የጸጥታ ኃይሎች በወልድያ ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት ግድያ በምንም ዓይነቱ መመዘኛ ከውግዘት የሚያመልጥ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ‹ጸረ መንግሥት ዝማሬ ያሰሙ ነበር›፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹ድንጋይ ይወረውሩ ነበር› የሚሉት ምክንያቶች የጸጥታ ኃይሎች በሕዝብ ላይ ጥይት እንዲተኩሱ የሚያበቁ ሕጋዊና ሞራላዊ ምክንያቶች አይደሉም፡፡ ማንኛውም ጸጥታን የማስከበር ሥራ መከናወን ያለበት ሰላምን በሚያሰፍን፣ የሰዎችን ሕይወትና ንብረት በሚጠብቅና ተመጣጣኝ የሆነ ኃይልን ለመጠቀም በሚፈቅድ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡
በኃይል የሚፈታ ችግር እንደሌለ መንግሥት ራሱ ከማናችንም በላይ የሚያውቀው ነገር ነው፡፡ የዛሬውን መንግሥት የመሠረተው ኢሕአዴግ ወደ በረሓ እንዲገባ ያደረገው ደርግ ችግሮችን ሁሉ በውይይት ሳይሆን በኃይልና በኃይል ብቻ ለመፍታት በመፈለጉ መሆኑን በየግንቦት ሃያ በዓሉ ስንሰማው ኖረናል፡፡ ለሰው የሚጠላውን ኃጢአት ራሱ ከመሥራት በላይ ውድቀት የለም፡፡ በዓሉ የአንድ ቀን በዓል ነው፡፡ ቢታገሡት ያልፍ ነበር፡፡ ሌላ ችግር ይከሰታል ተብሎ ከተጠረጠረና መረጃ ከተሰበሰበ እንኳን አያሌ የችግር መፍቻ አማራጮች ነበሩ፡፡ ‹የጸጥታ ችግርም› ‹የጸጥታ ኃይሎች›ም እኛ ሀገር ብቻ አይደለም ያሉት፡፡ ባለ ሥልጣኖቻችንም ለልምድ ልውውጥ በየሀገሩ ሲሄዱ ነው የሚኖሩት፡፡ ምነው ታድያ የተሻለ አማራጭ መማር አቃታቸው?
በዓሉ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ ዐቅመ ደካሞች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ የሚታደሙበት በዓል ነው፡፡ እንዴት ነው ወደነዚህ ሁሉ የሚተኮሰው? እንዴትስ ነው ‹ችግር ፈጠሩ› የተባሉትን አካላት ከሌሎች ለመለየት የሚቻለው? ጥይቱስ እንዴት ነው ከ9 ዓመት ሕጻን የሚጀምረው? እንዲህ ባሉ ዓመታዊ በዓላት ቀን የሚፈጠር ግፍ ከልጅ ልጅ ለመታወስና የበቀልን ስሜት ለመቀስቀስ ቀላል መሆኑን እንዴት ለማሰብ ከበደን? ከዚህ በኋላ ወልድያ ላይ የቃና ዘገሊላ በዓል ቃና ዘገሊላ ብቻ ሆኖ የሚታሰብ ይመስለናን? ገና ይዘፈንበታል፣ ይፎከርበታል፣ ይተረትበታል፣ ሙሾ ይወረድበታል፣ ውሎ ለቅሶ ይዋልበታል፡፡ ለመሆኑስ በየልቅሶ ቤቱ የተቀመጠው ሕዝብ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ፣ ስለ መንገድና ትምህርት ቤት፣ ስለ ባቡርና አውሮፕላን ማረፊያ የሚጨዋወት ይመስለናል? ገና ተዝካር፣ መት ዓመት፣ ሰባት ዓመት፣ ሃያ አንድ ዓመት የሙታን በዓል አለ፡፡ በነዚህ ዘመናት ሁሉ ምን የሚባል ይመስላችኋል?
እንዲህ ላሉ ችግሮችስ ጥይት መፍትሔ አለመሆኑን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ያለፈችበት ሁኔታ ብቻ እንዴት አያስተምረንም? ይልቅ ለምን የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ አንሠራም? ‹የሚያስለቅስ ነገር ነግሮ አታልቅስ ይለኛል› የሚል የትግርኛ አባባል አለ፡፡ ሕዝቡ ለምን ባሰው? ወጣቶቹ ለምን ተቃወሙ? የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩስ ምንድን ነው? ብሎ መሥራት አይሻልም፡፡ ለምን ሕዝብን ከሕዝብ ወገንን ከወገን የሚያጋጭና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቂም እንዲቋጠር ይፈለጋል? ለምንስ የዘርና የጎሳ መልክ እንዲይዝ ይፈለጋል? ወንጀለኞችስ ለምንድን ነው በጎሳ ካባ ውስጥ እንዲደበቁ ሁኔታዎች የሚመቻቹት? ከመሬት መንቀጥቀጡ(shock) በላይ ድኅረ መንቀጥቀጡ(aftershock) ውጤቱ የከፋ መሆኑን አናውቅምን? ችግሩንስ ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?
አሁንም ባለ ሥልጣኖቻችን ቆም ብለው የማሰቢያ ጊዜያቸው ባያሳጥሩት መልካም ነው፡፡ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ‹የከተማዋ ሁኔታ እየተረጋጋ ነው› ዓይነት ዜና ራስን ማታለያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ስብሰባ ደምን አድርቆ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዝምታ በመቀበል፣ ፋታም በፍጻሜነት ሊተረጎም አይችልም፡፡ በበላይ ዘለቀ ምክንያት በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወታደሮች ግፍ የተፈጸመበት የጎጃም
ገበሬ ምነው ዝም አለ? ሲባል
ዝም አልክ ይለኛል ዝምታ የታለ
ውስጤ እየጮኸ ነው እየተቃጠለ
ብሎ የገጠመው የልቅሶ ግጥም ሁኔታውን በሚገባ የሚገልጠው ይመስለኛል፡፡ አሁንም ሰይፍ ወደ ሰገባው፣ ቃታም ወደ ቦታው፣ ይግባ፡፡ ወንጀለኞችም ወደ ፍርድ፣ ችግሮችም ወደ መሠረታዊ መፍትሔ ይምጡ፡፡ መንግስትም ወደ ልቡናው ይመለስ፡፡