/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ዶ/ር አቢይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው በተመርጡበት የግንባሩ ምርጫ ሂደት ውስጥ እንዳልመረጥ ቅስቀሳ አድርጌያለሁ ሲሉ አቶ ደብረፂዮን ተናገሩ።
ዶ/ር ደብረፂዮን እንደተናገሩት ትግራይን ለማስተዳደር ከተመረጥኩ አጭር ጊዜ ስለሆነኝ መመረጥ አልፈለኩም ነበር ማለታቸው ትችት እያስከትለ መሆኑን ኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ገለጹ፡፡
በድርጅቱ ታሪክ ተቃውሞ የታየበትና ፉክክር የተስተዋለበት ነው የተባለለት የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በተጠናቀቀ ማግስት ወደ መቀሌ ያመሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ስብሰባው ልዩና አዲስ መልክ የያዘ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡
በአንጻሩ መመረጥ አልፈልግም ነበር ማለታቸው ድርጅታቸው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የደረሰበትን መናጋት ለመሸፈን የተጠቀሙበት ተራ ሽንገላ ነው ሲሉ አስተያየት ስጭዎች ተችተዋል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን የጠቅላይ ሚኒስትር ቦታውን ‘ስላልፈለኩ’ ነው የሚል መልእክት ለማስተላለፍ መሞከራቸው በህዝብ ላይ መሳለቅ መሆኑን ያሰመሩበት ተንታኝ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ “ስላልፈለኩ… እንጂ…” የሚያስብል ተራ ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረው፤ የህዝብ ብሶት ጣሪያ የነካበት፡ ውጥንቅጥ የሆነው የሃገሪቱ ፖለቲካ ዘመናዊ የለውጥ እምርታ ሊያሳይ የሚገባበት ፈታኝና አሳሳቢ ወቅት ላይ የትግራይን ህዝብ ላንተ ሰለ ነው ሀገር ያልመራሁት ማለት አሳሳቢ በሆነው ያገሪቱ ችግር ላይ ግዴለሽነትን ማሳየት ነው ብለዋል።
ተንታኙ እንደሚሉት ዶ/ር ደብረፂዮን ያደረጉት ይህ ቃለ ምልልስ የሚወክሉት ድርጅት አሁንም ራሱን በማታለል ላይ የተመሰረተ እና አሁን ያለንበትን ዘመን የፖለቲካ እርምጃ ያልተከተለ ነው ከማለታቸውም በተጨማሪ በግልጽ እንደሚታየው ኢህአዴግ ቀደም ሲል ገበሬውን ማህበረሰብ ለማንበርከክ ይጠቀሙበት የነበረውን ሽንገላ በአሁን ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ የሚፍጨረጨር መሆኑን የሚያመለክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢህአዴግ ዶ/ር አብይ አህመድ በአብላጫ ድምጽ ከማሸነፋቸውም በተጨማሪ ከህወሃት አባለትም ድምጽ አግኝተዋል ተብሏል።
በኢህአዴግ አባላት ጠቅላላ ጉባኤ መደበኛ ግምገማ ወቅት ዶ/ር አቢይ 108፤ አቶ ሽፈራው ሺጉጤ 59፤ ዶ/ር ደብረጽዮን 2 ድምጽ ማግኘታቸው ተዘግቧል፡፡