በ’ስህተት’ ገደልናቸው ስላሏቸው የሞያሌ ሰማዕታት /መሳይ መኮንን/

በ’ስህተት’ ገደልናቸው ስላሏቸው የሞያሌ ሰማዕታት /መሳይ መኮንን/

የትግራዩ ገዢ ቡድን የሚዘውረውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን እየተመለከትኩ ነበር። ተከታታይ ዜናዎቹ በ’ስህተት’ ገደልናቸው ስላሏቸው የሞያሌ ሰማዕታትና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የሚያትቱ ናቸው። መቼም ወታደራዊ ማዕረግ የረከሰበት ሀገር አንድ ሌተናል ጄነራል ውጊያ መምራት፡ የጦርነት ሮድ ማፕ ማዘጋጀት ትቶ የህዝብ ግንኙነት ወንበር ላይ ተቀምጦ ሲተረተር ማየት አስደናቂ ነው። ይህም የሆነባት በእነስብሃት እጅ ላይ በወደቀችው ኢትዮጵያ መሆኑ ነው።

የኮ/ል ማዕረግ የሚበዛበት የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት ምድብ በአንድ ሌ/ጄነራል ሲመራ ብክነት ነው ተብሎ የሚታለፍ ብቻ አይደለም። በሀገር ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀልም ነው። በሂደት መከላከያን እንደተቋም የማራከስና የማዳከም ስውር ሴራ መሆኑን መገመት አይከብድም። ባዶ ማዕረግ ለባዶ ጭንቅላት መደረቡ ትርጉም ባይኖረውም ።

ሌ/ጄ ሀሰን ኢብራሂም የሚባል የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት ማብራራያ በሰጠበት የኢቲቪ ዜና ላይ የሰማሁትን ማመን ነበር ያቃተኝ። ሰውዬው የ17 ሰዎች ጨፍጨፋን(እሱ 9 ሰዎች ናቸው ቢልም) በስህተት የተፈጸመ ነው ይላል። የኦነግ ሰራዊት መግባቱን ተከትሎ የተሰማራው አንድ ሻለቃ ጦር ውስጥ ያሉ አምስት ወታደሮችና አንድ አዛዥ በመረጃ ስህተት የፈጸሙት ግድያ ነው ሲልም ደረቱን ገልብጦ፡ ልቡን ነፍቶ ጸጸት በሌለው ድምጸት ይናገራል። አምስቱን ወታደሮች የጦስ ዶሮ አድርገው ሊቀጧቸው እንደሆነ ተመልክቷል።

የሞያሌውን ትራጄዲ በቅርበት ከነዋሪዎቹ አንደበት ላዳመጠ ሰው የሰውዬውን ቅጥፈት በሚገባ ይረዳዋል። ትላንት በቀጭኗ ሽቦ ከሞያሌ ነው ያረፈድኩት። ሁኔታውን በአካል የተገኘ እስኪመስል እዛው ሆኔ ተከታትዬዋለሁ። እንዴት እንደተጀመረ፡ በምን ዓይነት የጭካኔ እርምጃ እልቂቱ እንደተካሄደ የዓይን ምስክር ከመሆን አንድ ደረጃ ዝቅ ብዬ መመስከር የምችለው ጉዳይ ነው። ከወገኖቼ ዕልቂት በላይ ውስጤን በሀዘን የመታው የገዳዮቹ መግለጫ ነው። ”ስህተት”

የትግራዩ ገዳይ ቡድን ጡጦ ላልጣለ ህጻን እንኳን የማይመጥን ምክንያት ይዘው አደባባይ ሲወጡ ሁለት ግዜ መግደላቸውን አላስተዋሉም ማለት አይቻልም። ሆን ብለው ጠላት አድርገው የፈረጁትን ህዝብ በስነልቦና ጥቃት ለመደቆስ እንደሆነ ከግምትም በላይ መግለጽ የሚቻል ነው። በጥይት ከገደሏቸው ወገኖቻችን በላይ በ’ስህተት’ ገደልናቸው ብለው በአደባባይ ማቀርሸታቸው በህይወት ለቆየን ከስድብም በላይ ነው። ኦነግ መስለውን ገደልን እንዳይሉ የተጨፈጨፉት በሙሉ አንድም መሳሪያ በእጃቸው ያልያዙ ናቸው።

ተሰብስበው ሲጫወቱ ፡ በበረንዳ ላይ ሻይ ቡና ሲሉ የነበሩ ወጣቶችን ግንባርና ደረት በጥይት እየመቱ መግደል በምንም መለኪያ ስህተት ነው ተብሎ የሚገለጽ አይሆንም። ይህ ንቀት ነው። የጭካኔአቸው ለከት ማጣቱን የሚያመለክት ነው። እስከዛሬ የገደልናቸሁ ተገቢ ነው የዛሬው ግን ስህተት ነው የሚል ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። ለምን የትላንቱ ጭፍጨፋ ስህተት ተባለ? የጨለንቆውስ? የቢሾፍቱስ? የባህርዳሩ? የወልዲያው? የሲዳማው? የአኝዋኩስ? ዝርዝሩ ይቀጥላል።

ማዕረጉ የከበደው ሌ/ጄ ሀሰን የትግራይ ገዳይ ቡድንን መልዕክት ተፍቶ በ3ደቂቃ ዜና አረጋግቶ መውጣቱ ነው በእሱ ቤት። ያልተረዳው ግን ከጭፍጨፋው በላይ ጥይት በሌለው የውሸት መሳሪያ ህዝብን ዳግም የገደለበት መግለጫ መሆኑን ነው። ለማንኛውም ሞያሌ እንደሌላው የኢትዮጵያ ሰለባ የሆኑ አከባቢዎች በታሪክ የሚመዘገብ ትራጄዲን አስተናግዳለች። ከገዳዮቹ ስለገደሉበት ምክንያት የምንሰማበት ወቅት አይደለም። ለምን እንደገደሉን እናውቃለን። ወደፊትም እንደሚገድሉን አይጠፋንም።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገጉት በዓል ለማክበር አይደለም። ለፌሽታና ደስታም አይደለም። በጅምላ ለመግደልና ለማሰር እንጂ። ያንንም እያደረጉት ነው። በወለጋ ጀምረው፡ ሸዋ ተሻግረው፡ ሞያሌ ላይ በሰነዘሩት የዕልቂት በትር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት ከሚገባው በላይ አሳይተውናል። ምንም እንኳን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማው ውድቅ የተደረገ ቢሆንም እጃቸውን አውጥተው ለአዋጁ ድጋፍ የሰጡ በጥቂት ቁጥርም ቢሆኑ የኦሮሞ ተወካዮች፡ ሌላው የምክር ቤት አባላት ከትግራይ ገዳይ ቡድን እኩል በህግ ፊት የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

LEAVE A REPLY