/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ፍሬው ተገኝን ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጠ። ዶክተር ፍሬው ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ካመለከቱ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር ተወዳድረው የድምጽ ብላጫ በማግኘታቸው መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አሳውቋል።
በዘመነ ኢህአዴግ ዩኒቨርሲቲዎች በፖለቲካ ሹመኞች ሲመሩ በመቆየታቸው የቁጡሩን ያህል ጥራት ማምጣት ላለመቻላቸው ሁነኛ ምክንያት ሆኖ እንደቆየ ተጠቁሟል። ዩኒቨርሲዎች አሁንም ጥናትና ምርምር ባደረጉ ባለሙያዎች በውድድር ወደ መሪነት መምጣት የተሻለ የትምህርት ጥራት ሊያስገኝ ስለሚችል ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል።
ስርዓቱ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ሽንፈት በሗላ በተለየ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲዎችን የመማር ማስተማር ነጻነት በመንፈግ ከመምህር ከቅጥር ጀምሮ የዲፓርትመንት ሀላፊዎችን እንዲሁም ፕሬዚዳንቶችን በፖለቲካ ተመዝነው በመሾማቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን ትውልዱን የማብቃትና ማህበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይችሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ባለው ክረምት አምባሳደር ሆነው የተሾሙትን ዶክተር ፀጋየ አድማሱን የሚተካ ፕሬዚዳንት አወዳድሮ ለመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣቱ ተገልጿል።።