“መታገስ” ለእኛ እና ለእነርሱ… /በፈቃዱ ዘ ኃይሉ/

“መታገስ” ለእኛ እና ለእነርሱ… /በፈቃዱ ዘ ኃይሉ/

“አድማው የተጠራው መጥፎ ሰዐት ላይ ነው”፣ ወይም ደግሞ “ትንሽ ለምን አይታገሱም?” የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ደጋግመን እንሰማለን። ብዙ ግዜ በጭቆና እና በትዕግስት ላሳለፍነው ሕዝቦች ‘ታገሱ’ የሚለው ቃል ምን ያህል አሳማኝ ነው? የኢሕአዴግ ሹማምንት “ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ግዜ ይወስዳል” ሲሉ እንዲሁ ‘ስንጨቁናችሁ ታገሱን’ ማለታቸው ነው። “ታገሱ” ወይም “ለመቃወም አሁን ግዜው አይደለም” ማለት ማታለል ነው። አሁን ደግሞ በጣም እያሳዘነኝ ያለው ይህ ንግግር ከተቃዋሚው ወገን ወይም ከሕዝቡ ወገን ከሆኑት ሳይቀር መምጣቱ ነው።

“ታገሱ” ወይም “ግዜው አይደለም” የሚለው አስተያየት “ምክር እና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው” እንደሚሉት ነው እንጂ ይህ ሳይታሰብበት ቀርቶ አይደለም። ንግግሩ የማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹን) “Why We Can’t Wait” የሚል ጽሑፍ ያስታውሰኛል።

ማርቲን ሉተር ኪንግ “የሚያሳዝነው” ይላል፤ “የሚያሳዝነው ተጠቃሚ ቡድኖች ጥቅማቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አሳልፈው የማይሰጡ መሆናቸው ታሪካዊ ጥሬ ሐቅ መሆኑ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች ትክክለኛው ነገር ታይቷቸው ኢፍትሐዊነትን እምቢ ሊሉ ይችላሉ። … ቡድኖች ግን ከግለሰቦች የበለጠ ክፉ ናቸው።” ይህን አያደርጉም። ባለፈው ሳምንት እነበቀለ ገርባ የፍቺ ዝርዝር ውስጥ አልነበሩም። ሥማቸው የተጠቀሰው በኦሮሚያ ከሰኞ እስከ ረቡዕ የተጠራው አድማ መጀመሩ እንደማይቀር ቁርጡ ሲታወቅ ነው። ረቡዕ ይፈታሉ ከተባለ በኋላ ማክሰኞ ከሰዐት በኋላ የተፈቱት አድማው እና ተቃውሞ ዋና ከተማዋን ያንኳኳል በሚል ድንጋጤ እንደሆነ እናውቃለን። አሁንም የእነኮሎኔል ደመቀ ፍቺ ዜና የመጣው በአማራ ክልል ሰኞ ጀምሮ አድማ ሊካሔድ ይችላል በሚል ስጋት ነው። የኦሕዴድ መለወጥ፣ የብአዴን መግደርደር፣ የኢሕአዴግ መልመጥመጥ ሁሉም በሕዝባዊ ጫና የመጣ እንጂ በፈቃደኝነት የሆነ አንድም ነገር የለም።

ኪንግ ቀጥሎም እንዲህ ይላል፣ “ግዜ በራሱ ገለልተኛ ነው። ለጥፋትም ለመልካምም ነገር ሊውል ይችላል። አሁን አሁን ግን ግዜን ከደጋጎች ይልቅ ክፉዎች በአግባቡ ይጠቀሙበታል ብዬ ማሰብ ጀምሬያለሁ”። አባባሉ የተሳሳተ አይመስለኝም። ክፉዎች ሁሌም ሴራቸውን ለመጎንጎን፣ ከወደቁበት ለመነሳት ግዜ መግዛት ይፈልጋሉ። ታገሱ ይሉናል። ቅኖች ትግስትን በቅንነት ሲቀበሉ ክፉዎች ግዜውን ለክፋታቸው በአግባቡ ይጠቀሙበታል። ለኪንግ “…የሰው ልጅ ስኬት መሽከርከሩ የማይቆም ጎማ አይደለም።” ‘ደከመኝ በማያውቁ ሰዎች ጥረት የሚጨበጥ ነገር ነው’። እናም ‘ጊዜ፣ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ሁሌም በስሎ የሚጠብቀን ፍሬ ነው’ ይላል።

ትዕግስት መልካም ነገር ሆኖ ሳለ የጨቋኞች ግዜ መግዣ እንዲሆን መፍቀድ ግን ብዙ መስዋዕትነት ለከፈሉ ሕዝቦች አዋጭ አይደለም።

ይህንን ስል አመፅን የደገፍኩ ሊመስል ይችላል። በፍፁም። እንዲያውም ኪንግ በዚያው ጽሑፉ ላይ “በአመፅ ሁሉንም ነገር እናጥረግርገው” የሚሉ እና “እንታገስ ሁሉም በግዜው ይሆናል” የሚሉት ሁለቱም አንድ ናቸው ይላል። እኔም ስለምስማማበት ነው እዚህ የምጠቅሰው። ምክንያቱም ሁለቱም ምንም ለውጥ አያመጡም። ነገር ግን አመፅ አልባ አድማዎች እና ማስተጓጎሎች የታወቁ የሠላማዊ ትግል መርሕዎች ናቸው። መንገድ በመዝጋት የሚሰቃዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዘንግተው የራሳቸውን ቢዝነስ የሚያሳድዱ ግለሰቦች ለአጭር ግዜም ቢሆን የወገኖቻቸውን ጉዳት እንዲረዱት የማስገደጃ ቅዱስ ተግባር ነው። በተጨማሪም ለቢዝነሳቸው አለመስተጓጎል ሲሉ የተበዳዮችን ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ የበኩላቸውን እንዲያዋጡ የማስገደጃ ቅዱስ ተግባር ነው።

ትግሉ ይቀጥላል!
Qabsoon itti fufaa!

LEAVE A REPLY