/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲደረግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ። ህብረቱ በኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ዶክተር አብይ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባሰሙት ንግግር ለዲሞክራሲ፣ ለህግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር እንደሚሰሩና ከኤርትራ መንግስት ጋርም ለመወያየት እንደሚፈልጉ የተናገሩትን በማድነቅ፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ የህብረቱ ድጋፍ እንደማይለያቸው አስታውቋል።
ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳቱ ጉዳይ የማሻሻያ ፕሮግራሙ አካል እንደሚሆን የህብረቱ ፅኑ እምነት እንደሆነም ተገልጿል።
ከ1997ዓ.ም ምርጫ ወዲህ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት የአውሮፓ ፓርላማና የፓርላማው የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ አና ጎሜዥ የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት አስመልክተው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “በኢትዮጵያ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሽግግር የሚደረግን ጥረት የሀገሬው ህዝብ የሚደግፈውን ያህል የአውሮፓ ፓርላማ ያለ ጥርጥር እንደሚደግፏቸው በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ” በማለት ተናግረዋል።

























