/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የወልድያ እግር ኳስ ቡድን የመደበኛ ልምምድ መርሀ-ግብሩን ማቆሙንና ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተጫዋቾቹም ከተማውን ለቀው መውጣታቸው ታወቀ።
ለቡድኑ መበተንም የመንግስት ቀጥተኛ እንጅ እንዳለበት ደጋፊዎች እየተናገሩ ነው። ወልድያ በ11ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ወደ ጅማ በማቅናት ከጅማ አባጅፋር ጋር ጨዋታውን አድርጎ ሲመለስ 4 ተጫዋቾቹ አዲስ አበባ ላይ ከቡድኑ መለየታቸውም ተነግሯል።
በቡድኑ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይም የክለቡ የስራ ሀላፊዎች ዝርዝር ሁኔታ እንደሚሰጡ ተጠቁሟል። ወልድያ በተለይም ባለፉት አምስት ወራት በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ስትሆን በዚህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ፕሪሜርሊግ የሚሳተፈው ወልዲያ ከተማ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 11ኛ ሳምንት ባህር ዳር ከተማና ሽሬ እንዳስላሴ ባለፈው ሳምንት በለገጣፎ ሊደረግ የነበረ ጨዋታ በጸጥታ ምክንያት መቋረጡ የሚታወስ ሲሆን ዛሬም በአዲስ አበባ በኦሜድላ ሜዳ ጨዋታው ሊካሄድ ተጫዋቶች ወደ ሜዳ ከገቡ በሗላ የፀጥታ አካላት ከበላይ አካል በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት ጨዋታው እንዳይደረግ በማለታቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።