የኢትዮጵያም ትንሳዔ ይሁንልን! /በአንዱ-ዓለም አራጌ/

የኢትዮጵያም ትንሳዔ ይሁንልን! /በአንዱ-ዓለም አራጌ/

ኢትዮጵያውያን በአገዛዝ ቀንበር ሥር ነበርን፤ አሁንም በነበርንበት ቀጥለናል። በኢትዮጵያ የኅላዌ ዘመን ሁሉ አገዛዝ ተለይቶን አያውቅም። ለአለፉት 27 ዓመታት የተጫነብን የአገዛዝ ቀንበር ደግሞ ከመቼውም ጊዜ የተለየ ነው። የተለየ ብቻ ሳይሆን የከፋም ነው። የከፋ ያልኩት ዘርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው።

ዘርን መሠረት ያደረገው አገዛዝ በደምና ስጋ የተገመደውን የሕዝባችንን ቁርኝት ሳይቀር ለመበጠስ ትልቅ ተግዳሮት ጋርጦብን ነበር። ትዳሮች እንዲፈርሱ፣ ጉድኝቶች እንዲቀዘቅዙ፣ አለመተማመን በመሐከላችን እንዲነግሥ፣ በዘር ተቧድነን እንድንቆራቆዝ፣ ደም እንድንፋሰስ፣ አንዳችን ስለሌላው ልንሞት ሲገባን ሌላውን ለመግደል ያደባንበት ሁኔታ ተከስቷል። ይህን የመሰለው ሁኔታ የአገራችንን መሠረት እስከማናጋት የሚደርስ ተግዳሮት ሆኖ ነበር።

ከሁሉም በላይ ለሰው ዘር ሁሉ ቤዛ ስለሆነው መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በሚሰበክባቸው አብያተ ክርስትያናት ድረስ ዘልቆ በመግባት በዘር የመለያየት ሁኔታ መፈጠሩን በሐዘን እናስታውሳለን። በተለይ በውጭ አገራት በሚገኙ አብያተ ክርስትያናት ችግሩ ሥር የሰደደ መሆኑን እንገነዘባለን። የተለያዩ ብሔር ተወላጆች የራሳቸውን አብያተ ክርስትያናት ለመፍጠር የሔዱበት መንገድ ቅስምን የሚሰብር ነው። ብንችል ፈጣሪያችንንም ለመክፈል የምንተጋ ይመስላል። ይህ ሁኔታ ምን ያህል ከሰብአዊነት ጎዳና እያፈነገጥን እንደሆነ ብሎም ምን ዓይነት የሞራል ድቀት ውስጥ እንደምንገኝ ያሳያል።

አሁን የልዩነቱ ማዕበል ፀጥ ሲል ይሰማኛል። የልዩነቱ አቧራ ሲሰክን ይታየኛል። ከፊታችን ወደእኛ በሚገሰግሱ ዓመታት ከቆምንበት የመለያየት አዘቅት ወደ ሰማይ ጠቀስ የወንድማማችነት ተራራ ስንወጣ ይታየኛል።

ለዘመናት በአገራችን ላይ በደቀደቀው የአገዛዝ ጨለማ ላይ የብርሃን ፍንጣሬ ሲረጭ አያለሁ። ይህ የብርሃን ፍንጣሪ ለሁላችንም ወደሚያበራ የዴሞክራሲ ደማቅ ጀምበር እንዲለወጥ ከምኞት ባለፈ ሁላችንም ተቀዳሚ አጀንዳችን አድርገን እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንታገል ይገባል። የዴሞክራሲና የፍትሕ ፀሐይ የወጣበት ምድር ሕዝቡን ፆም አያሳድርም። ምርቱን በልግሥና ይሰጣል። ቁራሽ ፍለጋ በአየር፣ በምድረ-በዳና በባሕር ከአገራችን የምንኮበልልበት ዘመን ላይመለስ ሲነጉድ ይታየኛል። ይህ እውነት ደምና ስጋ እንዲለብስ ሁላችንም የተተበተብንባቸውን የመለያየት ድሮች በጣጥሰን ለእውነተኛ ፍትሕና ዴሞክራሲ የፀና ሠላማዊ ትግል አበክረን ልናደርግ ይገባናል።

የክርስቶስ ትንሳዔ ዘመንን ከፍሏል። ሞትን በፍቅር ድል ነስቷል። ጥላቻን በፍቅር ገድሏል። ይህ የትንሳዔ በዓል በየግል ሕይወታችን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የስኬትና የትንሳዔ ብሥራት እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ። እንደአገር ከአገዛዝ፣ ከችጋርና ከጥላቻ ጨለማ ወደ የዴሞክራሲ፣ የብልፅግናና የፍቅር ደማቅ ንጋት የምንሸጋገርበት ይሁንልን።

“በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ” እንደሚል የቆሰለው ልባችን ሊፈወስ ዘመን ደጃችን ላይ ቆሟል። አሁኑኑ የልባችንን በርና መስኮት ለፍቅር እንክፈት። ከፍ ብለው በሚታዩት የቤተ እምነቶቻችን ጉልላት ላይ የእውነት፣ የፍትሕ፣ የሠላም፣ የፍቅርና የወንድማማችነት አርማዎቻችን ከፍ ብለው ይውለብለቡ። የሃይማኖት መሪዎቻችን የሚሞተውን የሰው ልጅ ሳይሆን ዘላለማዊውን ጌታ በመፍራት እንደዓላማ ሰንደቅ ከሩቅ የሚታዩ የእውነትና የፍቅር ተምሣሌቶች እንዲሆኑ እመኛለሁ።

ትንሳዔ ስለፍቅር ፍቅርም ስለትንሳዔ ነው።
የኢትዮጵያን ትንሳዔ በፍቅር፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ ላይ እናንፅ!

ጥላቻን በማስወገድ ፍቅርን እንደቡልኮ እንልበስ – እንፈወስ።

LEAVE A REPLY