ፋታ ለአብይ ወይስ ለወያኔ? /ከአንተነህ መርዕድ/

ፋታ ለአብይ ወይስ ለወያኔ? /ከአንተነህ መርዕድ/

/ሚያዝያ 2018/
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ባልደረቦቹ የህዝባዊ እምቢተኝነቱ ውጤቶች መሆናቸውን ከዚህ በፊት ፅሁፌ ገልጨዋለሁ። ህዝቡ ይህንን ዘረኛ አገዛዝ በቃኝ ባይል ኖሮ እነዚህ ሰዎች እየቆጫቸውም ቢሆን የህወሃት አገልጋይ እንደሆኑ ይቆዩ ነበር። አዎ የህወሃት መሃይማን ከመሬት ተነስተው ሲሰድቧቸው (በጥፊም የተመቱ አሉ ይባላል)፣ ሲያስፈሯቸው፣ እነሱን ቁልቁል ደፍቀው ወደላይ በሃብትና በስልጣን ሲተኮሱ፣ ወገኖቻቸውን በግፍ ሲዘርፉ፣ ሲገድሉና ሲያሰቃዩ ሆድ ሆዳቸውን እየበላቸውም ቢሆን ዝም ብለው በአገልጋይነት ይቀጥሉ ነበር እንጂ አጉል መስዋዕት ለመክፈል አይነሱም ነበር።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ህዝቡ በቃኝ ሲል በተለይም የኦሮምያና የአማራ ወጣት በአልሞ ተኳሽ ግንባሩን ተመትቶ ሲወድቅ ሌላው ሳይፈራ ወደፊት በተቃውሞ ሲንደረደር፣ መቶ ሺዎች ታፍሰው ሲታሰሩ ሌላው ሚሊዮኑ እንደጎርፍ ሲመጣ፣ በመገደል፣ በመታሰር፣ በመደብደብ የስርዓቱን ክንድ ሲያልመው ከውስጡ ሆነው የሚያዩ የህዝቡ ልጆች ‘ጊዜው አሁን ነው’ ብለው መነሳታቸው በህዝባቸው ኃያልነት በመተማመን ነው።

ህወሃቶች እንኳዋን በቁማቸው ሞተውም አራት ኪሎን ማንም እንዳይረግጣት የተማማሉ ነበሩ። በትግል መስዋዕት ሆነን ያመጣነው እያሉም የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘለዓለማዊ ባርነት እንዳዘጋጁት በድፍረት ተናግረውም ነበር። አጫሉ (አራት ኪሎፍ ሲቱ አኒ) “አራት ኪሎ መግባት ለአንተ አይቀርብም ወይ?” ብሎ በመድረክ በመዝፈኑ እውነቱ አጥንቱ ድረስ የሰበቀው ዘርዓይ እንዴት እንዳንገበገበው አይተናል። በበዓለ ሲመቱ ላይ ደብረፂዮን፣ አባይ ፀሃዬ፣ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ በረከት ሲሞን፣ አርከበ እቁባይ … በህዝብ ደም የገነቡት ስርዓት እየፈራረሰ የሚጠሉት ኢትዮጵያዊነትና የሃገር ፍቅር ገንኖ ሲወጣ አይተዋል። በእራት ግብዣውም የስርዓታቸውን የቁም ተዝካር ተቋድሰዋል።

ወያኔዎች የቀራቸው መተማመኛ ምርኳዝ መከላከያው፣ ደህንነቱና ክደውት የኖሩትን የትግራይ ህዝብ በጉያው እንዲደብቃቸው ማድረግ ነው። ካንድ ዘር መልምለው ያስቀመጡት የጦር አመራር በውስጡ የሚገኘውን መቶ ሺህ ከህዝብ የወጣ ሰራዊት ህዝብ ላይ እንዲተኩስ ቢያዙትም የኋላ ኋላ አፈሙዙን እነሱ ላይ እንደሚያዞር ያዩታል። በትግራዋይ የተሞላው ደህንነትም በህዝቡ መሃል ገብቶ መረጃ መሰብሰቡ እንደድሮው የሚሳካለት አልሆነም። በሰብአዊ ጋሻነት ሊጠቀሙበት የሚታትሩት የትግራይ ህዝብም ልጆቻቸውንና ንብረቶቻቸውን ቀድመው ያሸሹና እንደመንግስቱ ኃይለማርያም ሊፈረጥጡ የተዘጋጁ ከሃዲዎችን ደግፎ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እንድማይቆራረጥ የታወቀ ነው።

በዚህ ሁኔታ የተዳከመው ህወሃት ሲወድቅ ጉዳት አያደርስም፣ አሁንም ጥፍጣፊ ጉልበት የለውም ብሎ የሚዘናጋ የዋህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ኃይሎች መተማመኛቸው ምንም ኃይል ሊያቆመው የማይቻለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው። የአመፁም ግብ ኢትዮጵያን ነፃ ማውጣት እንጂ የጠቅላይሚኒስትር ቦታ በዶክተር አብይ ማስያዝ አይደለም።

አንዳንድ የዋሃን ወይንም የወያኔ ተከፋዮች “ዶክተር አብይን ፋታ እንስጠው” ሲሉ ይሰማል። አዞዎች መንጋጋ ውስጥ አብይን አስገብቶ ፋታ እንስጠው ማለት ቆረጣጥመው ይብሉት ብሎ መወሰን ነው። በሌላ አነጋገር ሞት አፋፍ ላይ ላለው ህወሃት ፋታ እንስጠው የሚል ነው። ከፍ ሲልም ህወሃት አፈር ልሶ በመነሳት ዘራፊና ዘረኛ አገዛዙን እንዲቀጥል በህዝብ ላይ መፍረድ ነው። ፈረንጆች እንደሚሉት ብረትን ወደተፈለገ ቅርፅ ለመለወጥ እንደጋለ ነው መምታት። እንደ ልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ ፋታ የሚለው መዝሙር ሞት ያረገዘ አደገኛ መልዕክት ነው። ስለዚህ ዶክተር አብይንና ጓዶቹን ብሎም አገራችንን እንዴት እንርዳ? ነው ዋናው ጥያቄ።

ትግሉ መልካም ፍፃሜ እንዲያገኝ የዴሞክራሲያዊ ኃይላት ድርሻ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት እየተናበበና እየተቀናጀ በትንሽ መስዋዕት እንዲቀጥልና ወደ ድል እንዲደርስ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትንና ለአገሪቱ ያለሙትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። መጀመርያ አገሪቷ በወታደራዊ አገዛዝ ጨምድዶ የያዘው አስቸኳይ አዋጅ ማስነሳት የሚችለው ህዝቡ እንጂ አብይ አይደሉም። አብይን ከነስልጣኑ ማስፈታት የሚቻለው ህዝባዊ አመፁን የበለጠ በማቀጣጠልና የዲፕሎማሲ ትግሉን በማጎልበት አስቸኳይ አዋጅን ማስነሳት ስንችል ነው ።

አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ውስብስብ ቢሆንም ተራ በተራ መፈታት ካለባቸው የህብረተሰቡ ጥያቄዎች ውስት ጉልሆቹ የሚከተሉት ናቸው።
• አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት
• ማናቸውም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ
• ግድያ፣ እስራትና ማሰቃየት እንዲቆም
• ሰብአዊ መብት እንዲከበር
• ሰራዊቱ ህዝቡን ማሰቃየቱን አቁሞ ወደ ካምፑ እንዲመለስና ዳር ድንበር እንዲጠብቅ
• ተቃዋሚዎች በህዝባቸው መካከል በነፃ ተንቀሳቅሰው እንዲያደራጁ ማስቻል
• ህገወጥ አዋጆች እንዲሰረዙ
• የፕሬስና ሃሳብን የመግለፅ የመደራጀት መብት እንዲከበር
• ብሄራዊ እርቅ ጉባኤ እንዲዘጋጅ
• በግድያ፣ በዘረፋና በልዩ ልዩ ወንጀል የተሳተፉ ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ ናቸው። ዝርዝሩ ከፍ ይላል።

እነዚህንና ሌሎችንም መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ህዝቡ የተለያየ መንገድ ተጠቅሞ አንድ በአንድ እንዲፈቱ የእምቢተኝነት እርምጃ መውሰድ አለበት።

በተለይም ከዚህ በፊት ውጤታማ የሆኑት ቤት በመቀመጥ፣ መንገድ በመዝጋት፣ ግብር ባለመክፈል፣ ሥራ በማቆም፣ የአገዛዙ ንብረቶች ላይ እቀባ በማድረግ የህወሃትን እጅ እየጠመዘዙ ድሉን መንጠቅና ማስጠበቅ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝባዊ እምቢተኝነትን እንደግብአት ሳይጠቀሙ እርምጃ ይወስዳሉ ብሎ መጠበቅ የፖለቲካ የዋህነት ነው። ገፍቶ አራት ኪሎ ያስገባቸው ህዝብ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ሌት ተቀን በተግባር ከጎናቸው መቆም አለበት። ዶክተር አብይን ቤተመንገስት ወርውሮ አስገብቶ መተኛት ጠላት ፊት ሰራዊቱን አይዞህ ብሎ ልኮ ስንቅና ትጥቅ በመከልከል ለሞት እንደማጋለጥ ነው።
ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ ብለዋል ዶክተር አብይ
አሜን!

LEAVE A REPLY