቻቸው ነግረዋል። ፍቃደኛ አለመሆናቸውን፡ ሀሳቡ አደገኛ መሆኑን ገልጸውለት እንደነበረ ይነገራል። መለስ የኢትዮጵያ መሪ ሆኖ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ተቀምጦ፡ በአስተሳሰብ ከትግራይ ድንበር መሻገር ሳይችል፡ ዘመኑን ጨርሶ ኢትዮጵያዊ መሆን አቅቶት ወይም መሆን ሳይፈልግ እስከወዲያኛው ያሸለበ ሰው ነው። የሰሞኑ የኢንሳው ሰውዬ ቃለመጠይቅ የዚሁ የመለስ ዜናዊ ህልም ጭማቂ ነው።
የኢንሳውን ሰውዬ አለማድነቅ ይከብዳል። እነጌታቸው የሚሽኮረመሙበትን ጉዳይ አደባባይ አስጥቶታል። ከህወሀት የተለዩና ‘ተቃዋሚ’ ታፔላ ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ የቀድሞ ህወሀቶች ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩለትን አጀንዳ አፈር ከድሜ አብልቶታል። በአስተሳሰብ፡ በጽናት፡ በትጋት፡ በስኬታማነት፡ በሁሉም ነገሮች ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንቀድማለን፡ ያለበት ቃለመጥይቁ ከእንግዲህ የትግራይ የበላይነት የለም እያሉ ለሚያደነቁሩ ሰዎች አፍ የሚያዘጋ መሆን አለበት። በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ዋጋችን ከፍ እንዲል በሚል የጨዋ አነጋገር የበላይነት ፍላጎቱን ያራገበው የኢንሳው ሃላፊ በኢኮኖሚው፡ በቴክኖሎጂው፡ በሁሉ መስክ ቀዳሚነታችንን አስጠብቀን መዝለቅ የህልውና ጉዳያችን ነው ሲልም ደምድሟል። ስዩም መስፍን የጎንደሩን አመጽ ተከትሎ የበላይነታቸውን የሚፈታተን ነገር ሲመጣ፡ ”እንደዛማ ከሆነ እንተላለቃታለን” ማለቱንም አንዘንጋ።
እንግዲህ የሰሞንኛውን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ትኩረት እንድሰጠው ያደረገኝ ይሄው የህወሀት ህልውናን የሚፈታተን ፍጥጫ መፈጠሩ ነው። በእርግጥም በዚህ አጀንዳ ላይ ኦህዴድና ብአዴን ግንባር ፈጥረዋል። የበላይነቱ አንገሽግሿቸዋል። ሁሌ ተላላኪ፡ ሁሌም አሽከር፡
ሁሌም ታዛዥ መሆን ሰልችቷቸዋል። ህወሀት መቀሌ ላይ ህንፍሽፍሹን አጠናቆ በጣም አደገኛውን አመራር ሰይሞ ጓዙን ጠቅልሎ አዲስ አበባ ሲገባ የጠበቀው የትላንቱ ኦህዴድ አይደለም። የቀድሞው ብአዴንም አይደለም። ዘግይተወም ቢሆን የነቁ፡ የህዝባቸው ብሶት እረፍት የነሳቸው፡ በመጨረሻው ሰዓትም ቢሆን ስማቸውን ከጥቁር መዝገብ ላይ እንዲፋቅ የወሰኑ የኦህዴድና የብአዴን አመራሮች የህወሀትን የዘረኘነት ሉጋም ሊበጥሱ መሆኑን ምልክት አሳይተዋል።
አሰላለፍ
አሁን ነገሮች ግልጽ እየሆኑ ነው። አሰላለፉ ታውቋል። ማን ከማን ጎን እንደቆመ ፍንትው እያለ ነው። ተወደደም ተጠላም አንድ መስመር ደምቆ እየወጣ ይመስላል። የኢትዮጵያን የወቅቱን ፖለቲካ በቅጡ ለሚረዳ ሰው እንደውሃ ኩልል ብሎ የሚታየው ነገር ተፈጥሯል። ብዥታው ጠርቷል። የሰሜን አሜሪካው የተጋሩ መግለጫን ብቻ ብንወስድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ደርቢ ይገለጽልናል። ተጋሩዎች አዛኝ ቅቤ አንጓች የሆነውን፡ ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት የቀረውን የሀዘን መግለጫ በማስፈራሪያ አጅበው ሲያወጡ መልዕክቱ ግልጽ ነበር። ሰልፋቸው ከማን እንደሆነ ያሳዩበት ነበር። ሺዎች ሲገደሉ፡ መቶ ሺዎች ሲፈናቀሉ፡ ከአንድ ቤት አምስት የቤተሰብ አባላት በአግዚ ጥይት ሲደፉ፡ ከጋምቤላ እስከ ጎዴ፡ ከጂንካ እስከ ወልቃይት የኢትዮጵያ ልጆች ከትግራይ በበቀሉ እንጉዳዮች በገፍ ሲጨፈጨፉ አንድ ዘለላ እንባ ማፍሰስ ያልቻሉት ተጋሩዎች በእነዚሁ እንጉዳዮች አቀናባሪነት ለተፈጸመ ግድያ ለቅሶ መቀመጣቸው በእርግጥም መልዕክቱ ግልጽ ነው። ከሰሞንኛው አሳዛኝ ዕልቂት በብዙ እጥፍ የሚልቅ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ መፈጸሙን የዘነጋን ከመሰላቸው ተሳስተዋል።
እናም አሰላለፉ ለይቶለታል። ደርቢው ታውቋል። ህወሀትና ሶህዴፓ ጋብቻ ፈጽመዋል። ለጋብቻቸው ድምቀትም የኢትዮጵያን ህዝብ ጭዳ ሊያደርግ በሚችል የጥፋት መስመር ላይ እየጋለቡ ነው። ህወሀቶች ሁሌም እንደሚያስፈራሩት የበላይ ሆነው ካልቀጠሉ ኢትዮጵያን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። ለዚህ የጥፋት ተልዕኳቸው ደግሞ አብዲ መሀመድ የሚባል የመንደር ካድሬ አሰልጥነው በ6ሚሊየን የሶማሌ ኢትዮጵያውያን አናት ላይ አስቀምጠውታል። ዕውቀት የነጠፈበት፡ ድንቁርና የነገሰበት፡ ጎረምሳው አብዲ መሀመድም ከህወሀት ጄነራሎች በሚሰጠው ትዕዛዝ እየፈጸመ ያለው ግዙፍ አደጋ የኢትዮጵያ የወቅቱ ብርቱ ፈተና፡ የመጪው ጊዜ ስጋት ሆኗል።
የለማ መገርሳ መንገድ
ይህን ሰው አለመከተል ይቻላል። አለመደገፍም መብት ነው። አንድ ሀቅ ግን ፈጦ እየታየ ነው። የህወሀትን የዘረኝነት እብጠት ማስተንፈስ የቻለ ሰው ነው። የበላይነት ግልቢያውን በድፍረት የተጋፈጠ መሪ ነው። የዚህ ሰው መንገድ የሚጎረብጥ አይደለም። ከኦሮሞ ልብ ባሽገር ጥቂት የማይባሉ የሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ቀልብ የገዛ፡ ጆሮ የተሰጠው ለመሆኑ በማህበራዊ መድረኮች የሚደረጉትን ውይይቶች በመታዘብ መግለጽ ይቻላል።
ህውሀት ለማን ለማንበርከክ ወጥመዶችን ከመዘርጋት ወደኋላ አላለም። በሶማሌ ተወላጆች ላይ ሰሞኑን የተፈጸመው ዕልቂት ለለማ ከተዘጋጁት ወጥመዶች አንዱ ነው። የኦሮሚያ ክልል ልዩ መብት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚለው አጀንዳም ሌላው ካርድ ነው። ህወሀት ሁለቱንም ዘርግቷቸዋል። የአዲስ አበባን ጉዳይ ዳግም በመቀስቀስ ለማ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የተሰጠውን ክብር ለመግፈፍና ወደ ቀድሞው የዘር ፍጥጫ ለመዝፈቅ ታጥቆ ተነስቷል። በሶማሌዎች ግድያም የህውሀት ጣት ለማ ላይ መቀሰሩ ያለምክንያት አይደለም። ሌሎች ወጥመዶችም ይጠበቃሉ። ለማ በጀመረው መንገድ ገፍቶ ከቀጠለ የህወሀት ወጥመድ ከየአቅጣጫው መዘርጋታቸው አይቀርም። እናም ከለማ ጎን መቆም የኦሮሞም በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ህዝብ የወቅቱ ሃላፊነት ነው።
የገዱ አንዳርጋቸው መንታ መንገድ
ገዱ መንታ መንገድ ላይ ቆሟል። በዚህ በኩል የህወሀት የተሳለ ጥርስ ያፏጭበታል። በዚኛው ደግሞ የህዝብ አብዮት ይለበልበዋል። በእርግጥ ገዱ አንዳርጋቸው ማኖ ነክቷል። በጎንደሩ ህዝባዊ ዕምቢተኝነት የያዘው አቋምና ከህዝብም ያገኘው ድጋፍ ከግጨው ታሪካዊ ስህተቱ በኋላ አብሮት የለም። ገዱ ከሁለት አንድ ያጣ ሆኗል። ህወሀት በገዱ ላይ በለስ ቀንቶታል። ከህዝብ ልብ ውስጥ እንዲወጣ የቀመረው ዘዴ በመጠኑም ተሳክቶለታል። ነገር ግን ገዱ ዕድል አለው። ከእነለማ ቡድን ጋር ያሳመረውን አሰላለፉን ከገፋበት ያጣውን የህዝብ ልብ መልሶ የማያገኝበት ምንም ምክንያት የለም። በተለይም በመካከለኛውና ታችኛውም የብአዴን አመራሮች የሚንቀለቀለው የለውጥ እሳት ለገዱ ጋሻና መከታ መሆኑ ይታመናል። እናም ገዱ ሀሞቱ እንዳይፈስ መታገል አለበት። የእነለማ መንገድ የሰመረ እንዲሆን የእነገዱ ጠንከር፡ ቆፍጠን ማለት ወሳኝነት አለው።
ህወሀቶች በፍርሃት ቢናጡም ማድባታቸውን አልተዉትም። ቅዝምዝሟን ከተሻገሯት፡ ይህቺን የምጥና የጭንቀት ጊዜ ካለፏት በመጀመሪያ ሰልቅጠው የሚበሉት የለማንና የገዱን ሃይል ነው። ባለፈው እንዳልኩትም ይህ ስብሰባ ለኦህዴድና ብአዴን የሚያስገኘው አንዳች ጥቅም የለውም። ይልቅስ የተነቃነቀውን የህወሀት ዙፋን ለማረጋጋት፡ የትግራይን የበላይነት አረጋግጦ ለማስቀጠል ነው። እናም ስብሰባውን ረግጠው መውጣት ይኖርባቸዋል። ከዚያም ተሻግረው ፓርላማውን ማፍረስ ይጠበቅባቸዋል። ከዚያ በመለስ የሚወሰድ እርምጃ ትርጉም የለውም። ህወሀትን አፈራርሶ፡ ከጥልቅ ጉድጓድ ከመቅበር ያነሰ እርምጃ ጥገናዊ እንጂ ዘላቂ ለውጥ አያመጣም። የኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ቋንቋ ያስተላለፈው መልዕክትም ይሄው ነው።