“የዚህ ሰው ጥፋቱ ኢትዮጵያን ማፍቀሩ ብቻ ነው” /ያሬድ ሹመቴ/

“የዚህ ሰው ጥፋቱ ኢትዮጵያን ማፍቀሩ ብቻ ነው” /ያሬድ ሹመቴ/

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ማርቆስ አብርሐም በትላንትናው እለት ለእስር መብቃቱን ሰማን።

ይህ ሰው የዓድዋን ድል በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ በግዙፍ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና በጎንደር ወጣቶች ግዙፍ አጀብ አክብሮ ያስከበረ። ጥሮ ግሮ ያገኘውን ገንዘብ ለሀገር ፍቅር ስሜት መግለጫነት ሲዘራ የኖረ። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲል ብቻ የምንሰማው የነደደ የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው ወጣት ነው።

እንደ ክስ የቀረበበትም ወንጀል ቢኖር “ኮከብ አልባ ሰንደቅ አላማ ይዘሀል” የሚል እንደሆነ ሰምተናል። ይህ ሰንደቅ እኮ የዓድዋ ዘመቻ መሪ እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። የዓድዋ ድል አልባሳትንና ምስሎችን በወቅቱ በነበረው መልክ ለትዕይንት ሲያበቃ የወቅቱን ሰንደቅ መጠቀሙ እንደ ወንጀል ተቆጥሮበታል።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ፤ በሀገር ፍቅር መርህ፤ በኢትዮጵያ አንድነትና ህብረት ስሜት፤ ለሚጓዝ ምርጥ የሀገር ልጅ በሙሉ ስጋት መሆኑ እንዲገባን መደረጉን ታዝበናል።

አራስ ባለቤቱን ተለይቶ፤ ገና የተወለደ አራስ ህጻኑን ቤቱ ትቶ፤ ለእናት ሀገር ፍቅር በሰራው መልካም ስራ ምክንያት ዛሬ ማደሪያው እስር ቤት መሆኑ እጅጉን የሚያስለቅስ፤ የሀገራችንን መጪ ግዜ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚከት፤ ፈጽሞ ለልብም ለአእምሮም ሙግት የማይመች ከንቱ ነገር ገጥሞናል።

ማርቆስ አሸባሪ አይደለም። ሀገር ወዳድ ወጣት እንጂ። ማርክ ድብቅ ጀርባ የለውም። የጀግኖች አያቶቹ ፍቅር እንጂ።
ድፍን ሀገር የሚያውቀው ሀቅ ነው።

እባካችሁን በስህተት ነው በሉና ማርቆስን ፍቱልን። ለእኛም በሀገር የመኖር ተስፋችንን አታጨልሙብን።

የዚህ ሰው ስህተቱ ኢትዮጵያን ማፍቀሩ ብቻ ነውና፤ እናንተም ኢትዮጵያን አፍቅራችሁ ከስህተቱ አንፁት።

ፈጣሪ ማርቆስንና ቤተሰቦቹን ይጠብቅልን።
ሠላም ለኢትዮጵያ!!
(ሼር በማድረግ ለማርቆስ ድምጽ እንሁነው)

LEAVE A REPLY