/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በኦሮሚያ ክልል ለሦስተኛ ቀን የቀጠለውን ህዝባዊ እቢተኝነነት ተከትሎ የወረዳና ዞን ባለስልጣናት እራሱን ኮማንድ ፖስት ብሎ በሚጠራው አካል እየታሰሩ መሆኑ ተገለጸ።
ኮማንድ ፖስቱ ህዝቡን ለስራ ማቆም አድማ አስተባብራችኃል በማለት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ የወረዳ አመራሮች ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
ከዚህ ቀደምም የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አባላትና ያለመከሰስ መብት የነበራቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ፣ የነቀምት ከተማ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ፣ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቄለም ወረዳ የፍትህ አስተዳደር ኃላፊና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ከሰኞ ጀምሮ በተሳካ ሁኔታ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ 12 ሰዓት ላይ መጠናቀቁ ተገልጿል። በሦስት ቀናቱ የስራ ማቆም አድማ ከአስር በላይ ንጹሀን ዜጎች ህይወት እንዳለፈ ሲታወቅ በሽህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ደግሞ ለግፍ እስራት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።