ገዱን ያስለቀሰው ብቸኝነቱ ይሆን? /ሞሀመድ አሊ ሞሃመድ

ገዱን ያስለቀሰው ብቸኝነቱ ይሆን? /ሞሀመድ አሊ ሞሃመድ

SamuelWondyifraw አንድ ማለፊያ ትንታኔ ለጥፎ አየሁ። የተነጋገርን ይመስል የማስበውን ነው የፃፈው። ገዱ የአማራ ክልል ፕሬዝዴንት ሆኖ ሳለ የወልዲያ ወጣቶችን ሰብስቦ ለምን አለቀሰ? የወንድ ልጅ እንባ እንዲህ እንደዋዛ በቀላሉ ይፈሳል? የገዱ ለቅሶ ምስጢሩ ወዲህ ይመስለኛል።

ሰሞኑን ደሴ ሄጄ ከሰሜን ወሎ ልጆች (ጓደኞቼ) ጋር ስለገዱ አንስተን እያወራን ነበር። ገዱ በሰሜን ወሎ ዳውንት ተወልዶ ያደገ ሲሆን በትምህርቱ በጣም ጎበዝና በአካባቢው ሥመ-ጥር ከሆኑ ተማሪዎች አንዱ ነበር። ግና ትምህርቱን ከዳር ሳያደርሰው በቀድሞው ኢህዴን ሰዎች ተጠለፈና ፖለቲካ ውስጥ ገባ። አንዳንድ ጓደኞቹ ፖለቲካውን በጊዜ በቃን ብለው ወደ ትምህርታቸው ሲመለሱ እሱ ግን እንደዋዛ ከገባበት ወጥመድ በቀላሉ መውጣት አልቻለም።

የአካባቢው ልጆች እንደሚሉት ገዱ ከበፊቱም ቁጭት ነበረው። እነሆ አሁን የሰሜን ወሎ – ወልዲያ – ቆቦ – መርሳ. .. ልጆች ደም እየፈሰሰ ነው። ሀዘንና ቁጭቱን በአካባቢ ደረጃ እንየው ከተባለ ገዱ ከማናችንም ይቀርባል። ግን ምንም ማድረግ አይችልም።

“ብአዴን” ተብየው ፀረ-አማራ ኃይል በነማን ሲመራ እንደነበር ብዙ ተወስቷል። አብዛኞቹ በዕድሜ ምክንያት ወደውጭ የተገፉ ቢመስሉም ከቅርብ-ርቀት አልጠፉም። የብአዴን አመራር አዲስ ቢመስልም ዛሬም ውስጡ ከፀረ-አማራ አስተሳሰብ አልጠራም። እንዳውም በፀረ-አማራ ኃይሎች ተተብትቧል ማለት ይቀላል።

ገዱ ከታችም ከላይም; እንዲሁም ከጎኑ እርምጃውን የሚለኩ “ጅቦች” እንዳሉ ያውቃል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥቃት ኢላማ ውስጥ እንዳስገቡት ያውቃል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ምን ማድረግ ይችላል? ማን ነበር “በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ብዙ ማወቅና ምንም ማድረግ አለመቻልን የመሰለ ስቃይ የለም” ያለው? አዎ; ግሪካዊው ፈላስፋ ሄሮዶተስ ነበር።

እናማ ገዱ ጥቃቱ ተሰምቶታል። ስለሆነም የቁጭት እንባውን አፈሰሰ። በዚያ ላይ ብቸኝነትም የሚሰማው ይመስላል። እናም ጣቱን ቀሰረ። ወደማን? “ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ብአዴን ነው” ሲል እቅጩን ተናገረ። “ብአዴን” ሲል ጣቱን ወደነማን እየቀሰረ እንደሆነ ልብ በሉልኝ! ነገሩን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ “ችግሩ የተጠራቀመ ብሶት ውጤት ነው” ሲል አከለበት። ገዱ ይህን ብሶት አሳምሮ ያውቀዋል። እናም ብሶቱ ፈነቀለውና በወጣቶቹ ፊት አለቀሰ።

ይህ የኔ ግንዛቤ ነው።

LEAVE A REPLY