ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ መበርበሩን አመነ

ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ መበርበሩን አመነ

የፌስቡኩ ፈብራኪና አለቃ የሆነው ማርክ ዙከርበርግ ‘በስህተት’ የሰዎች ግላዊ መረጃ ያለፍላጎታቸው መበርበሩንና ለአንድ የፖለቲካ አማካሪ ድርጅት ጥቅም መዋሉን አመነ።

‘ካምብሪጅ አናሊቲካ’ የተባለ የፖለቲካ አማካሪ ተቋም የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ ለፖለቲካ ጥቅም ማዋሉን ተከትሎ ነው የማህበራዊ ትስስር ዘዴው ወቀሳው እውነት መሆኑን ያመነው።

ዙከርበርግ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሲሰጥ “የግለሰቦች ግላዊ መረጃ ያለአግባብ ተበርብሯል” ብሏል።

ዘግየት ብሎም ከሲኤንኤን ጋር ቃለ-ምልልስ ያካሄደው ዙከርበርግ በሁኔታው ‘በጣም ማዘኑን’ እንዲሁም ይህን ህገ-ወጥ ድርጊት የፈፀመ ሰዎች ላይ ደግሞ ‘እርምጃ’ ለመውሰድ ማቀዱን ተናግሯል።

የአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርቦ ስለሁኔታው ማስረዳት መቻሉ እረፍት እንደሰጠው የተናገረው የፌስቡክ አለቃ ዙከርበርግ የሰዎችን ግላዊ መረጃ የሚበርብሩ መተግበሪያዎች (አፕሊኬሽን) ይህን ማድረግ እንዳያቻላቸው ለማድረግ የማያደርገው ጥረት እንደሌለም አሳውቋል።

“የእርስዎን ግላዊ መረጃ የመጠበቅ ግዴታ አለበን። ይህንን ማድረግ ከተሳነን ግን እርስዎን ለማገልገል ብቁ አይደለንም ማለት ነው” ሲልም በፌስቡክ ገፁ አስፍሯል።

የሰሜን አሜሪካው የቢቢሲ ቴክኖሎጂ ነክ ዘገባዎች ተንታኝ የሆነው ዴቭ ሊ ግን የፌስቡክ ይቅርታ አልተዋጠለትም። “ትልቁ ነገር ጥያቄ ይቅርታ መጠየቁ ሳይሆን ይህ ጉዳይ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ምርመራ መካሄዱ ነው” ሲል ይከራከራል።

ፌስቡክ በአውሮፓውያኑ 2014 ላይ የገጠመውን ዓይነት የመረጃ መሹለክ ክስተት ድጋሚ ማጋጠሙ ትልቅ ትንታኔ የሚፈልግ መሆኑንም ዴቭ ያስረዳል። የሰዎች ግላዊ መረጃ ያለፍላጎታቸው ሲበረበር ማስጠንቀቂያ እንኳን አልደረሳቸውም ይህም ምላሽ ይፈልጋል ባይ ነው ተንታኙ።

ፌስቡክ ላይ ጫናዎች የበረቱ ሲሆን ‘ካምብሪጅ አናሊቲካ’ የተሰኘው መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ተቋም እንዴት አድርጎ የ50 ሚሊዮን ያህል ተጠቃሚዎችን መረጃ እንደበረበረ አሁንም በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።

የአሜሪካው ፌዴራላዊ የንግድ ኮሚሽን ፌስቡክ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ማዘዙን አንዳንድ ዘገባዎች እየጠቆሙ ይገኛሉ። የአውሮፓ ሕብረትም መሰል እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል እየተነገረ ነው። የአንግሊዝ መረጃ ኮሚሽን ደግሞ ካምብሪጅ አናሊቲካ የተሰኘው ተቋም ላይ ግልፅ ምርመራ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ነው።

የፖለቲካ አማካሪ ተቋሙ በ2017ቱ የኬንያ ድጋሚ ምርጫም ውስጥ እጁ እንዳለበት ዘገባዎች ከጠቆሙ በኋላ ግልፅ ምርመራ እንዲካሄድ ጫናዎች እየበረቱ ይገኛል።

ምንጭ~ ቢቢሲ አማርኛ

LEAVE A REPLY