መግቢያ
አዲሱ አለም በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ፣ በእንግሊዝኛ “New World Order” ተብሎ የሚታወቀውና ፕረዚዳንት ቡሽ ሲንየር በይበልጥ ያስተዋወቁት ወይም ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “አንዷለም”ያሉት ስርዐት አይደለም። አንዷለም፣ ሀገሮችን በኢኮኖሚ ያስተሳሰረ ስለሆነ በቀላሉ ሊፈርስ የሚችል አይደለም። በዚህ ጽሑፍ አዲሱ አለም ተብሎ የቀረበው በኢኮኖሚ ስለተጣመረው አለም ሳይሆን፣ በአዲስ ፖለቲካ ቀዝፈት ጎራ የፈጠሩትን መንግሥታት ሁኔታ የሚገልጽ ነው። የመንግሥታት በሁለት ጎራ መከፋፈል ልዩ የታሪክ ምዕራፍ የሚፈጥር ይመስላል። በእቅድ የመጣ አይመስልም፤ ያለ ብልሀትና እቅድ ሆነ ለማለትም ያዳግታል። በቀላሉ የሚቀለበስ ጉዳይ አይመስልም። በመጠኑም ቢሆን ቀውስ እንደሚፈጠር ይገመታል። ለውጡ ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደመጣና የሚያስከትለውን በጎ እና መጥፎ ነገር ከሚታየው አቻ አንጻር ጸሐፊው ለመግለጽ ይሞክራል። ሆኖም የጽሑፉ ዋናው ትኩረት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ያመቻቻል በሚለው ሁኔታ ላይ ይሆናል። ስለዚህ፣ የደራሲው አላማ በአለም የተጸነስው የሞለቲካ ለውጥ በተለይ ለኢትዮጵያ የሚያመጣውን አጋጣሚ ዕድል አጉልቶ ለማሳየት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ መስፍርት የሌለው መከራ ተቀብሏል። ምንግዜም ከብዙ ችግር በኋላ፣ ሕዝብ መልካም ነገር በእርግጥ ይመጣል ብሎ ተስፋ ያረጋል። በተአምርም ይሁን በሰው ቆራጥ ርምጃ ውሎ አድሮ አንድ ቀን መፍትሄው ይገኛል ብሎ ያምናል። አሁን የተፈጠረው የአለም ሁኔታ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የችግሩ መፍቻ በር ይከፍታል የሚል ከፍተኛ ግምት አለ። ማናቸውም ርምጃ የሚያስከትለው በጎ ውጤት ቢኖረውም፣ በመጠኑም ቢሆን መጥፎ ሊያመጣ ይችላል። በጎው ውጤት ኢትዮጵያ የምትቀዳጀው አዲስ የዘላለም የሰላም ኑሮ፣ የሰፊ ብልጽግና እና የበጎ አስተዳደር ዘመን እንደሚሆን ይገምታል። ይህ ጽሑፍ ለዚሁ ምግባር ዕቅድ ማፍለቂያ መነጸር እንዲሆን ለማድረግ ያለውን ዕድል ደመቅ አርጎ ይገልጻል።
የአለም ሀገሮች ወይም ኃያል መንግሥታቶች፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አለም ተደላድሎ በሰላም እንዲኖር የወሰዱት እርምጃ ነበር። የአለም መንግሥታት መደራጃ ተፈጥሮ፣ ግጭትንና ብጥብጥን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ማስከበር፣ ድህነትንና በሽታን ለማጥፋት ዋናው አላማው አድርጎ ብዙ የተሳኩ መርሆችን እየመፈጽ ቆይቷል። በዚህ ወቅት፣ ያልተጠበቀና ያልታሰበ ታሪካዊ ሁኔታ ተከስቷል። በአለም መንግሥታት መካከል አዲስ ፖለቲካ ገጾች ይታያሉ። እነሱም፣ ሰፍኖ የቆየው ዘመን ስርዐት ማለቂያና የሌላ ስርዐት መግቢያ ሆኖ ይታያል። የዚህ ሂደት የሚያስከትለው በጎ ወይም መጥፎ ውጤት አይታወቅም። በየጎራው የሚካሄድ ብዙ ውስጣዊ ሂደት አለ። ይኽም ባንድ በኩል ታላላቅ ሀገሮችን የሚያፈራርቃቸው መስሎ ሲታይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚያጎራርጥ ሁኔታ እንደሚሆን ይገመታል። መንግሥታት ‘ከመቻል’ ጋር የነበራቸው ግንኙነት አቁሞ ‘ከታፈሰ’ ጋር ሆኗል። ኢትዮጵያ ከ‘ከታፈሰ’ጋር ስትሰለፍ፣ ሌላው ጎረበት ‘ከመቻል’ጎራ ገብቷል። ይህ ድልድል የሚያስከትለው ውዥግብ አይታወቅም። የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚና የማህበራዊም ሁኔታዎች የሚያናጋ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ተንቃም እጅግ የምትከጀል ሀገር ናት። ድሃ ተብላ ስትታወቅ፣ የማትጠቅምና የማትፈለግ ሀገር አስመስሏታል። ዳሩ ግን፣ በብዙ ሀገሮች የፖለቲካ መንጋጋ ውስጥ እየታኘከች የኖረች፣ እነደ ጫት ሱስ የሆነችባቸው ሀገር ናት። ድሀ የተባለችው ኢትዮጵያ፣ የተፈጥሮ ኃብቷና የሕዝብ ጉልበት ወደር የለውም። በህዝቧ ታሪክ ደግሞ በአፍሪካም ሆነ በአለም ያላት ሚና ከኃያላን መንግሥታት ጋር የምትነጻጸር ነበረች። ጥንት፣ ፋሽሽት ጣሊያን ኢትዮጵያ “የኔ ጉዳይ ናት፣ እሷን የሚመለከተው ሁሉ በኔ በኩል ማለፍ አለበት” የሚል ሂስ ነበረው። እንግሊዝም ተመሳሳይ የቅኝግዛት ጽንስ ለመመስረት ብዙ ጊዜ ሞክራለች።
በዘመናችን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ እኔን ይመለከተኛል የሚሉ ተተክተዋል። እስራኤል፣ ተጋሪ ቅርስን ሰንሰለት አድርጋ በኢትዮጵያ ውስጥና ውጭ ጉዳይ ላይ ሰፊ ሚና እንደምትጫወት ይታወቃል። ጣሊያንና እንግሊዝ ያደርጉት የቅኝ አገዛዝ ስልት ነበር። አሁን እስራኤል በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ጣልቃ ገብ ስራ ግን፣ የወዳጅነት እንጂ የቅኝግዛት ስልት ተብሎ አልታየም። የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ኃይል ለዚህም ለዛም ግራጅ እየሆነ ብዙ ጉዳት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተፈጽሟል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኋላም ወገኑ የማይበጀውን የአሜሪካንን ፖለሲ ሲቃወም፣ ለውጥ እንዳይመጣ እየተሰናከለ ቆይቷል።
አዲስ ዘመን በአዋጅ የሚከፈት አይደለም። ባህሪንና ህሊናን መለወጥ ይገባል። ለለውጥ የሚያስፈልጉ አስቸጋሪ መዋቅርቶችም አሉ። ኢትዮጵያ ወራሪ ኃይልን የምትቋቋምበትና የምታሸንፍበት በቂ ኃይል አላት።
የውስጥ ጠላቷ ግን ሊያንበረክካት ይችላል። የውጭ ጠላት በየሆቴሉ ተደብቆ የቅኝት አገዛዙን የሚያስፈጽመው ቁጥሩ ብዙ ነው። ማንንም ሊያታልል በሚችለው ዘዴው ከሚዘርፈው ሰፊ ሀብት ቆንጭቦ የማይጸየፉት ነፍስ መግዥ ምጽዋት እየሰጠ ኢትዮጵያን ኮልሾ ለመግዛት ችሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቅኝግዛት ረመጥ ወጥቶ በታላቅ ስልት የመሸጋገሪያ መንግሥት ከዚያም በኋላ ቋሚ መንግሥት ለማቋቋም ብቁ ነው። ብዙ ኃይል አለው። በሰላም ተባብሮ መኖርን ያውቅበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የአለም የመጀመሪያው ሪፕብሊክ መንግሥት ነበር፤ እንደተባለው። አሁን ደግሞ የመጀመሪያው ዲሞክራቲክ ሕዝብ መሆኑን እንደሚያሳይ ጥርጥር አይኖርም!
የመንግሥት ግልበጣዎች
ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ:-
ጀነራል መንግሥቱ ንዋይና ወንድሙ ግርማሜ ንዋይ ከአበሮቻቸው ጋር ያካሄዱት መፈንቅል መንግሥት፣ 1ኛ፣ ወቅታዊ መሆኑንና አለመሆኑን? 2ኛ፣ ዕንባ ብቻ አስረጨ ወይስ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ? በሚል የሚነሱትን ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ለመመርመር የዚህ ጽሑፍ አላማ አይደለም። ይህ ጽሑፍ የመንግሥት ግልበጣዎችን ሀሳብ ያነሳው፣ በነመንግሥቱ ንዋይና ከዚያም ቀጥሎ የተካሄዱት የመንግሥት መፈንቅሎች በውስጡ ንጹህ ትግል ወይስ በውጩ ኃይል ስውር ዕርዳታና ድጋፍ የተካሄዱትን መፈንቅሎች ለይቶ ለማቅረብ ነው። ይህን ማድረጉ ባገርና ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት እንዳይደርስ፣ የቅኝ አገዛዝ ስልት እንዳይመሰግ የትግሉን ጥራት ለማሳወቅ ነው።
በውጭ ድጋፍ የሚፈጸም የመንግሥት መፈንቅል፣ ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ ነው። ስለዚህ፣ ማናቸውም ውስጣዊ አካል ከሚፈጸመው መፈንቅለ መንግሥት እጅግ የተለየ አላማና ግብ ያለው ነው። በውጭ አካል ድጋፍ የሚፈጸመው መፍንቅለ መንግሥት ለብዝበዛና ለጥፋት የሚዳርግ ሲሆን፣ ፍጻሜውም ሀገርንና ሕዝቡን አቆርቁዞ፣ ሀብቱን በመበዝበዝ አድኽይቶ ለመግዛት ነው። እነ መንግሥቱና ግርማሜ ለውጩ ሴራ የሚመቹ አልነበሩም። የውጩ አፈንፋኝ ይህን በመረዳት ቶሎ ብሎ መፈንቅሉን ለማክሽፍ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል።
ኮለኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም:-
ኢትዮጵያ፣ ለራሷ፣ ለአህጉሩና ለአለም ሕዝብ የምትችለውንና አገልግሎት በመስጠት ተከብራ የምትኖርበትን በጎ ስራ እየሰራች ኖራለች። ዳሩ ግን፣ ለግል ጥቅም ኢትዮጵያን ከህሊውናዋ ውጭ የሆነ ስራ እንድትፈጽም የሚወሰውሷት ኃይሎች ነበሩ። ይህ ጉዳይ የዲፕሎማቲክ ግጭት ፈጥሮ፣ በተለመደው ዛቻና ማስፈራሪያ ቢደረግባትም፣ የዲፕሎማቲክ መፍትሄ ስላልነበረ፣ ኢትዮጵያ ችላ ብላ ቆየች። ስለዚህ፣ ትእዛዙን ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ የውጩ ኃይሎች፣ የንጉሡን አገዛዝ ለማውደም ዕቅድ አደረጉ። የኢትዮጵያ መንግሥትን መደምሰስ ማለት፣ ታሪኩን፣ ባህሉን እና ኃይማኖቱን ማጥፋት ስለሚሆን፣ ሊቆጣጠሩት በሚቻለው መንገድ ለማካሄድ የመደምሰሻ ዘመቻውን በሁለት መፈንቅለ መንግሥት እቅድ ሆነ። የ1ኛው ደረጃ ዘመቻ በኮለኔል መንግሥቱ ተፈጸመ። መንግሥቱ ኃ/ማርያምም ዋናው ምግባሩ ሀገር ጠባቂዎችን መሪዎቿን ሙልጭ አርጎ ማጥፋት ነበር። መንግስቱ ምግባሩን ካከናወነ በኋላ 2ኛው ደረጃ ተጀመረ። መንግሥቱን በደቡብ ሸፋፍነው ሲያወጡ፣ ወያኔ በሰሜን እያጎራ እንዲገባ አረጉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋው መልካም አስተዳደርና ሰላም ነበር።
የወያኔ አገዛዝ:-
የ1ኛው ደረጃ ጥፋት ፍጹም ስለነበር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ የሚወድምና የሚጠፋ ነገር አል ብሎ አልገመተም ነበር። የአንድ ሰው ነፍስ መጥፋት እጅግ አሰቃቂ እየሆነ በየሀገሩ ሲወሳ፣ ወያኔ የሚጨፈጭፈው ሕዝብ ግን ከአለም አይንና ጆሮ እንዳይሰማ ተደርጎ ቆየ። ወያኔን ‘አይዞህ የጋራ ጠላታችንን ነው’ የተባለ ይመስል፣ ግፉን በአማራው፣ በኦሮሞው፣ በአፋሩ፣ አንዋኩ፣ ወዘተ ኗሪውን እንደ ዜጋ ቀርቶ እንደ ሰው ሳይቆጥር እንደ ቅጠል አቃጠለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መስፍርት የማይገኝለት በደል ተፈጸመበት። ከትግራይ የፈለቀው ወያኔ ዙሮ ጠባሳውን እያየ ቂምበቀል ለመፈጸም የመጣ መሆኑን ይፋ አረገ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሪዎች ኋላም በታሪኩና በባህሉ ላይ የተነጣጠረ እንደሆነ ተረዳው። ወያኔም ጽዋ የሚከፍልበትን ግፍ እየሰራ ይገኛል። ወያኔ ጦርነት ኑሮው ይመስላል። አጥፍቶ መጥፋት የሚለው ቋንቋ አለ። አሳዛኙ ይህ መስዋዕትነት ሆኖ ይታያል። በኢትዮጵያኖች አስተሳሰብ አጥፍቶ መጥፋት የዘራፊ እና የሌባ ቋንቋ ነው። ሌባ መዝረፍ አላማው ሲሆን፣ ሲዘርፍ መገደል እንዳለ አምኖና ተቀብሎ ነው።
አዲሱ አለም፤ መንግሥታትና አሜሪካ:-
የአለም ሁኔታ በተለያየ መንገድ ምንጊዜም ይለዋወጣል። በአለም ላይ ትልቅ ሽሚያ አለ። ሽሚያው ሀብትን አስመልክቶ ነው። በገዛ ሀገራቸው ድሆቹ ከሚያረጉት ይልቅ የሀብታሞቹ ሽሚያ የባሰ ነው። ስለሆነም፣ ህገወጥ የሆነ ቅሚያና ዝርፊያ ተጨምሮበታል። በዚህ ትርምስ ያልተለዋወሰ ሀገር የለም። ዲሞክራሲ የሚባለው የአስተዳደር ሕግና ደንብ የአለም መሪዎች ሊያከብሩትና ሊፈጽሙት ያልቻሉት ከባድ ሰነስርዐት ሆኖባቸዋል። ‘አትዋሽ፣ አትስረቅ፣ ወዘተ” የሚባሉት የህግ መሰረቶች፣ ከመግደል የባሱ ሀገር እጥፊ ወንጀል ሆነዋል።
ጀነራል ፓወል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሪ የነበሩት፣ ረዳታቸውን “ዕውነቱን ንገረኝ። የተባበሩት መንግሥታት ፊት ቃሌን ልሰጥ ነው” ነገር ሲሉት፣ ያንኑ ውሸት ደጋግሞ አረጋገጠላቸው። በሰጡት ሀሰት ቃል፣ መስፈርት የሌለው ንብረት፣ ህይወትና ሀገር ወድሟል። በቅርቡ አምባሳደር ሄርማን ኮሆን በአንድ ውይይት ላይ፣ “ፕረዚዳንት ኦባማ በምን ሂሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት ዲሞክራታዊ ነው አሉ?”መሳይ ጥያቄ ሲጠየቁ፣ የሰጡት መልስ፣ “የተሰጣቸው ማስረጃ የተሳሳተ በመሆኑ ነው” ብለዋል። አምባሳደር ኮሆን እሳቸውም፣ “እኔ የማደርገውን አለቃየ አያውቅም” ብለዋል ነበር። ፍኖተሰላም (ኢሕአፓ)በቅርቡ ባወጣው ቪዲዮ፣ አምባሳደር ሱዛን ራይስ ስለኢትዮጵያ ምርጫ ለፕረስ መግለጫ ሲሰጡ፣ ገዡ ፓርቲ በ“መቶ ፐርሰንት” አሸንፏል አሉ። “መቶ ፐርሰንት?” ብሎ ለተገረመው ሲመልሱ ትን እስኪላቸው እየሳቁ ‘አዎ መቶ ፐርሰንት!’ በማለት አረጋገጡ። ይህ መሳቂያና መሳለቂያ የሆነው ውሸት፣ ብዙ ደም እንዲፈስ፣ ንብረት እንዲወድም አድርጓል።
መሪዎች በያሉበት ከንቱ ሆነዋል። በየሀገሩ ያለው ሕዝብ ለከፍተኛ ስልጣን የመረጠው ሰው ሕዝብ አገልጋይ መሪ ለመሆን ብቁ አልሆን እያለ ብዙ ሀገሮች ከብጥብጥ ውስጥ ገብተዋል። አሜሪካ ምሳሌ መሆን ፈጽሞ የማይገባት ሀገር ስትሆን፣ አሁን ምሳሌ ሆናለች። ድሮ የረፕብሊካኑን እጩ ሲያሸንፍ፣ ተሸናፊው የዲሞክራቱ እጩ፣ አሸናፊውን አድንቆ፣ መሸነፉን ተቀብሎ ተጨባብጠው ይለያያሉ። ይህ አሜሪካኖች የሚኮሩበት ባህል ይባል ነበር። ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ እየተባለ ለሳምንት ይወሳ ነበር። ይህ ባህል ተቀይሯል። ተመልሶ ላይመጣም ይችላል። ምርጫውን ያልተቀበለው ሕዝብ በማግስቱ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል።
የፕረዚዳንት ትራምፕ መመረጥ የተቃወመው አሁንም ቁጭቱ አልበረደለትም። ከስልጣን ለማስነሳት የሚደረግ ጥረት አለ። በአንጻሩ ደግሞ፣ ፕረዚዳንት ትራምፕን አጥብቀው የሚደግፉ አሉ። እጩ የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን ቢመረጡ እሳቸውንስ ምን ችግር ይገጥማቸው ነበር ማሰላሰል ይከጀላል። ሀሳቡ ሁለት ግሜት ውስጥ ይከታል። አንዱ ጥንቅ ትራምፕ በሰው አእምሮ ያገባው ሀሳብ ነው። ካልተመረጥኩ ምርጫው ተሰአልቧል ማለት ነው ያለው ነው። ቢሸነፍ ኖሮ፣ አማኙና ደጋፊው ማቆሚያው የማይታውቅ ሁከት ይፈጠር ነበር ማለት ነው።
ሁለተኛው ግምት፣ የክሊንተን ደጋፊ በተለይ ስታብሊሽሜንቱ (ባላባቱ) ትራምፕን አንድ እብድ አስቆጥረው ያስገልሉት ይሆን ነበር። ያም ይኽም ጤና ግምት አይደለም። ለማናቸውም በአሜሪካ ምርጫ የቆሰቆሰው ቀውስ በቀላሉ የሚበርድ አይደልም። በዚያ ላይ በቅርብ በሆነው አሜሪካን ሌላ ችግር ውስጥ ገብታለች። ፕረዚዳንት ትራምፕ ራሱ ወይም አማካሪው የአሜሪካንን ሕዝብ በረቀቀ ጥበብ ከብጥብጥ እንዲወጣ አድረዋል ተብሎ ሊገመት ይችላል።
የአሜሪካ ተፈራራቂና ተሰነጣጣቂ ፖለሲ:-
ፕረዚዳንት ኦባማ ስለ ፕረዚዳንት ትራምፕ ያሳሰባቸውን ሲናገሩ፥ “ትራምፕን አቅልላችሁ አትገምቱት” (Don’t underestimate Trump) ብለዋል። ፕረዚዳንት ትራምፕ ብዙ ሰው የማይዋጥለት ሀሳብና ፖለሲ እያቀረቡ ይገኛሉ። አበጀህ የሚሏቸው ብዙ ናቸው። በግራና በቀኝ የተሰለፈው ተቀናቃኝ የሚስማማውን ፖለሲ ፈጽሞ አላገኘም። ሕዝቡ በሁለት ስለተከፈለ የሚያወጡት ፖለሲ አንዱን እንጂ ሁለቱንም ፈጽሞ የሚያረካ አልሆነም። ይህ በቀላሉ የማይታይ ከባድ ችግር ነው። በዚህ አንጻር፣ አሚሪካ ምን መፍትሔ ታገኛለች፣ ካላገኘችስ ወደየት አቅጣጫ ታመራለች የሚለው ፍራቻ እየከረረ ሄዷል።
ባስተዳደሩ ያልተደሰተው፣ ኃብታሙም ድሀውም በየጊቢው እኩል ይንጫጫል። ትራምፕ እጅግ ብልጥ ወይም ተላላ መሆናቸው ገና ተለይቶ አይታወቅም። እስራኤልን አስመልክቶ ያደረጉት ውሳኔ ብዙ ምርምር ያስፈልገዋል። ውሳኔአቸው አለምን ለሁለት እንደሚከፍል ሳያውቁ አረጉት ለማለት አይቻልም። የአሜሪካን ሕዝብና እሳቸውም ከገቡበት ለመውጣት ታስቦ የሆነ ይመስላል። የእስራኤልን ድርጊት መደገፋቸው የሕዝብ ትኩረት ወደ ውጭ እንዲሆን የተደረገ ዘዴ መስሏል። እስራኤል ትራምፕ የሷን ውሳኔ እንዲደግፉ ወስውሳቸው ነው የሚል ግምትም አለ። በዚህ ላይ የተቀዋሚውና የደጋፊው ብዛት አይታወቅም። የእስራኤል ወገኖች የአረቡም ደጋፊዎች ብዙ ሀይል አላቸው። ግን አሜሪካ በዚህ ላይ የቆየ ፖሊሲ አላት።
ትራምፕ ያንን ፖሊስ አፍርሰዋል። አብዘኸኛው የአለም መንግሥታት ውሳኔውን ተቃውመዋል። ከአረቡ ቡድን ጋር በጥቅም የተወሳሰቡ የአውሮፓ፣ ኤዥያ፣ ደቡብ አሜሪክና አፍሪካ አገሮችም አሉ። መንግሥቶች የራሳቸውን ጥቅም ትተው የትራምፕን ፖሊሲ ደግፊ ሁኑ ቢባሉ፣ የሚጎድልባቸውን ጥቅም አመዛዝነው ይመርጣሉ። በንዚን የመኖር ወይም መጥፋት ጉዳይ ነው። ሚልዮን አህያና ግመል ቢኖረውም አይኖርም! ይህ ችግር እየታወቀ፣ ፕረዚዳንት ትራምፕ የወሰዱት ርምጃ የራሳቸውን ጭንቅ መውጫ አስመስሎታል። ይህ እና የኮሪያው ችግር የውስጡን ጣጣ በሚገባ ሽፍኖታል። በትራምፕ ድርጊት ላይ ሌላ ሀሳብ ተጠንጥኗል። እምቢተኛዋ እስራኤል ከአለም ያላትን ችግር እንድትገነዝብ ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሪ አለ። እስራኤል ከአለም መንግሥታት የሚገጥማትን ችግር በእርግጥ እንድታውቅ ለማድረግ ከሆነ፣ አሁን አወቀች እናም ተለየች ማለት ነው። ይህ መጥፎ ስም ነው። የሚደረገው በቀል አይታወቅም እንጂ፣ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ እጁን ያወጣውንና ያላወጣውን ኃብታም በተለይ ድሀ መንግሥት ስም በጥቁር መዝገባቸው ሲመዘግቡ አምሽተዋል።
የፕረዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ አለም ስለ አሜሪካ የነበረውን ክብር ክብደትና ዝቅ አደረገው ተብሏል። ይህን ሀሳብ የሚያፈርስ ሀሳብም አለ። ኢስራኤል በወሰደችው ርምጃ ሰፊ ቅዋሜ እንደሚነሳባት ተገንዝባ፣ አሜሪካ በዚህ ችግሯ ወቅት በጎኗ እንዲቆም የተሳካ የዲፕሎማቲክ ብልህ ርምጃ ነው ብለው ያመኑ አሉ። ትራም የእስራኤል ችግር የአሜሪካ ችግር ነው በማለት የታወቀውን ዕውቅ አረገው። የእስራኤልን እና የአሜሪካን ዝምድና አቅርቦ አራራቀው የሚሉም አሉ።
ለማናቸውም የፕረዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ በቀላሉ የማይፈታ የፖለቲካ ሸለቆ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። ከዚያም ይበልጥ፣ ልዩነቱ እየሰፋ አለም ከምን ደረጃ እንደሚደርስ የሚታወቅ አይደለም። የአለም መንግሥታት ወይም የአሜሪካ መንግሥት ለጢሱ ማናቸው ቀዳዳ እንደሚሰጡ አይታወቅም። አሜሪካ ጥቅሙ ከተጓደለበት ውሳኔውን ያበርድ ይሆናል። ችግሩ ሌላ የፕረዚዳንት ምርጫ እስኪሆን ድረስ መጠበቁ እና መቆየቱ ነው። ፖለሲውን መቀየር ወይም መጨበጥ በዚህም በዚያ አከፋፋይ ነው። አሜሪካ አይቶት የማያውቀው የፖለቲካ እሳት ውስጥ ነው።
ፕረዚዳንት ትራምፕ ቀጥለው የሚወስዱት እርምጃ ይኖራል። በእርግጥ ሊሆን የሚችለው አንዱ፣ የትራምፕን ፖሊሲ ያልደገፉት በምጽዋት የሚኖሩ ሀገሮች አበል ማቋረጥ ነው። ድሆቹ አገሮች አማራጭ መፈለግ ግዴታቸው ይሆናል። አረቦችም በአጸፌታ ፖሊሲውን ለተቃወሙ በጎ ለማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ይህ ሁሉ ግብግብ ወዴት እንደሚያመራ አይታወቅም። በዚሁ ጎራ ክፍፍል ነገሩ ይበርድ ይሆናል። ከዚህ ውጥንቅጥ ፖለቲካ ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ዕድል ምን እንደሚሆን ለመመርመር ሲባል የአለም ፖለቲካ ማእበል ማወቅ አስፈላጊ ስለሆነ፣ የአለም ፖለቲካ ውጣ ውረድ ችግር በመጠኑ ተጠቁሟል። በአንጻሩ የኢትዮጵያን አለኝታ ሊታወቅና ሊለይ ይቻላል።
የኢትዮጵያ አዲስ ዘመን
የውጭ መንግሥታት ድጋፍ:-
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት ትልቅ የፖለሲ ለውጥ በማድረግ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰው መብትን አስመልክቶ በአገዛዙ ላይ የተሰማውን ዝቅተኛ አስተያየት ገልጿል። የኢትዮጵያ ገዢ ክፍል፣ መልእክቱ ምን ማለት እንደሆነ አይገባው ይሆናል። ከገባው ግን በዕርግጥ ይተራመሳል። ወይኔ መሪ የሚወልድ ቅጽ ወይም የስልጣን ‘ፒራሚድ’የሆነውን አቋቋም አጥፍቷል። የሀገሪቱ አመራር ስልጣን በቅርጭ እንዲሆን ተወስኗል። በቅርቡ ባደረጉት ስብሰባ ታላቅ የፍ/ቤት ችሎት ሆኖ ታይቷል። ሕግና ፖሊስ ቢኖር ከዚይ የነበሩት የሰጡት እርስ-በርስ የወንደል ስራ ክስ ምስክር ሆኖ ታፍሰው እስር ቤት መታጎር ይገባቸው ነበር። የሰጡት ምስክርነት ለያንዳንዱ ክስ መመስረቻና መወንጀልያ በቂ ማስረጃ ነበር። የእድሜ ልክ እስራት የሚገባቸው ስልጣን ላይ እንዲቀመጡ ተደርጎ ስብሰባቸው አልቋል።
“ቅዱስ ደም አፍሰን ያያዝነውን ስልጣን ማንም ሊቀማን አይችልም፤ እስከ መጨረሻ ደም ጠብታ እንዋጋታለን።”“ኦሮሞ ምን ይፈልጋል? ዲሞክራሲ ሰጥተነዋል። እማራ ቢያጠፉት ነገ ተመልሶ ችብ የሚል፣ የስልጣን ጥማት ያለው ለወያኔ ትልቅ ጦስ ነው።
ቀጥቅጠን መቶ አመት እንገዛዋለን።” ወያኔዎች በተፈጥሮ ሁሉ የሚገኘው በጦር፣ የሚስተካከለውም በጦር እንደሆነ ያምናሉ። ከላይ የተበመረዳት የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት እጅግ አሳሳቢ ማስጠንቀቂያ ልኳል። ዳሩ ግን፣ ወያኔ ደጋፊ ሀገሮች አለቆች አለው። “ዝም በሏቸው፣ እናንተን የሚያሳስባችሁ ሁኔታ አይኖርም በማለት” ጥፋት ተግባራቸውን ግድያቸውን እንዲቀጥሉ የሚያደርጉ ይኖራሉ። ፈጅተው በተራቸው ቢተላለቁ ደንታቸው አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብም በበኩሉ ያገኘውን ተስፋ ይዞ ትግሉን ይቀጥላል። ኢትዮጵያኖች የተባበሩት መንግሥታት የሰጧቸውን ድጋፍ ማሰራጨትና ማሳወቅ አለባቸው። ለመንግሥታት ኤምባሲዎች፣ ለአሜሪካ ኮንግረስና ለሚድያ ማሰራጨት አለባቸው።
የኢትዮጵያኖች ሚና:-
በስያትል የተቋቋመ የኢትዮጵያኖች ግብረኃይል አቻምና አንድ ትልቅ ስብሰባ አድርጎ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲናገሩ ከተጋበዙት መሀል፣ አንዱ የተከበሩ የኦሮሞው ተወላጅ ሸህ መሀመድ ነበሩ። በሚማርከው ንግግራቸው አድማጩ በአድንቆት ይቀመጥ ይነሳ ነበር። ከፊሉን ቆሞ በማጨብጨብ አሳልፎታል። ምንጊዜም የማይረሳው ስለወገኖቻቸው የሚያውቁት ምስክርነት ነበር’ ኣንዲህ ሲሉ ገለጹት፣ “እኔ ሙሉ ልብስ፣ ጫማ፣ ሰዐት ነበረኝ። የወትሮ ልብሴ ነው። በአጋጣሚ ወደ አማራ ሀገር ወደተባለው ሂድኩ። በመንደሩና በገጠሩ አለፍኩ። የጠበቁት በልብሱ ያንሸባረቀ ሕዝብ ነበር። ያተረዳሁት፣ ጫማ ትልቅ ብርቅ መሆኑን ነው። ሰዐት በእጄ ካሰርኩ ዘመን አልፏል። በሄድኩበት ሁሉ አንድ ሰው ሰዐት አድርጎ አላየሁም። በድህነቱ ከልቤ በጣም አዘንኩ። አለመግባባትን ባገራችን ተስፋፍቷል። ይኼንን ሁኔታ ለሌላው ብነግረው አይቀበልም። እባካችሁ እንግባባ፣ አብረን እንስራ!የሚያራርቁንን ጠላቶች አንስማ!” ይህ ጸሐፊ ይህንን ንግግር በብዙ ድረገጾች እንዲታተም አድርጎ ነበር። መልዕክቱ ደርሶ የብዙ ኢትዮጵያኖችን ልብ እንደነካ አያጠራጥርም። ወያኔም ወዲያውኑ ሲሜቱን ገልጿል፣ “ነጻነታቸውን ብንሰጣቸው ወደ ነበሩበት ሊመለሱ ፈለጉ!” በየከተማው ያሉ ግብረኃይሎች ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸም አለባቸው። ወያኔ የነዛው ታሪክ እኒህን ታላላቅ ጎሳዎችን ለመለያየትና ጥላቻን ለማሰራጨት ነው። የተነዛውን ጥላቻ ኢትዮጵያኖች ማውደም አለባቸው። ደምህ ደሜ!ይበል።
የድርጅቶች ሚና:-
ብዙዎቹ ድርጅቶች ለትብብርና አብሮ ለመስራት መልካምና ቀና መንፈስ ያላቸው ናቸው። አንዳንድ አስቸጋሪ መሪና ግለሰብ እያጋጠማቸው ብዙዎቹ ተቀላቅሎ ውጤተቢስ ከመሆን መገለልን መርጠው የተቆጠቡ አሉ። እስከ አሁን ድረስ ሁሉም ድርጅት የየግሉን ፍሬአማና ውጤተቢስ ሚና ሲያካሂድ ቆይቷል። በዕርግጥ ሚኤሶንና ኢሕአፓን ቀስተደመና (ግንቦት 7) ወዘተ የተፈጠሩበት የፖለቲካ ስልት ጣሉ ማለት አይቻልም። አዲሲቱን ኢትዮጵያዊ ለመገንባት ማንንም ድርጅት እንዳልነበርክ ሁን ማለትም ተገቢ አይደለም። ዳሩ ግን፣ አዲሲቱን የኢትዮጵያን መንግሥት ለማቋቋምና ለመመስረት የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋጽኦ ተፈላጊነት ባዶ ሆኗ። ምክንያቱ ከዚህ ባጭሩ ይገለጻል፣ ግን በግላቸው መርምረው እጅግ የላቀ አስተዋጽኦ የሚሰጡበትን ምግባር ቦታውን መያዝ አለባቸው። ይህም ባጭሩ ይገለጻል። ዋናው ፍሬ ነገር፡ የፉክክሩ፣ የመቆራቆዙ፣ የመከሻሸፉ ዘምን አለቀ ደቀቀ የሚባልበት ወቅት ላይ ተገብቷል። የሚፈጠሩት
1. የሽግግር መንግሥት አስባሳቢ፣
2. የሽግግር መንግሥት፣
3. የቋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሆንት አካሎች ለመፍጠር የሚፈጠሩት አካሎች አንድም የፖለቲካ ፍልስፍና መወያያ መድረክ ስለማይሆን በግለስብ እንጂ በድርጅትና ክምችት የሚካሄድ አንድም አንቀጽ ስለማይኖር ነው።
ስለዚህ የፖለቲካ ድርጂቶች የሽግግሩ ምግባር ሲጀመር በማግስቱ ድርጂቶቻቸውን ሌል ገጽ ባለው ምግባር መቀየር ይኖርባቸዋል። እንደተጠቀሰው፣ የሽግግሩ መንግሥት በሶስት ደረጃ የሚፈጸም ነው። አሰባሳቢ ድርጅት የሽግግሩን መንግሥት ለመምርጥ ይመሰረታል። የሽግግሩ መንግሥት ድርጂት በተራው የኢትዮጵያን ቋሚ መንግሥት ያቋቁማል። ቋሚው መንግሥት የወደፊቱን የአሰተዳደር ስርዓት አማራጭ አጥንቶ ለህዝብ እንዲመረጥ ያደርጋል። ይህን ለመቀዳጀት የግለሰብን ትብብር፣ ዕውቀት፣ ልምድና ጥበብ የሚሻ እንጂ የፓርቲን ፍልስፍና እና ሂደት ፈጽሞ አይጠቀምም። ሆኖም ድርጅቶች ለዚህ ምግባር ሰራዊታቸው በግለሰብ እየገባ ትልቅ ስራ እንዲያከናውን ማድረግ ይገባቸዋል። የዚህም ምግባር ውጤት በመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማና ግብ ነው። ስለዚህ አላማቸው በስብስብ ተፈጸመ ማለት ነው።
ሰብሳቢና አሰባሳቢ ድርጅት:-
ብዙሃን በታላቅ ስሜት ተነሳስተው የሚጀምሩት ምግባር ነው። ሆኖም ትልቅ ስልትና ልምድን ይጠይቃል። ያገር ጉዳይ ስለሆነም ሰፊ ልቦና እና ጥበብ ያስፈልገዋል። የተለመደ ስላልሆነ ብዙ አዳዲስ ጥናት ይፈልጋል። ለዚህ አሰባሳቢ ስራ የተሻለና አግባብ ሆኖ የሚታየው ሸንጎ ተብሎ የሚታወቀው ድርጅት ወይም በተመሳሳይ አቋም የተመሰረቱት ይሆናሉ። ስም እና ምግባራቸውን ቀይረው የሽግግሩ መንግሥት ሰብሳቢና አሰባሳቢ ሆነው ቢቀዳጁ እጅግ በጣም ውጤታማ ይሆናል። አሰባሳቢው ድርጅት በአዋጅ ሲመሰረት፣ መላው የተቀዋሚ የፖለቲካ ኃይል አቋምና ህልውና ውድቅ ይሆናል።
በሽግግሩ ወቅት የሚያደርጉት የፖለቲካ ሚና አይኖርም። የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነክ የሆኑ ድርጅቶች አመሰረታታቸውን ወደ ስነ-ምርምር ምግባር (Think-Tank) እደሚባለው ድርጅት አይነት መለወጥ ጠቃሚ ይሆናል። በስራ ያለው የሸንጎ ድርጅት በራሱ መነሳሳት አሰባሳቢ ድርጅቱን ሊፈጥር ይችላል። አሰባሳቢው ድርጅት፣ መነሽውና መድረሻው የሽግግሩን መንግሥት ማቋቋም ነው።
እንደገና እያንዳንዱ ግለሰብ ከሽግግሩ መንግሥት ገብቶ በሌላ ሚና አገልግሎት ሊያበረክት ይችላል። የድርጅቱ ስም የሽግግር መንግሥት አሰባሳቢ ይሆናል። አስባሳቢው በህግ የሚታወቅና የድርጅት ሕጋዊ አቋም ያለው ይሆናል። እንደተቋቋመ አላማውን፣ ውስጣዊ ህጉንና ደንቡንና አዘጋጅቶ ይፋ ያረጋል። በጊዜያዊ ወይም በቋሚነት የሚያገለግሉ ባለስልጣን በአባሉ ይመረጣሉ። የአሰባሳቢው ድርጅቲ ዋና ምግባሩ አባሎችን፣ ደጋፊ ግለሰቦችንና ማሰባሰብ ሲሆን የወደፊት የሽግግሩ መንግሥት መስራቾች ከዚሁ አካል የሚወጡ ይሆናሉ። ጥንቃቄ የሚደረግበት ትልቅ መዝገብ ይፈጥራል።
የኢትዮጵያን የሽግግር መንግሥት መስራች አባል ለመሆን የማይጓጓ ወገንና ዜጋ ስለማይኖር እጅግ ብዙ አባል እንደሚመዘገብ መገመት ይቻላል። በተጨማሪ፣ አሰባሳቤው ከግለሰቦችና ከድርጅቶች ምክርና ሀሳብ ለማገኘት እንዲችል ግንኙነት ይፈጥራል። መስራች አባሎች በናት ሀገርና በመላው ዓለም ያሉ ወገኖች እያንዳንዳቸው አጭር የግል ታሪካቸውን እየሰጡ መመዝገብ ይጀምራሉ። ይህ ታሪካዊ መዝገብ በክብር ይጠበቃል። የሽግግሩን መንግሥት የሚመሰርቱት ቁጥራቸው ምን ያህል ሲደርስ እንደሆነ የአሰባሳቢው ድርጅት የሚወስነው ይሆናል። ግን ሲያንስ ከመቶ ሺህ የማያንስ ቢሆን ታሪካዊ ይሆናል። እኒህ አዲሲቱን ኢትዮጵያ መስራቾች ይሆናሉ። እንቁ ታሪክ ነው።
የስራ ማካሄጃ ወጭ:-
የማናቸውም የድርጅት ስራ የተለያየ ብዙ ወጭ ይኖረዋል። የአሰባሳቢውን ድርጅት ሰፊ ስራ ይጠብቀዋል። ወጩም በዚያ ልክ ነው። እጅግ አስፈላጊ የሀገር ጉዳይ ስለሆነ፣ በገንዘብ እጦት ምክንያት ሊጓደሉ የማይችሉ ብዙ ወቅታዊ ቁምነገሮች ይኖራሉ። አሰባሳቢው ድርጅት ምንም እንኳን የበጎ ፈቃደኞች አስተዋጽዖ የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ አንዳንድ ስራወች ያለክፍያ በሚገባ ሊጠናቀቁ አይችሉም። ስለዚህ አሰባሳቢው ድርጅት ከአባሎች፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ለጋሾች ዕርዳታ መጠየቅ ይገባዋል። ለዚህ የተቀደሰ ታላቅ ምግባር በራሳቸውና በድርጅታቸው ስም ዕርዳታ እንዲያደርጉ አሰባሳቢው ድርጂት መጣር ይገባዋል።
ለዚህም ራሱን የቻለ በዚህ ምግባር ላይ የሚሰማራ አንድ ክፍል ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከመንግሥታትና ከዓለም ድርጅቶች የማተሪያል ድጋፍ ለመስጠት የሚችለው እየተጠና ሊጠይቅ ይገባል። አሰባሳቢው ድርጂት በየትኛውም ሀገር ካሉ ኢትዮጵያ ድርጅቶች እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ አለበት። ይህ ትልቅ ዋጋ አለው። ስራውና ኃላፊነቱን ከፍ ያረግዋል። ግንኙነት ሲፈጥርና እርዳታ ለመጠየቅ ሲሞክር፣ የድርጅቶች እውቅና እንደ ምስክር ሆኖ ያገለግላ። የአሰባሳቢው ጽህፈት ቤት አብዘኸኛው ባለሥልጣን በሚገኙበት ከተማ ቢሆን ይመረጣል። ግን ይህ ግዳጅ ሆኖ አስፈላጊ ሰዎችን እንዳያግድ ጽ/ቤቱ በሚያመች አካባቢ እንዲሆን ድርጅቱ ይወስናል። አብዘኸኛው ስራ በኤልክትሮኒክስ (Internate)ግንኙነት የሚፈጸም ነው። ጽ/ቤቱ በልገሳ የሚቋቋም ሊሆን ይችላል። ካልሆነ አባሎችና ድርጅቶች ለዚህ የሚሆን ወጭ ድርጅቱ አሳስቦ ወጭው እንዲሸፈን ይደረጋል። አሰባሳቢው ድርጅት ስምና ዕውቅና ታማኝነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ባለስልጣኖች የሚመስላቸውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የሽግግሩ መንግሥት:-
የሽግግሩ አሰባሳቢ ድርጅት በየትም ሀገር ተቀናጅቶ ሲጨርስ ጊዜው ሲያመች ወደኢትይጵያ ይተላለፋል። ዕቅዱ በስራ የሚውለው በኢትዮጵያ ምድር ይሆናል። የሽግግሩ አሰባሳቢ እንዲሁ በኢትዮጵያ እኩያ ድርጅት ይኖራል። በኢትዮጵያ የሚገኘው አሰባሳቢ ከውጭ የተፈጸመውን አጣምሮ በአባሉ ምርጫ ሰፊ የሽግግሩ መንግሥት አካል ይመርጣል። የፖለቲካ መሪዎችና ግለሰቦች በቋሚው መንግሥት የሚወዳደሩ ከሆነ ከሽግግሩ መንግሥት ሚና ራሳቸውን ያስገልላሉ። የመጀመሪያው ቋሚ መንግሥት አመሰራረት ላይ ካልተሳተፉ የሽግግሩን መንግሥት ከሚመርጠው አካል በግለሰብነት ሊቀላቀሉና ሊያገለግሉ ይችላሉ። የመጀመሪያው ቋሚ መንግሥት ከተመረጠ በኋላ የሽግግሩ መንግሥት ሚና በአዋጅ መፈጸሙ ተነግሮ ስራው ያልቃል።
ቋሚው መንግሥት:-
ቋሚው መንግት በሽግግሩ መንግሥት አስፈጻሚነ ይቋቋማል። ቋሚ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ ከተቋቋመ በኋላ፣ የሽግግሩ መንግሥት ሚና በአዋጅ ይፈጸማል። ቋሚው መንግሥት ሰፊ ስራ ይኖረዋል። አንድ የሊቃውንትና የሀገር አባቶችና እናቶች አካል ይፈጥራል። ይህ አካል፣ በባህል፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚና በፖለቲካ የአስተዳደሩ ግዛትና ሀገራዊ ዕውቀት ያላቸው፣ እንዲሁም ስለአለም ሁኔታ በሰፊው የሚያውቁ ግለሰቦችን ያዋቀረ ይሆናል። ዋናው ምግባራቸው አስፈላጊና ጠቃሚ፣ በህዝቡ ተፈላጊ የሆነውን የሀገር ማስተዳደሪያን፣ የፌደራሊዝም ወይም ሌላ ስልቶችን አጥንተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ለምርጫ ለማቅረብ ይሆናል። ይህ አካል ሰፊ ጥናት ከማድረጉም ሌላ፣ በየአህጉሩና ሀገሮች እየዞረ የአስተዳደርን አይነትና አሰራር ሁኔታ ይገነዘባል። አማካሪ አዋቂዎችን ያነጋግራል። በዚህ አይነት ጥናት የሀገሪቱ አማራጭ የአሰተዳደር ምርጫ ለህዝብ ይገለጻል። በትምህርትም አይነት ይቀርብለታል። ለጥያቄው መልስ የሚሰጡ ይመደባሉ። ከዚህ ረጂም ትምህርት በኋላ ሕዝብ የሚመስለውንና የሚወደን አስተዳደር ይመርጣል። ቋሚው መንግሥት አዲሱን የኢትዮጵያ አስተዳደርና ሕገመንግሥት በስራ ያውላል።
እንቅፋቶችና መሰናክሎች:-
ይህ ዕቅድ በስራ እንዲውል ሲደረግ፣ ብዙ እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ዕቅድ እጅግ የተከበረ የሀገር ጉዳይ ስለሆነ ያንን በመፍራት በቀላሉ የማይደፈር ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ይህ ዕቅድ የነሱን የብዙ አመት ድካም የሚያፈርስ መስሎ ስለሚታያቸው ደስ ላይላቸው ይችላል። ዳሩ ግን፣ በወያኔ ጊዜ በኢትዮጵያ የፓርቲ መሳተፍ የሚታለም አልሆነም። ይህ ዕቅድ ፓርቲዎች ሊያደርጉ ይፈልጉት የነበረውን በሌላ መንገድ አስፈጸሙ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ፍጻሜ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሚና አገባደደ ማለት ነው። ስለሆነም እንዲሳካ የነሱ ሰፊ ትብብርን ይጠይቃል። ወያኔ ይህን ዕቅድ የዘመኑ ማለቂያ አርጎ እንደሚያየው ጥርጥር አይኖርም። በሌላ በኩል ከዚህ የበለጠ የሰላም ለውጥ እንደማይግኝ ተረድቶ ይለወጥ ይሆናል! ሆኖም ሌላው ልቡ ደግሞ ዕቅዱን ለማናጋት ከፍተኛ ጥረት ላድረግ ያስብ ይሆናል። ይህን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቆአ ማድረግ ነው።
የብዙሐን ዚና ማሰራጫ:-
የብዙሐን ዜና ማሰራጫ ለውጥን አስመልክቶ አስፈላጊ ድርጊቶችን ሌት ከቀን እያካሄዱ ናቸው። በዚህ ዕቅድ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ለሰሚና አንባቢዎቻችው እንደሚወያዩበት በማድረግ ብዙ ሀሳብ ተቀላቅሎበት የላቀ እቅድ እንደሚያደርጉት የጠበቀ ተስፋ አለ። እቅዱ በውጤቱ እያንዳንዱ ሰውና ድርጅት የኔ እቅድ ብሎ እንዲያስበው ማድረግ ዋናው ቁምነገር ነው። ስለዚህ፣ ወገኖች በፓልቶክ፣ ሬድዮና ፌስቡክና አዳራሹ ሁሉ ልዩ ገጽታ ሰጥተውት በሰፊው እንደሚወያዩበት ከፍተኛ እምነት አለ። ከነዚህ ውይይቶች የሚገኘው ፍሬነገር እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። ብዙ ነገርን ለማስተካከል ይረዳል። ያገር ጉዳይ ስለሆነ የተለያዩ ሀሳቦች ተጨምቀው ለዕቅዱ ስጋና አጥንት ሆነው እንዲቀርቡ ያደርጋል።
የተቀዋሚዎች-ተቃዋሚዎች:-
የተቀዋሚዎች-ተቃዋሚዎች ይኖራሉ/አሉ። ይህንንም ዕቅድ ሊጻረሩ ይችላሉ። እነሱ የራሳቸው ዕቅድ እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም። ይህ ዕቅድ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንጂ ያለውን ስርዐት ለማስተካከልና ለማቃናት አይደለም። የማይስተካከለው ባህሉ፣ ታሪኩና ኃይማኖቱ ነው። የተቀዋሚዎች-ተቃዋሚዎች የሚባሉት ከወያኔ የተገለሉት፣ በተቃዋሚ ስም እንዲታወቁ የሚፈልጉት ናቸው። ከተቀዋሚው ህሊና ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተስማምተው የሚገኙ አይመስሉም። በመሪ ለውጥ ያምናሉ። ግን፣ የስርዓቱን መለወጥ ፈጽሞ አይቀበሉም። እንደ መሐል ሰፋሪ ያለ ባህሪ ይመስላል።
ለኢትዮጵያኖች ደግሞ፣ ስርዐቱ እንጂ ከበደና በርሄ ችግር አይደሉም። የተቀዋሚዎች-ተቃዋሚዎች ችግር ከበደና በርሄ ናቸው። ወያኔዎች ይወገዱ። ክልሉ ግን እንዳለ ይቆይ። በቋንቋን ፈሊጥ የተመሰረተው ፌደሬል አሰተዳደር ይስማማናል ይላሉ። ነገሩ “አልሸሹም ዘውር አሉ” ነው። ይህ ከወያኔ አካል ውጭ ሆኖ የወያኔን ርዐይ የሚመክት ነው ከአዜብ መስፍን ያላነሰ። የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን የወያኔ ቅርስ (ሌጋሲ)የሚሉትን ሀሳብ ለማጥፋት የተነሳ ነው። የትጋርይ ሕዝብ የተቀዋሚዎች-ተቃዋሚዎች አደገኛ አቋም ተገንዝበው፣ ከሰፊው ወገን ጎን በመቆም አዲሲቱን ኢትዮጵያ እንዲገነቡ መዘጋጀት አለባቸው።
መደምደሚያ:-
የቀረበው ዕቅድ እንደ አንድ ዕቅድ ሆኖ መታየት አለበት። ስለዚህ ሌላ አማራጭ ዕቅድ ወይም ይህ ተሻሽሎ ታላቅ እቅድ ለማፍለቅ እንደሚቻል መገመት ተገቢ ነው። ዋናው ቁምነገር ግን፣ ችግርንና ቀውስን አስወግዶ በዘዴ ወያኔን ትጥቁን ማስወለቅ ነው። ለውጥ እንዳይመጣ ተብሎ እጅግ የተወሳሰበ ድርጊት በስራ ውሏል። ያ ስረአት ከተነካ፣ ብጥብጥና ዕልቂት እንደሚሆን አባይ ጸሀይና ጓደኞቹ አሳስበዋል። የኢትዮጵይ ሕዝብ ሲነሳ እልቂቱ በነሱ በሌቦቹ እንጂ በኢትዮጵያ ወገኖች ላይ ሊሆን አይችልም።
የኢትዮጵያኖች ልቦና ከዚህ በኋላ ሰላም እንጂ ዕልቂት አያስብም። ይህ ዕቅድ ይህን በመገንዘብ የሰላም ለውጥ የሚፈጸምበትን መፍትሔ ይዞ ቀርቧል። ወያኔ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመዶለት፣ ለውጥ በሰላም እንዳይመጣ ብዙ የሽቦ አጥር እንዳዘጋጀ ታውቋል። ብዙ ወገን ይህን ውስብስብ ሁኔታ በማየት፤ ለውጥ እንዴት እንደሚመጣ ግራ በመጋባት ተስፋ ወደመቁረጥ ደረጃም የደረሰ አለ። ብስቅልቅል ሁኔታ አልፎ እንዴት የሰላም ለውጥ እንደሚመጣ ለማሳየት፣ከዚያም በተለያየ ፍራቻ ተውጦ ለሚጨነቀው፣ ይህ ዕቅድ የሚያረጋጋው ይሆናል። በይበልጥ ደግሞ፣ ተናቁረውና ራሳቸው የኢትዮጵያ ድሞክራሲ መሰናክል በሆኑት ፓርቲዎች ወገን ከእንግዲህ ወዲህ መጨነቅ የለበትም።
ማንም መንግሥት ከበጎ ሕዝብና ከጥሩ መንግሥት ጋር መስራት ዘለቄታ ጥቅም እንዳለው ይረዳል። የአሜሪካን መሪዎች የሚያሳስቱ ድብቅ ኃይሎች አሉ። ፕረዚዳንት ኦባማ ታላቅ መሪ ነበሩ፣ ግን በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ስህተት ድብቅ ኃይሎች አሳሳቷቸው። ኪስንጀር ኒክሰንን አሳስቷል። ኮሆንም እንዲሁ። ሂላሪ ክሊንተን በቤንጋዚ ባደረገችው ችልተኝነት የፕረዚዳንትነት ምርጫዋ አጥታለች። የአሜሪካ ፖለሲ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ፣ ተፈራራቂ ጉዳት በአሜሪካ ሕዝብ ላይ እያደረሱ ነው። በኮንግረስና በእስቴት ዲፓርትሜንት እየተውለበለቡ፣ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዳይመሰረት፣ ሰላምና ብልጽግና እንዳይሰፍን አሜሪካ ድጋፏን ለኢትዮጵያ እንዳትለግስ እነዚሁ የጥቅም ድብቅ ኃይሎች ያደረጉት መሰናክል ይህ ነው አይባልም።
እንደነ አቶ መስፍን መኮንን ያሉት ቆራጥ የኢትዮጵያ ልጆች የአሜሪካ ኮንግረስ አባሎችን በመማጸን የእድሜአቸውን አንድ ሶስተኛ ዘመን አሳልፈዋል። እንደነ ታማኝ በየነ ያለውም ስለወገኖቹ ስቃይ እንቅልፍ አልወስድህ ቢለው፣አቅሙ የሚችለውን ቅዋሜውን ለመግለጽ ሲል የኤምባሴ በር ድንበር ተላልፈሀል በመባል ቢከሰስም፣ የአሜሪካ ፍ/ቤት ሰብእዊ ስራን ተገንዝቦ፣ በጎ ፍትህን አሳይቷል። እንደ እነዚህ ወገኖች ሁኑ ባይባልም፣ ባቅማችሁ የምትችሉትን አድርጉ ማለት ተገቢ ነው። ይህም ሲባል፣ በሺህ የሚቆጠሩት ህይወታቸውን የተሰውትን፣ ወያኔን በየቀኑ የሚጋፈጡትን፣ በየፊናው ሌት ከቀን የሚታገሉትን፣ የጀግኖች ጀግኖች በመዘንጋት አይደለም። የወጣቱ ቆራጥነት ይህን እቅድ ቀስቅሷል ቢባል ትክክል ነው። በእውነትም በነሱ ጉልበት፣ ኃይልና ጥበበ ላይ የተጸነሰሰ ነው።
እስራኤል ኢትዮጵያ በመዳፏ ውስጥ እንዳለች በመቁጠር፣ አንድም የሚያሳስባት ነገር ላይኖር ይችላል። ይህ ድምዳሜ እጅግ የተሳሳተ ፖሊሲ ነው። የኢትዮጵያ አምላክ የሚያመጣው ተአምር አይታወቅም። ድርጊቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዳጅነቱ ዋጋ ያልተሰጠው መሆኑን እንዲያውቅ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ዝቅተኛነቱን እንዲገነዘብ የሚያስደርግ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው። በኢትዮጵያ ላይ ግፍ ስራ እየሰራ ያለውን ወያኔን መደገፍ፣ ደጋፊው እንዳደረገው ይቆጠራል። ኢትዮጵያኖች በየአረብ አገሩ ሲጨፈጨፉ፣ በደሉን የፈጸሙት ኢትዮጵያኖች ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ታሪካዊ እስስር በመገንዘብ ነው። ጉዳቱ እስራኤሎችን የተሰማቸው አይመስልም። ለዚህ ግፍ ያበቃቸው መሳሪያ የሚያግዙለት ወያኔ ነው። እስራኤል ወያኔን መደገፏ ታሪካዊ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያን በእግሯ እንድትቆም የሚያበቋት ብዙ ኃይሎች አሏት። በስደት ያለው ዩኒፎርም ለባሽ ዕድል ቢያገኝ ኢትዮጵያን የላቀች ኃያል ሀገር ያረጋታል። ሌላው ኃይል ሲጨመር፣ እንኳን አንድ ኢትዮጵያ፣ አስር የአፍሪካ ሀገሮችን በቅጽበት በልማት ሊያንጸባርቁት ይችላሉ።
የኢትዮጵያ ትልቁ ጉዳት ፍሬዎቿን እንድታጣ ማድረጉ ነው። ይህን ሀይል ማሰባሰብና ለፍሬ እንዲውል ማድረግ ጊዜው አልተላለፈም። አለም በተናጋ ሁኔታ ላይ ነው። በተለየ ሁኔታ ለኢትዮጵያ አዲስ ዘመን መክፈቻ አጋጣሚ ፈጥሯል። አሜሪካ የራሱን ጥቅም እየፈለገ ነው። በምጽዋት ሀብቱን እየቦጠበጡ የቆዩት፣ ተነጻጻሪ ጥቅም አላገኘባቸውም። እንደ ወያኔ ያለው ሸክም እንጂ ለአሜሪካ አንድም ጥቅም አልሰጠም። ርዳታው ሲቆም፣ የወያኔ ወታደር ጠመንጃ መሸጥ ይጀምራል። ይህ የሚሆንበት ቀን ሩቅ አይደለም። በሌላ በኩል፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያኖችን በደል አጥብቆ ተረድቷል። ከዚህ በኋላ አስፈላጊ የሞራል ድጋፍ ለመስጠት ወደ ኋላ አይልም።
ይህ እቅድ እያንዳንዱ ወገን ተሳትፎበት እቅዴ እንዲለው ይህ ጸሐፊ ትልቅ ተስፋ አለው። አዲስ ኢትዮጵያን እንጀምር!
/2018/