ምሁራንና አክቲቪስቶች ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ ጠየቁ

ምሁራንና አክቲቪስቶች ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግእዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ ጠየቁ

ምሁራኑ የተለያዩ ጥናታዊና ታሪካዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አዳርጋቸው የሚከተለውን ደብዳቤና ጥናታዊ ጹፉፍ በማያያዝ አቅርበዋል።

_______________

ጉዳዩ— ኦሮምኛን በአማራው ክልል በግእዝ ስለማስተማር

ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራው ክልላዊ መንግስት ፕሬዘዳንት

ክቡር ፕሬዚደንት ሆይ፡-

የአማራ ክልል ከኦሮሚያ ቀጥሎ ብዙ ሕዝብ የሚኖርበትና ስፋት ያለው ክልል ነው። ከአማራ ክልል ውጭ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ አማርኛ ተናጋሪዎች እንደሚኖሩት፣ የአማራ ክልልም የሌሎች ብሄረሰቦች አባላት በስፋት ይኖሩበታል። ከዚያም የተነሳ በአማራ ክልል ሆነ በተቀረው የአገራችን ግዛቶች የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገራሉ።

አንዳንዶች ቋንቋን የማንነት ምልክት አድርገው የማየት ዝንባሌ አላቸው። ሆኖም ግን ቋንቋ በዋናነት የመግባቢያ መሳሪያ ነው። አንድ ሌላ ቋንቋ የምናውቅ ከሆነ፣ አስተማሪ ወይም ሐኪም ሆነን ወይም በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች፣ ቋንቋው የሚነገርበነት አካባቢ ከሕዝቡ ጋር በቀላሉ የመግባባት እድል ይኖረናል። ቋንቋ ማወቅ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ሊበረታታ የሚገባው ነው።

አንደኛ- ከአማርኛና እንግሊዘኛ ቀጥሎ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ ስለማስተማር

በአዲስ አበባና በአማራ ክልል (ከሚሴ ከተማ የሚገኝበት በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞንን ሳይጨመር) በትምህርት ቤቶች የአማርኛና የእንግሊዘኛ ትምህርቶች ይሰጣሉ። በሌሎች ክልሎች ግን ዜጎች ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ ይማራሉ። ለምሳሌ በትግራይ ክልል እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ትግሪኛ፣ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ሃዲዪኛ፣ በሶማሌ ክልል እንግሊዘኛ፣ አማርኛና ሶማሌኛ ..ይማራሉ። ብዙ ቋንቋ አለማወቃቸው የአዲስ አበባና የአማራው ክልል ተማሪዎችን ግን ብዙ ጥቅሞች እንዲጎድልባቸው ሊያደረግ ይችላል ብለን እናስባለን።

ከአሥራ ዘጠኝ አመታት በፊት ፣ ሁሉም ክልሎች (ከአማራ ክልልና ከአዲስ አበባ በስተቀር) ከአማርኛ በተጨማሪ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ስለሚማሩ፣ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ግን የአፍ መፍቻና የፌደራሉ የስራ ቋንቋ አንድ በመሆኑ፣ የክልሉ ተማሪዎች አንድ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ብቻ በመማር በወደፊት የስራ ህይወታቸው ላይ የሚደርሰውን ተግዳሮት ለመቀነስ፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ አንድ ጥናት አስጠንቶ ነበር። በዚህ ጥናት ዙሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶር በድሉ ዋቅጃራ፣ በፌስ ቡክ ገጻቸው

“በ1990 – የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለጨረታ ያቀረበውን፣ የተጠቀሰውን ጥናት ያጠናነው እኔና ሁለት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነትምህር ባለሙያዎች ነበርን፡፡ በክልሉ በሳይንሳዊ መንገድ ናሙና በመውሰድ (ወላጆችን፣ የትምህርት አስተዳደር ሰራተኞችን፣ መምህራንንና ተማሪዎችን) በተደረገው በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት የኦሮምኛ ቋንቋ በክልሉ ትምህርት ቤቶች በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሰጥ በአንደኛነት መመረጡን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አጥኚዎቹ አዋሳኝ ቋንቋዎችን ከግምት ያስገባና ጥናቱን መሰረት ያደረገ ሀሳብ (recommendation) አቅርበን ነበር”

ሲሉ ጽፈዋል። ዶር በድሉ ፣ ከሰማኒያ ሺህ ብር በላይና ወደ አንድ አመት ገደማ የፈጀው ጥናት ዉጤት፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ባዘጋጀው መድረክ ቀርቦ ዉይይት እንደተደረገበትን ገልጸዋል።

በመሆኑን ክብርነትዎ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአማራ ክልል የትምህርት ፖሊሲ የሚሻሻልበትና ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ ቀጥሎ በዜጎች ወይንም በወረዳው አስተዳደር ምርጫ ሶስተኛ የአገራችንን ቋንቋ የሚማሩበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ሊሆን ይችላል እንላለን። ያ ከሆነ አብዛኞቹ ወረዳዎች ምርጫቸው ኦሮምኛ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን።

ይህ አሰራር በሰለጠኑት አገራት በተለይም በአውሮፓ የተመለደ አሰራር ነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ የትምህርት ፖሊሲ እያንዳንዱ ዜጋ ከፈረንሳይኛና ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ በምርጫ እንዲማር ይደረጋል። አንዳንዶቹ ጀርመንኛ አንዳንዶቹ ራሺያኛ፣ አንዳንዶቹ ጣሊያንኛ .. ይመርጣሉ።

ሁለተኛ – የግእዝ ፊደላትን መጠቀም የአገር ቅርስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው

ምእራባውያን ለጥቁር ህዝብ መሸጥና መዋረድ እንደ ምክንያት የሚጠቀሙበት አንዱና ትልቁ መከራከሪያቸው “ጥቁሮች የራሳቸውን ስነፅሁፍና ፊደል መቅረፅ ያልቻሉት ዝቅተኞች ስለሆኑ ነው” የሚለው ነው። ይሄን ትርክት ውድቅ ለማድረግ፣ ግእዝን ምናልባት የተሻለ ስምም ሰጥተን ኢትዮጲስ ወይም ሌላ ብለነው ወደቀረው አፍሪካ እንዲስፋፋ መታገል ነበረብን። ሆኖም በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች በመወጠራችንና በሃገራችን የሰፈነው የማንነት ፖለቲካና ከኢትዮጵያ የተለየ ማንነት ይፈልጉ የነበሩ አክራሪ ብሄርተኞች አሉታዊ ጫና ምክንያት አላደረግነውም። እንኳን ወደ አፍሪካ አገሮች ግእዝን ልንወስድ ቀርቶ በአገራችን የነጮችን ፊደል፣ ላቲን፣ ለአንዳንድ ኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተጠቀምን ነው። አንዳንድ ወገኖች የግእዝ ፊደልን የአንድ ብሄረሰብ እርስት አድርገው የመቁጠር ዝንባሌ ሲኖራቸው አንዳንዶች ደግሞ የግእዝ ፊደል ብቃት እንደሌለው አድርገው ያስባሉ። የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው አይጻፉም። ስፔሊንጉን ለማወቅ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ፊደላት ግን ሰው እንደሚናገረው ስለሚጻፉ፣ የስፔሊንግ ስህተት ሊሠራባቸው አይችልም። ስለዚህም ከላቲን ፊደል ይልቅ ግእዝ የበለጠ ይመረጣል።

ኤርትራውያን መቼ የግእዝን ፊደላት አንፈልግም አሉ ? ከኢትዮጵያ ተገነጠሉ እንጂ መቼ ከፊደላችን ተገነጠሉ? እንደውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር፣ በላቲን እንቸክችከው ቢሉ፣ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በመገንዘባቸው ግን ፊደሎቻችን ላይ ሙጭጭ ብለው ይዘዋቸው ሄዱ።

ግእዝ የአማራው ማህበረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ቅርስ ነው። ከአረብኛ ውጭ ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው። አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ፣ ሃዲዪኛ፣ ከንባትኛ፣ ንዉርኛ፣ አኙዋክኛ፣ አገዉኛ፣ አደሪኛ፣ ስልጢኛ.. በአሁኑ ጊዜ የግእዝ ፊደላትን ነው የሚጠቀሙት። አደሪኛ ለአስር አመታት ላቲን ይጠቀሙ የነበረ ቢሆንም ግእዝ ይሻላል ተብሎ ወደ ግእዝ ዞሯል።

ኢትዮጵያ በአባቶቻችን መስዋትነት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች አገር ናት። የራሱ ባህል፣ የራሷ ቋንቋዎች፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ቅርሶች ያላት። በአገራችን የሌለ ፣ ለአገር የሚጠቅም፣ ከባእድ አጋር ይዘን ብንመጣ ችግር አይኖረውም። ሆኖም ግን የተሻለ ነገር እኛ ጋር እያለ የሌሎችን ማምጣት ተገቢ አይደለም። ፊደል እንደሌለን፣ ቅኝ የተገዛን ይመስል፣ የኛን የተከበረ ፊደል ጥለን ላቲንን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጠቀም ሊበረታታ አይገባም። ሌሎች ክልሎች የተለየ መስመር ቢከተሉም የአማራ ክልል ግን የአገርን ቅርስ በማስጠበቅ አንጻር የመሪነት ሚናዉን እንዲወጣም በአክብሮት እንጠይቃለን።

ሶስተኛ – የግእዝ ፊደላትን ለኦሮሞኛ ስለመጠቀም

አፋን ኦሮሞ በላቲንም በግእዝም ይጻፋል። በኦሮሚያ ክልል በተለይም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የተወለዱ ወገኖች አፋን ኦሮሞን በላቲን ነው የሚጽፉትና የሚያነቡት። ሆኖም ላቲኑ በጣም ውስንነት አለው። በኦሮሚያ የሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰባትና ከአርባ አመት በላይ የሆኑ ኦሮሞዎች ግእዝ ፊደልን ማንበብ ነው የሚቀናቸው። ቋንቋው በላቲኑ ምክንያት በኦሮሚያ ከተወሰኑ ወገኖች አጥር ውጭ ሊያድግ አልቻለም።

ዶ/ር ፍቂሬ ቶሎሳ፣ ለተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ ለኦሮምኛ ከላቲን ይልቅ ግእዝን መጠቀም ምን ያህል በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ቅልጥፍና፣ በሊንጉስቲክ (ቋንቋ ጥናት) እና በሳይንስ አንጻር የተሻለ መሆኑን አስነብበውናል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሶ የጻፉትን፣ ዶ/ር አበራ ሞላ ሌሎች በርካታ ምሁራን ያደረጉትን ጥናት በተወሰነ መልኩ ያካተተ ተያያዥ ሰነድ፣ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ የተወሰዱ ሁለት ገፆችን አብረን አያይዘናል።

ክቡርነትዎ ሆይ!

እርስዎ አንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም።

በእዚህና እላይ በተዘረዘሩት የአመክንዮ ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለ ክብራችንና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ አፋን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደመሆኑ በኢትዮጵያዊ ፊደል በግእዝ እንዲጻፍ ፈር ቀዳጅ ይሆኑ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቅዎታለን። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ማድረግ ባይቻልም፣ ቢያንስ በተወሰኑ ለኦሮሚያ ክልል ቅርበት ባላቸው ወረዳዎች በግእዝ የአፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻል በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ፣ በግዕዝ ፊደላት “መጫፈ ቁልቁሉ” ተብሎ የኦሮምኛ ቅዱስ መጽሓፍ ተተርጉሟል። የዛሬ 120 ዓመት እንኳን፣ ቅዱስ መፅሐፍን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን፣ አሁንማ በዘመነ- ገጽ 4 የ4 ኮምፒዩተር፣ በቀላሉ ኦሮምኛን ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለ ችግር መክተብ የማንችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ዋናው ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራትና ፍላጎት ናቸው!!

ከታላቅ አክብሮት ጋር

ዶ/ር አበራ ሞላ

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ

ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ

ዶ/ር ባዬ ይማም

ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ

አትሌት ገዛኸን አበራ

የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ

አቶ ያሬድ ጥበቡ

አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው

አቶ ተፈራ ድንበሩ

አቶ ሙሉጌታ ዉዱ

አቶ አበባየሁ ደሜ

አቶ ብርሃኑ ገመቹ

አቶ አብርሃም ቀጄላ

አቶ ሃብታሙ ኪታባ

አቶ ግርማ ካሳ

ግልባጭ፣

ለአማራው ክልል የትምህርት ክፍል ቢሮ

ለአማራው ክልል የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት

ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንቲ ክብር አቶ ለማ መገርሳ

ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት

ኦሮምኛን በገዝ ፊደል መጻፍ ከሳይንስና ከተእክኖሎጂ፣ ከታሪክ፣ ከባህል፣ ከጠቀሜታና ከአመችነት አኳያ ያለው ጥቅም በስፋትና በዝርዝር ያስቀመጠ ጥናታዊ ሰነድን ቀርቧል።

1 COMMENT

  1. ኦሮምኛ በእማራው ክልል ማስተማሩ በጥም መደገፍና። መበረታታት ያለበት ሀሳብ ነው። ቁንቁዋ ህብረተሰብን የሚያቀራርብ፣ የሚያግባባና በኢኮኖሚውም በኩል ጥቀሜታ አለው። የህብረሰቦቻችን ቁዋንቁዎች። ኦሮምኛ፣ ጉራጉዊኛ፣ ሲዳምኛ፣ ከንባቲኛ፣ ትግሪኛ፣ ወላይተኛ ወዘት ተብለው ይጠራሉ ታዲያ ከግእዝ የመጣው በእማራው ክልል የሚነገረው አማርኛ ለምንድነው ወደ ሁዋላ ተመልሶ ግእዝ የሚባለው? ምነው ቃሉን ፈራችሁት? አሁንም የዚህ መከረኛ አማራን የመጥላት እንኩዋ ባልለው ገሸሽ የማድረግ አባዜ አልተወገደም ማለት ነው? በበኩሌ ኦሮምኛ በአራው ክልል አማርኛ በኦሮሚያ ክልል ቢባል ደስ ይለኛል።

LEAVE A REPLY