ለፍርድ ተቀጥረው የነበሩት የኦፌኮ አመራሮች ፍርድ ቤት አልቀረቡም /በጌታቸው ሺፈራው/

ለፍርድ ተቀጥረው የነበሩት የኦፌኮ አመራሮች ፍርድ ቤት አልቀረቡም /በጌታቸው ሺፈራው/

~ በመዝገቡ ከተከሰሱት መካከል 9ኙ ትናንት ተፈትተዋል

ጥር 3/2010 ዓም በመከላከያ ምስክርነት የጠሯቸው ባለስልጣናት እንዳይመሰክሩላቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ውድቅ ከተደረገባቸው በኋላ ለፍርድ የተቀጠሩት የኦፌኮ አመራሮች ዛሬ ጥር 10/2010 ዓም በቀጠሯቸው ፍርድ ቤት አልቀረቡም። ጥር 3/2010 ለዛሬ ለፍርድ የተቀጠሩት ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በመዝገቡ የተከሰሱት ተከሳሾች በዛሬው ቀጠሮ ያልቀረቡ ሲሆን የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ለምን እንዳላቀረቡ ሲጠየቁ ቀጠሮውን በደንብ ስላልሰሙ ዛሬ ማቅረብ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ለመስጠት እና ማረሚያ ቤቱ ተከሳሾቹን ለምን እንዳላቀረበ መልስ እንዲሰጥ ለጥር 28/2010 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ መከላከያ አሰምተው ያልጨረሱ ተከሳሾች እንዳሉ በመግለፅ ፍርድ ቤቱ ለፍርድ የሰጠው ቀጠሮ ላይ ጥያቄ አቅርበዋል። መከላከያ ያልጨረሱትን ተከሳሾች ስም ዝርዝርም አቀርባለሁ ብለዋል።

በሌላ በኩል ከተከሳሾቹ መካከል 5ኛ ተከሳሽ አብደታ ነገሳ፣ 6ኛ ተከሳሽ ገላና ነገራ፣15ኛ ተከሳሽ ዩሱፍ አለማየሁ፣ 16ኛ ተከሳሽ ሂካ ተክሉ፣ 17ኛ ተከሳሽ ገመቹ ሻንቆ፣ 18ኛ ተከሳሽ መገርሳ አስፋው፣ 19ኛ ተከሳሽ ለሚ ኤዲቶ፣ 20ኛ ተከሳሽ አብዲ ታምራት እና 21ኛ ተከሳሽ አብዲሳ ኩምሳ በትናንትናው ዕለት መፈታታቸውን ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል።

በመዝገቡ 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብዲሳ፣ 9ኛ ተከሳሽ ፍራኦል

ቶላ፣ 10ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ደረጄ፣ 13ኛ ተከሳሽ አሸብር ደሳለኝና 22ኛ ተከሳሽ ሔልካኖ ኮንጤራ በብይን በነፃ መሰናበታቸው ይታወሳል። በመሆኑም በመዝገቡ ጉዳያቸው የሚቀጥለው 1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖ፣ 2ኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ፣ 3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ፣ 4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ፣ 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ፣ 12ኛ ተከሳሽ ተስፋየ ሊበን እና 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ ናቸው።

LEAVE A REPLY