በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ጥፋት አስመልክቶ ከክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት (ካብኔ) የተሰጠ መግለጫ
በክልላችን ሁለተናዊ ልማት ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዘርፈ ብዙ ተግባር በመንግስትና በመላው ህብረተሰብ የተቀናጀ ጥረት ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የሀገራችንንም ሆነ የክልላችንን ተስፋ ያለመለሙ ለውጦችና ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይህም ውጤት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መጥቷል፡፡ በቀጣይነትም ይህንኑ የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ለማስፋት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በመንግስት በኩል የህዝቡን እርካታ በሚፈለገው መጠን ያለማረጋገጥ ድክመቶች እየተፈታተኑን ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የህብረተሰቡ እርካታ እጦት ፣ ቅሬታ እና ብሶት ወደ ግጭት እያመራ ዋጋ እያሰከፈለን ይገኛል፡፡
ሰፊው የክልላችን ህዝብ የአገራችን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በፈቀደለት መሠረት ከኋላ ቀርነት ተላቆ ከድህነት ለመውጣት በትጋት በሚረባረብበት በአሁኑ ወቅት ይህንኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴውንና የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ልማት ግስጋሴውን የሚገቱ ፈተናዎች እየተደቀኑበት ነው፡፡ ሰሞኑን በክልላችን በተለይም በወልዲያና አካባቢዉ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስና የሠላም መናጋት የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ወልዲያ ከተማ ቀደም ሲል በወልዲያ እና በመቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም የቃና ዘገሊላ በዓል በሚከበርበት ዕለት በበአሉ ታዳሚዎችና በህግ አስከባሪ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት ውድመት የተከሰተ ሲሆን ውሎ ሲያድርም ግጭቱ በቆቦ እና መርሳ ከተሞች የቀጠለ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ አልፏል፡፡ ከሁሉም በላይ በወልዲያ፣ በቆቦና በመርሳ ከተሞች ነዋሪዎች 13፤ ከፀጥታ ሃይሉ 2 በድምሩ የ15 ወገኖቻችን ህይወት ማለፉ ከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት ፈጥሮብናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ መስተዳድር ምክር ቤቱ ከሁሉ አስቀድሞ በጠፋው ውድና መተኪያ የሌለው የሰው ህይወት ከልብ የተሰማውን ጥልቅና መሪር ሃዘን እየገለፀ ለተጐጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ይመኛል፡፡
የተከሰቱ ግጭቶች መሠረታዊ መነሻ ምክንያቶቻቸው የህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎች እንዲሁም ቅሬታዎችና ብሶቶች መደማመርና ሳይፈቱ መዋል ማደራቸው ሲሆን በየደረጃው ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ካለመስጠት ጋር የተያያዙም ናቸው፡፡ የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት እነዚህን ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ከምንጊዜውም በላይ ጥረት እየደረገና በትኩረት እየጠሰራ ይገኛል፡፡
የክልሉ መንግስት በወልዲያ ከተማ ጉዳቱ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ በልዩ ትኩረት በርዕሰ መስተዳድሩ መሪነት በቦታው በመገኘት ቅድሚያ የዜጐችን ህይወት ለመታደግና ግጭቱን ለማስቆም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በጋራ ተረባርቧል፡፡ በዚህም የህብረተሰቡ ቀና እና አስተዋይነት የተሞላበት ተሳትፎ ተጨምሮበት አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ ክስተት ከጥፋት ውጪ የሚገኝ አንዳችም ትርፍ ካለመኖሩም በላይ አንዳንዶቹ የግጭት አዝማሚያዎች የህዝቦችን ፀንቶ የኖረ አብሮነትንና አንድነትን በሚጐዳ መልኩ የተከሰቱ መሆናቸውና የመንግስት ተቋማትና የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ የዜጐች ሀብትና ንብረት በአጭር ጊዜ እንዲወድም አድርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ክስተት ግን በምንም መንገድ ቢሆን ግጭቱ የተከሰተባቸውን የአካባቢ ህዝቦች የማይወክል ተግባር ነው፡፡
በዚህ ጥፋት ለህዝብ ጥቅም የተገነቡና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ የመንግስት ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ሁሉም ውድመቶች በዚህ ዘመን ሊታዩ የማይገቡ አሳፋሪ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ግጭቱ የህግ የበላይነትን ከመጣሱ የተነሳ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ህይወት አናግቷል፤ ስጋትና ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል፡፡
የአማራ ክልል ህዝቦች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሁሉም የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር አኩሪ ባህልና ጥብቅ የሆነ ትስስርንና አብሮነትን ጠብቀው መኖርን የሚያውቁና በዚህም የሚገለፅ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የእነዚህ እሴቶች ባለቤት የሆኑት የወልዲያና አካባቢው ነዋሪዎችም ግጭቶቹ ከተከሰቱ በኋላ በአካባቢው የህግ ጥሰትና ስርዓት አልበኝነት በመንገሱ የራሳቸውም ሆነ የመንግስት ሃብትና ንብረት ከዘረፋና ከጥፋት እንዲድን እንዲደረግ ለመንግስት ጥሪ ከማቅረባቸውም ባለፈ በሚችሉት አቅም ሁሉ የተጎዱትን ወገኖች በመደገፍና ከፖሊስ ጎን ሆነው ፀጥታውን በማስከበርና አጥፊዎችን ለህግ እንዲቀርቡ በመተባባር ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ ሌላ በአካባቢው ግጭት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በቦታው በመገኘት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማወያየት ችግሮች በውይይትና በጋራ የሚፈቱ መሆናቸውን በመተማመን በአካባቢው የተፈጠረው ሁከት በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶችና በመላ ህብረተሰቡ ትብብር ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የማድረግ ሥራ በመሰራት ላይ ነው፡፡ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በሰላም እና የህግ የበላይነት ጉዳይ ላይ መተማመን በመጀመሩ በአሁኑ ጊዜ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ለህግ እየቀረቡ ከተሞቹም ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ መግባት የጀመሩ ሲሆን መንገዶችም ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ህገ መንግስት አንቀፅ 56 ንዑሱ አንቀፅ (1) መሠረት የክልሉ ከፍተኛ አስፈፃሚ እና አስተዳደራዊ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ (6) እንደሚደነግገው መስተዳድር ምክር ቤቱ በክልሉ ውስጥ ህግና ስርዓት መከበሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ወቅታዊ አቋም እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-
================
1. በወልዲያ ከተማ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሃይማኖት ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት የተፈፀመውን ድርጊት በሚመለከት ምንም እንኳን አንዳንድ ቡድኖች የሀይማኖቱ ስርዓት በማይፈቅደው መልኩ ተንኳሽ ተግባራት መፈፀማቸው ስህተት መሆኑን ብናምንም ፤ መነሻው ምንም ይሁን ምን የተፈፀመው የሰው ግድያም ሆነ በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የተደረገ ተኩስ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት በሚካሄድበት እና ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅትና ቦታ ፀጥታ ያደፈረሱም ይሁን በስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች ላይ ጥይት የተኮሱ፣ ሰው የገደሉ፣ ልዩ ልዩ ጉዳት ያደረሱ አካላት ጉዳዩ በዝርዝር ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
2. ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በወልዲያ ከተማ የደረሰውን ጉዳት መቃወምና በመሰለው መንገድ ማውገዝ ህገ-መንግስታዊ መብት ቢሆንም ይህንን በወልዲያ ከተማ የተፈጠረውን ግጭት በምክንያትነት በመጠቀም በዕለቱም ሆነ በተከታዮቹ ቀናት ዜጎች በያዙት አመለካከትም ሆነ ማንነታቸው ላይ በመመስረት የደረሰው ጥቃት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ተግባር በመሆኑ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ኢንቨስትመት እንዲወድም ፣ የግለሰቦችና የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዲቃጠል፣ እንዲዘረፍና በልዩ ልዩ መንገድ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ፣ በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያስተባበሩም ሆነ የተሳተፉ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ክህብረትሰቡ ጋር በመተባበር እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡
3. በህብረተሰቡ የተነሱ በአመራር አካላት፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በፍትሃዊ ተጠቃሚት የሚገለፁ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዝርዝር ተለይተው በቅደም ተከተል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡
4. በወልዲያና በአካባቢው የተፈጠረው ግጭት ያደረሰው ጉዳት አሁን ከደረሰው በላይ እንዳይሆንና አድማሱን እንዳያሰፋ የፀጥታ ሃይሎች ያደረጉት ርብርብ የሚያስመሰግናቸው ሲሆን በታጋሽነትና በወገናዊነት ስሜት፣ የፀጥታውን ችግር ለመቅረፍ ለከፈሉት መስዋዕትንት እና ላደረጉት መልካም እንቅስቃሴ መስተዳደር ምክር ቤቱ ላቅ ያለ ምስጋናውን ይገልፃል፡፡
5. በወልዲያ፣ በቆቦ፣ በመርሳና በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ በተለይም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ያሳዩት ርብርብ አክብሮታችን ላቅ ያለ መሆኑን እየገለፅን በቀጣይም ህብረተሰቡን ሠላሙን ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደተለመደው ሁሉ ከክልሉ የፖሊስና የፀጥታና ሃይል ጐን ተሰልፎ እንዲንቀሳቀስ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በቀጣይም መንግስት የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ እና ሃብት፣ ንብረት ያወደሙ ማናቸውንም ወገን መረጃ ላይ ተመስርቶ ከክልሉ በተወከሉ ሙያተኞችና አመራራሮች ደረጃ እያጣራ በመሆኑ ይህ እንደተጠናቀቀ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድና ይህንን በግልጽ ለህብረተሰቡ የሚሣውቅ መሆኑን ሲያረገግጥ የህብረተሰቡንም ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አጥብቆ እንደሚሠራ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡
በመሆኑም ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብም በየአካባቢው ከልማት ሥራው ሳይቋረጥ በአብሮነት መንፈስ የሰላም ባለቤትነት ተግባሩን ለአፍታም ቢሆን ሳይዘነጋ ከፀጥታ ሃይሉ ጐን በመቆም ሰላም ለማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ በቀጣይነት እንዲወጣ አበክሮ ያሳስባል፡፡
ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳደር ምክር ቤት
ባህር ዳር