18 ክልከላዎች ያሉት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድወራት እንደሚቆይ ተገለጸ

18 ክልከላዎች ያሉት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድወራት እንደሚቆይ ተገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ የወያኔው መከላከያ ሚኒስትርና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሪቴሪያት ሲራጅ ፈጌሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃጸም በተመለከተ ማብራሪያ ሰጡ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላ ሀገሪቱ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን ለስድስት ወራትም እንደሚቆይ ተናግረዋል። በስድስት ወራት ውስጥም ሁኔታዎች ካልተረጋጉ ተጨማሪ ለአራት ወራት ሊራዘም እንደሚችልም አስረድተዋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ 18 አይነት ክልከላዎች የያዘ ሲሆን ለጠብ የሚያነሳሱ የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየት፣ የጦር መሳሪያዎችን መያዝ፣ እንደ አስፈላጊነቱ በማንኛውም ሰዓት ያል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍተሸና ብርበራ ማድረግ፣ አስፈላጊ በሆነባቸው አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደብ መጣል፣አንዳንድ የህትመት ውጤቶችን ማቀብ፣ ትዕይንትና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን መከልከል፣በቡድን መንቀሳቀስ መቆጣጠር፣ ለፀጥታ መረጋጋት አስጊ መስሎ ከተገኘ ማንኛውም አይነት የመገናኛ ዘዴዎች ማቋረጥና ሌሎች ክልከላዎች በአዋጁ መካተታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ይሆን ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ ሲመልሱ “አሁን ያለው መንግስት በህዝ የተመረጠ ስለሆነ የሽግግር መንግስት” ሊመሰረት እንደማይችል አሳውቀዋል። ወታደራዊ መንፈንቅለ መንግስትም እንደማይኖር ጨምረው ገልጸዋል።

ከትናንት ጀምሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በ15 ቀናት ውስጥ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንደሚቀርብም ገልጸዋል። በህገ-መንግስቱ መሰረት አዋጁ ተፈጻሚ ለመሆን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት 2/3ኛ ድምጽ ማግኘት አለበት። በመሆኑም በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያላቸው ኦህዴድና ብአዴን ለአዋጁ ድጋፍ መንፈጋቸው እየተነገረ ነው።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚወሰዱ እርምጃዎች
-ይፋዊ ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን፣ ፅሁፍ ማዘጋጀትን እና አትሞ ማሰራጨትን፣ ትእይንት ማሳየትን፣ በምልክት መግለፅን ወይም መልዕክትን በማንኛውም ሌላ መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግን ይከለክላል።
· ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም ደግሞ እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል፣
· የህዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ሲባል የአደባባይ ሰልፍና ሰልፍ ማድረግን፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን ይከለክላል።
· በህገመንግስቱና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን የጠነሰሰ፣ የመራ፣ ያስተባበረ፣ የጣሰ ወይም በማንኛውም መንገድ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈ ወይም ተሳትፏል ተብሎ የሚጠረጠር ማንኛውም ሰውን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ያደርጋል። ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በመደበኛው ህግ ተጠያቂ ያደርጋል።
· ወንጀል የተፈፀመባቸውና ሊፈፀምባቸው የሚችሉ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ ማናቸውንም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበር እንዲሁም ማናቸውንም ሰው ማስቆም፣ ማንነቱን መጠየቅ እና መፈተሽ ይችላል።
· በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ እቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ተጣርቶ ለባለመብቱ ይመለሳል።
· የሰዓት እላፊ ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል።
· ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ እንዲሆም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ ወደተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋል።
· የተቋማትን የመሰረተ ልማትን የጥበቃ ሁኔታ ይወስናል።
· የህዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የጦር መሳሪያ ወይም ስለት፣ እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን ቦታዎች ለይቶ ይወስናል።
· በሰላም መደፍረስ ምክንያት የፈረሱ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን ከክልል እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር መልሶ እንዲቋቋሙ ያደርጋል።
· ብሄር ተኮር በሆነ ወይም በሌሎች ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ከክልል መንግስታት እና ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር ወደ ቀድሞ መኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ድጋፍ ያደርጋል።
· ህዝብ የሚገለገልባቸው የአገልግሎት ተቋማት፣ የንግድ ስራዎች ወይም የመንግስት ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ተገቢውን ጠበቃ ያደርጋል።
· ይህን ተላልፎ አገልግሎት ያቋረጠ ማንኛውም ሰው በህግ ተጠያቂ ይሆናል።
· የመሰረታዊ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርቦት የዝውውር እና የስርጭት ደህንነትን ያረጋግጣል።
· የትራንስፖርት ፍሰት ደህንነትን ይቆጣጠራል፤ ያረጋግጣል።
· በትምህርት ተቋማት የመማር እና ማስተማር ሂደት ከሚያውኩ ተግባራት የፀዱ እንዲሁም መደበኛ ስራን የሚያስተጓጉሉ እንከኖች እንዳይፈጠሩ ይሰራል።
· ህገመንግስቱ እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር፣ ከአደጋ ለመጠበቅ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች ይወስዳል።
እነዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮምንድ ፖስት የሚወሰዱ አርምጃዎች ናቸው

LEAVE A REPLY