ለአፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ ባሉበት /ያሬድ ጥበቡ /

ለአፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ ባሉበት /ያሬድ ጥበቡ /

ክቡርነትዎ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ባስገቡበት ወቅት፣ ለውሳኔዎ የሰጡት ምክንያት ከተገቢ በላይ መሆኑን ብረዳም፣ በርስዎ ምትክ ወያኔ ሊጎልተው የሚችለው ሰው እንደ አስመላሽ ዓይነቱን ወያኔ፣ ወይም ሌላ የጎማ ማህተም ሆኖ የሚያገለግል የሽፈራው ሽጉጤ ዓይነት ሰው እንዳይሆን በመፍራት ከኢትዮጵያችን ጥቅም አኳያ ወደሥራዎ እንዲመለሱ ከተማፀኑዎት ጥቂት ሰዎች መሃል አንዱ ነኝ። ለመመለስ ሲወስኑም እጅግ ከተደሰቱት መሃል።

ወደ ወንበርዎ ከተመለሱ ወዲህ ባሉት ቀናት ግን የኢትዮጵያችንን ተስፋ የሚያጨልሙ የዘር ጭፍጨፋዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። እነዚህን መስመሮች ስተይብ ቆቦ ውስጥ አማሮችን ዒላማ ያደረገ ግድያ እየተካሄደ ነው። በዚህ የተናደዱ ወጣቶችም የወያኔ አባላትና ተጠቃሚዎች በሚሏቸው የቢዝነስ ተቋሞች ላይ አፀፋዊ እርምጃ እየወሰዱ ነው። ንብረቶች እየወደሙ ለመሆኑ የወያኔ ማህበራዊ ሚዲያ ፊታውራሪዎች እየዘገቡ ነው።

ይህን የቆቦ ተቃውሞ የቀሰቀሰው የቃና ዘገሊላ በዓል ላይ በወልዲያ በንፁሃን ዜጎች ላይ አጋዚ ያካሄደው ጭፍጨፋ ቢሆንም፣ ከጀርባው የራያ ቆቦ መሬት በእብሪት ወደ ትግራይ መጠቅለሉ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየ የህዝብ ብሶት እንደነበር ፍንጭ የሚሰጥ ነው ብዬ አምናለሁ። ትግራይ የኢትዮጵያ እስከሆነች ወሰኗ አሎውሃ ሆነ ሆጤ ተራራ የወሎ ሰው በሆደሰፊነት ሊያሳልፈው ዝም ብሎ ነበር። ሆኖም ከከተራ በዓል ጀምሮ ሲተናኮሰው የሰነበተው የአጋዚ ጦር በቃና ዘገሊላ በዓል መጠናቀቂያ ላይ በስናይፐርና መትረየስ የታገዘ ጭፍጨፋ ሲያወርድበት፣ ይህ በራሱ ኢትዮጵያዊ ወገኑ የተደረገበት አድርጎ ሊቀበለው አልቻለም ። በጠላት ጦር የተካሄደ የጅምላ ፍጅት አድርጎ ነው የወሰደው። ስለሆነም፣ ብሶቱ በአፋጣኝ ወደሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት ይችላል። ኢትዮጵያችንም ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ልትገባ ትችላለች።

ይህን ደብዳቤ ልፅፍልዎት ያነሳሳኝ የጉዳዩ አሳሳቢነት ነው ። በወገን ላይ የታሰበበት፣ የታቀደ፣ በዘር ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ጭፍጨፋ እንዴት ሊካሄድ ቻለ? የመከላከያ ሃይሉ የእዝ ተዋረድ ምን ቢሆን ነው እንዲህ አይነት የታቀደና የታሰበበት ፍጅት ሊካሄድ የቻለው? የህዝብ ተወካዪች ምክርቤት ምን ማድረግ ይችላል? የኢህአዴግ ሥራአስፈፃሚ ስብሰባ ተከናውኖ መሪዎቹ በጋራ ቆመው መግለጫ በሰጡ ማግስት፣ ከወር በፊት የመቀሌን የእግርኳስ ቡድን አዋርዳችኋል በሚል በአውቶማቲክ መትረየስ እንበቀላችኋለን የሚል የወመኔና ዘረኛ ፍጅት ሲካሄድ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፉ ተሸብቦ ሊቀመጥ አይቻለውም ። መመርመር፣ ጥፋተኛው ለፍርድ እንዲቀርብ ለመንግስት መመሪያ መስጠት፣ የህዝብን እምባ ማበስ ይገባዋል። ክቡርነትዎ እጅ ላይ ትልቅ ሃላፊነት ወድቋል ።

ከሥራ መልቀቅ ሙከራዎ በኋላ ወደ መንበርዎ የተመለሱት፣ ለ27 ዓመታት እንደተለመደው የወያኔዎች የጎማ ማህተም ለመሆን አይደለም። ከነአስመላሽ የዘረኛ ፖሊሲ አመራር ለመቀበል አይደለም። በህሊናዎ ሃይል ለመሥራት እንጂ ። የወከልዎትን ህዝብ ለማገልገል እንጂ። ምንም እንኳ ከአንድ የምርጫ ወረዳ ተመርጠው የመጡ ቢሆንም፣ በአፈጉባኤው መንበር ላይ ሲሰየሙ የሚወክሉት የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ ነው ። ስለሆነም የዚህን የአጋዚ ፍጅት ጉዳይ እልባት ሊያስገኙለት ይገባል። አንዱ ወሳኝ መፍትሄ ትግሬዎች በመከላከያውና ደህንነቱ መዋቅር ውስጥ ያላቸውን የበላይነት የሚያስቆሙ ድንጋጌዎችን እርስዎ የሚመሩት ምክርቤት መወሰን ይችላል። ከሰው ሃይል ብሄራዊ ተዋፅኦ ባሻገርም የመከላከያው ተግባር ሃገርን ከውጪ ወራሪ መከላከል እንጂ ህዝብ ብሶቱን እንዳይገልፅ መከላከል እንዳልሆነና፣ ይህንን በተላለፉ የመከላከያ መኮንኖች እስከሞት ድረስ በሚያስጠይቅ ወንጀል የሚያስከስስ ህግ እንዲወጣ ማድረግ የያዙት ሥልጣን የሚያስገድድዎ ይመስለኛል ።

ክቡር አፈጉባኤ አባዱላ ሆይ! የኢህአዴግ ሥራአስፈፃሚ ጉባኤ በተጠናቀቀና ለሃገራዊ መግባባት በጋራ እንሠራለን በተባለ ማግስት የተካሄደው የወልዲያ ጭፍጨፋና ዛሬ ቆቦ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ፍጅት የሚነግረን ነገር ካለ፣ የሃገሪቷ የሰላም ተስፋ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑን ነው ። ወያኔ ደካማ ተሰሚነት ያለውና፣ የህዝቡን እምባ ሊያብስ የሚችለው ይህ ምክርቤት በመሆኑ፣ በአፈጉባኤው ላይ የወደቀው ኃላፊነት ሃገራዊና ትልቅም ነው ። የምክርቤቱን መድረክ የህዝቡ ድምፅና ዋይታ የሚሰማበት መድረክ በማደረግና፣ በተደመጠውም የህዝብ ድምፅ ላይ የተመሠረቱ ህጎችና ድንጋጌዎች ህዝቡን እያረጋጉና ተስፋ እንዲሰንቅ እያገዙ ካልሄዱ ነገሮች በአፋጣኝ ሊዳፈኑ ይችላሉ ። ክቡርነትዎ ድምፅዎትን ያሰሙ፣ ኃላፊነትዎን ይወጡ ። የሚያስፈራዎትም ጉዳይ ሊኖር አይችልም። ቢያንስ ታላቁ የኦሮሞ ህዝብ በዙሪያዎ ነው ። የኦህዴድ ዴሞክራሲያዊ አመራር ድጋፍ ከጎንዎ ነው ። አሁን እነአስመላሽን የሚፈሩበት ወቅት አይደለም። የሚፈሩበት እንጂ። አዲስአበባን ዙሪያዋን የከበባትን የቄሮ ድጋፍ ይዘው አያመንቱ። አበው እንደሚሉት ጊዜን ሥሩበት እንጂ አይሥራብዎ! ፈጣሪ ቀናውን ያሳይዎ! የዚህ ወጣት ሰማዕት ምስል ከህሊናዎ አይውጣ። ፍትህም እንዲያገኝ እርዱት።

LEAVE A REPLY