/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ የ“ሽብር” ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸውን በቀጠሮ በመከታተል ላይ የነበሩት ዶክተር መረራ ጉዲና ዛሬ መፈታታቸው ታወቀ።
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ፊርማ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የተጻፈው የማስፈቻ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው የዶ/ር መረራ ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑን አመልክቷል።
አቶ ጌታቸው አምባየ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/3/ሠ ጠቅሰው ዶክተር መረራን ጨምሮ ሌሎች ተፈቱ የተባሉት 115 እስረኞች የሚፈቱት “ለህዝብና ለመንግሥት ጥቅም ሲባል ክሱ እንዲነሳላቸው የተወሰነ መሆኑን አስታውቃለሁ።” በማለት ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከዶክተር መረራ ጋር ተፈቱ የታባሉት እስረኞች እስካሁን በስም ለይቶ ማወቅ አልተቻለም።ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ወር ለ“ሀገራዊ መግባባትና የዲሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት” በማሰብ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ለመፍታት መወሰኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ዶክተር መረራ ጉዲና በአውሮፓ ህብረት ጋባዥነት በብራስልስ ስብሰባ ተካፍለው ሲመለሱ ህዳር 2009ዓ.ም ጀምሮ በእስር ቤት ማሳለፋቸው ይታወቃል።