የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በሚቀጥለው ሐሙስ እንደሚጀመር ታወቀ። መረጃዎች እንደጠቆሙት 180 አባላት ያሉት የድርጅቱ ስብሰባ ከመጋቢት 1 እስከ መጋቢት3/2010 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ለማድረግ መርሃ-ግብር እንደተያዘለት ታውቋል።
ም/ቤቱ በስብሰባው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን እንደሚያነሳ የተገለጸ ሲሆን የድርጅቱን ወቅታዊ አቋም፣ የፓርቲውን ስድስት ወር የአፈፃፀም ሪፖርት መገምገም እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ መቀበልና በምትካቸው የፓርቲውን ሊ/መንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም እንደሆነ ተገልጿል።
የኢህአዴግ ምክር ቤት ከ4ቱ ፓርቲዎች የተውጣጡ 180 አባላትን ያቀፈ ሲሆን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የደቡብ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደህዴን) እና ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሃት) ናቸው።
ከኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባ በፊትም 36 አባላት ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከሰኞ እስከ ዕሮብ ባለው ጊዜ ውስጥ ለስብሰባ እንደሚቀመጥ ተነግሯል።
የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸው እንደሚነሱ ወይም እንደሚለቁ ከገለጹ በሗላ በቦታው ማን ይተካል የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እየተሸራሸረ ይገኛል።
ከህወሓት በስተቀር ሦስቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የየራሳቸውን እጩ እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል። ከኦህዴድ ዶክተር አብይ አህመድ፣ ከብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ደህዴን ስብሰባውን አጠናቆ የድርጅቱን መሪ መርጦ ባያሳውቅም አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው እየተገለጸ ነው።
የመከላከያ ሀይሉን፣ ደህንነቱንና ፌዴራል በፖሊስን ጠርንፎ እንደያዘው የሚታወቀው ህወሐት ከጀርባ በመሆን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን ለሚፈልጉት ሰው ለመስጠት በሩጫ ላይ መሆናቸው በስፋት እየተነገረ ነው። ለዚህም የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች፣ የተመረጡ የትግራይ ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ ግለሰቦች የተሳተፉበት በመቀሌ የሰማዕታት ሐውልት ለሁለት ቀናት ዝግ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል። ስብሰባውንም በስዩም መስፍንና ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እንደሚመራ ታውቋል።
ህወሓቶች ዶክተር አብይን የመምረጥ ፍላጎት እንደሌላቸውን ይልቁንም ጉዳያቸውን ያስፈጽማሉ ብለው ከሚያምኗቸው አቶ ደመቀን ወይም ከዴህዴን የሚወከለውን ሰው ለማስመረጥ ፍላጎት አንዳላቸወውም ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ ግን በሚቀጥለው አርብ ወይም ቅዳሜ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።