አብይን ፍለጋ /መስፍን ማሞ ተሰማ/

አብይን ፍለጋ /መስፍን ማሞ ተሰማ/

“ቃል ካልወጣ በአእምሮ ውስጥ ቢብሰለሰል ብቻውን ሀሳብ ሊሆን አይችልም።” ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)

የኮርያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ኢንተርቪው ሊያደርጉኝ መጥተው ከብዙ ውይይት በሁዋላ “እንዴት ስለስፔስ ታስባላችሁ? እናንተ ድሃ ሀገር ናችሁ። ህዝባችሁ አግራሪያን (አርሶ አደር) ስለሆነ ማሰብ ያለባችሁ አግሪካልቸር እንዴት መሻሻል እንዳለበት አይደለም እንዴ?” ብሎ በጣም ደፋር ወጣት ጋዜጠኛ ጠየቀኝ። የመለስኩለት መልስም እንዲህ ነበር፤-

እናንተን ነፃ ለማውጣት ወደ ኮርያ ስንዘምት ጠቅላላ ጦርነቱን የመራው ሰውዬ ጄኔራል ማካርቲ ይባላል። አራት ኮከብ ማዕረግ ያለው የአሜሪካን ጄኔራል ነው። ጄኔራል ማካርቲ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓንን ለመውረር ጦር አዝምቶ የገባና የኮርያ የርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ ደቡብን ለማገዝ የቆመውን ሀይል ለመምራት ወደ ሶል የሄደ ሰው ነበር። ከጦርነቱ በሁዋላ ኮርያኖችን ሰብስቦ ኮርያን መልሶ ለማደራጀት (አሁን ያለውን አይደለም) አንድ ሴንቸሪ ያስፈልጋል ብሏቸው ነበር። አንተ (ጋዜጠኛውን ነው) አታውቃቸውም። ያንተ አያቶችና አባቶች ይህንን ኔጌቲቭ ኢነርጂ ባለመቀበል መቶ ዓመት ሳይሆን በሰላሳ ዓመት ኮርያ በነበረችበት ሳይሆን በብዙ እጥፍ በልጣ እንድትፈጠር አድርገዋል። ቻይናና ኮርያ ስፔስ ቴክኒዮሎጂ የሚባል በጀመሩበት ሰአት ጂዲፒያቸው በተለይም ቻይና 300 ዶላር ፐር ካፒታ አይሞላም ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ 27 ሚሊዮን – ፕላስ – ተማሪዎች (የሚማሩበት) ትምህርት ቤት አላት። የኮርያን አጠቃላይ ፖፑሌሽን ግማሽ እጥፍ የሚሆን ማለት ነው። ኢትዮጵያ ሰሜንና ደቡብ ኮርያን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት እጥፍ ትሰፋለች። ከፍተኛ ፖፑሌሽንና ስፋት ብቻ ያላት ሳይሆን በተፈጥሮ ሀብት በፍፁም አይወዳደሩም።

እና እናንተ ኮርያኖች ነፃ ከወጣችሁ በሁዋላ የደፈራችሁትን ሳይንስ እኛ ደግሞ ለሺህ ዓመት የቆየ ታሪክ ያለን ሰዎች አንፈራም ብቻ ሳይሆን በስፔስ መስክ ወይ በፊውቸር ሳይንስ መስክ የተሻለ ውጤት አምጥተን እናሳያችዃለን። ይህ ደግሞ የሚሆነው ተረት ተረት ሳይሆን ናሳ ውስጥ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችን በማየት፤ ሲያትል በመሄድ በማይክሮ ሶፍት ውስጥ ያሉ በጣም ብርቅዬ የኮምፒዩተር ጀግኖችን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል።

ይህ ድንቅና ምጡቅ ርዕይ ያዘለ ቃል የተነገረው በወርሃ ግንቦት 2008 ዓ/ም ነበር። ተናጋሪውም የኢህአዴጉ ዶ/ር አብይ አህመድ። ይህንን ሀገራዊና ትውልዳዊ ሩቅ ዓላሚ (ቪዥነሪ) ስስማው የናሳው ዕውቅ ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ ትዝ አለኝ። ቅጣው ናዚስት ህወሃትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ከሳይንቲስትነት በተጨማሪ በቅምጥልና በክብር ከቤተሰቦቹ ጋር ከሚኖርበት ሀገረ አሜሪካ ሁሉን ጣጥሎ ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ ጫካ ገብቶ ብረት አንግቦ ለመፋለም ኤርትራ ወረደ። ህልምና ትግሉ ግን በአጭር ተቀጨ። ጎልማሳውን ሳይንቲስት ማን ገደለው? ወይስ ማን አስገደለው? አንድ ቀን ታሪክ ቆፍሮ ሀቁን ያወጣል። ቅጣው በህይወት ቆይቶ ቢሆን ኖሮና በ2010 ዓ/ም መጋቢት 24 ቀን በእለተ ሰኞ በተፈጠረው ታሪክ ስለ ሀገሩ መፃዒ ዕጣ ፈንታ ምን ይሰማው ነበር?! ስንቶች ስለ ኢትዮጵያ በአጭር ተቀጩ?

በ2008 ዓ/ም የተነገረው የኢህአዴጉ አብይ አህመድ ጥሪና ቪዥን ግን ያስደነግጣል። ስለምን? ከኢህአዴግ ውስጥ እንደምን ቢሆን ቪዢነሪ ሊወጣ ይችላል? በምዕራቡ ዓለም የሚገኙትን ድንቅና ክቡር ሳይንቲስቶቻችንንና ተመራማሪዎቻችንን ዕውቅና ከመስጠትና ከማክበር ማዶ ነገ ኢትዮጵያን በዓለም የሳይንስና የቴክኒዮሎጂ ማማ ላይ የሚያቆሙ ናቸው ብሎ እንደምን ኢህአዴጋዊ ሊመሰክርና በፍፁማዊ ዕምነትም ሊናገር ቻለ? እንደምንስ ቢሆን ነው ኢህአዴጋዊ ስለ አባቶች ታሪክ በክብርና በኩራት ለመናገር የበቃው? መለስና የመለስ ሌጋሲ የኢትዮጵያ ታሪክ የደብተራ ታሪክ ነው አይደለም እንዴ የሚለው? ብዙ መጠየቅ ይቻላል። ምክንቶቹን መተንተን ግን ከንቱ ነው።

አዎ ወጣቱ አብይ አህመድ ኢህአዴግ ነው። ህወሃት ወይም ህወሃታዊ ግን ከቶም አልነበረም። ህወሃትና ህወሃታዊነት ዲያብሎሳዊነት ነው። ሰውን ‘በወርቅ’ እና ‘በመዳብ’ መመደብ። ዘወትር ክፉ ማሰብና ክፉ ማድረግ። ይህ የህወሃት ተፈጥሮ ደግሞ ከቶም አይለወጥም። ህወሃታዊነት ማለትም የመለስን ሌጋሲ ለማስቀጠል ነው ጠ/ሚኒስትር የሆንኩት ያሉትን ሃይለማርያም ደሳለኝን መሆን ማለት ነው። አባ ዱላ ገመዳን መሆን ማለት ነው። ሲራጅ ፈጌሳን መሆን ማለት ነው። አብዲ ኢሌን ሽፈራው ሽጉጤን አለምነው መኮንንን የጥፋትና የርኩሰት አጋፋሪውን በረከት ስምዖንን መሆን ማለት ነው። ህወሃት ከፅድቅ መንገድ ሰው ያስወጣል እንጂ ሰውን ወደ ፅድቅ አይመራም። ህወሀትና ህወሃታዊነት ማለትም ሰዋዊ ባህሪንና ተፈጥሮን አውልቆ የጣለ የጥፋትና የሴራ ማዕከል ማለት ነው። ህወሃት የዘረኝነትና የክፋት አልፋና ኦሜጋ ነውና።

ከኦህዴድ ማህፀን የወጣው ቲም ለማ መገርሳ ግን ከህወሃትና ከህወሃታዊነት ያልተላቆጠ የዲየብሎስን ስጋና ደም ያልወሰደ ነው። እንዴት ነው ታዲያ እኒህ ሁለቱ በኢህአዴግ ማዕቀፍ በአንድ መድረክ የቆሙት? ይህ እጅግ ውስብስብ የሆነ ሰው የመሆን ልዕለ ሰብዕና ባላቸው የቲም ለማና በእግሩ ለመቆም እግረ ወርቹን እየፈታ ያለውን የቲም ገዱን ኢህአዴጋውያንና ሰው መሆንን አውልቀው የጣሉ ህወሃትና ህወሃታውያን በአንድ መድረክ ላይ የሚስተናገዱበት የኢትዮጵያ ብቻ የሆነ በኢትዮጵያም ብቻ የተከሰተ ፖለቲካዊ ‘ፓራዶክስ’ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ ካልሆነ በቀር ይህንን ፓራዶክስ /ተቃርኖ/ ሊተነትንም ሆነ በቅጡ ሊረዳው አይችልም። የቲም ለማ ብርታትና በራስ መቆም ለቲም ገዱ ብርታትና በራስ መቆም ከዘራ ሆኗል። ኦቦ ለማ መገርሳ ቲሙን አስከትሎ ወደ ሰሜን በማቅናት ባህር ዳር ገብቶ በኢትዮያ ሰማይ ደመና ውስጥ የተሸሸገውን የኢትዮጵያዊነት ኮከብ ከተሸሸገበት ሄዶ በታላቅ አክብሮትና ግርማ ሞገስ ወደ ዙፋኑ ከመለሰው ወዲህ በህወሃት መዳፍ የተመራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የ27 ዓመት ጥቀርሻ የሚጠረግበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል። አብይን የምንፈልገውም በቲም ለማ ውስጥ በመገኘቱ ነው። ኦቦ ለማ መገርሳ እንደ ወተት የረጋ እንደ ቅቤ የበሰለ ቪዢነሪ መሪና መካሪ ነው። አብይን ያገኘነው በቲም ለማ የቪዝን ቃል ውስጥ ነው።

ቃል ጉልበት አለው። ይተክላል ይነቅላል፤ ትውልድ ይፈጥራል ትውልድ ያጠፋል፤ ፍቅር ይዘራል ጥላቻ ይዘራል። በቃል ውስጥ ሀገርም መስራት ይቻላል። ኢትዮጵያ የተሰራችውም የፈረሰችውም በቃል ስለሆነ፤ – አብይ አህመድ ነው የቃሉ ባለቤት። ፍልስፍናዊና ምናባዊ ነው – ቃሉ። ለምሳሌም ወደ ምድር ሲወርድ ኦቦ ለማ መገርሳ ማንነትን እንዲህ ተርጉሞታል ፤ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው። ይህ ቃል – የተነቀለን ማንነት መልሶ ተክሏል፤ የጠፋን ትውልድ አግኝቷል። እየፈረሰች የነበረችውን ኢትዮጵያ መልሷል። በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ በዘር እንዲጠፋፋ የተደረገውን ኦሮሞውንና አማራውን ሌላውንም የኢትዮጵያ ልጅ ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ እንደ ችቦ አስተሳስሯል። ከሰሜን አሜሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተበተነውን ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ሲቃ አስለቅሷል። ህወሃትንና ህወሃታውያንን ግን አስበርግጓል። አዎ የኦቦ ለማ መገርሳ ቃል ጉልበት ሆኗታል፤ ኢትዮጵያ። የህወሃት እሳትና ጭድ ሴራ በቲም ለማ መገርሳ ማጭድና በቲም ገዱ አንዳርጋቸው መንሽ ተበራይቶ ተበትኗል። አፓርታይዳዊው የህወሃት የሥልጣን ምርኩዝ ተሰብሯል። አሁን የህወሃት ጥድፊያ የተሰበረውን ምርኩዝ ለመጠገን ነው፤ ሁሉ ከንቱ በሆነበት የመጨረሻው ሰዐት። የተጠገነ ዕድሜው አጭር መሆኑን መካሪ አጥቷል ወያኔ።

የህወሃት የበላይነት ማብቂያ ደወል የተደወለው አስቀድሞ ጎንደር ላይ በ2008 ዓ/ም ነበር። ትንታጉ የአማራው ወጣት ፋኖ “የኦሮሞው ደም ደሜ ነው! በቀለ ገርባ መሪያችን ነው!” ያለ ጊዜ። ህወሃት ‘ማይግሬን’ የሆነ ራስ ምታት የያዘው ያኔ ነበር። ወደ ዕብደት የተለወጠው ደግሞ ኦቦ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ በኦሮሞ ወጣት (ቄሮ) “ጣና ኼኛ” የተባለ ኢትዮጵያዊ መዝሙር ከኦቦ ለማ መገርሳ ኦህዴድ መውጣቱን ባበሰረበት መልዕክቱ ነበር። ገዱ አንዳርጋቸውና ቲሙ ድፍን ፋኖን (የአማራውን ወጣት) እና ምሁር፤ አዛውንትና ባልቴት አሰልፎ በዘንባባ ዝንጣፊና በቄጤማ ጉዝጓዝ የጠፉበትን ወንድምና እህቶቹን አክስት አጎቶቹን ጓደኛ መምህሮቹን በነቂስ ወጥቶ ተቀበላቸው። በውጪና በውስጥም ያሉ አርቀው ማሰብ የተሳናቸው ፅንፈኞችና ሟርተኞች ሁሉ እንደ ማለዳ ጤዛ የሚረግፍ ጥሪና ህብረት ነው አሉ። ህወሃትም ዕውነት መሰለው። የሁለቱ ህብረት ደወሉ እስከ አራት ኪሎ አስተጋባ። ሀጫሉ ሁንዴሳ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ደርሰናል ሲል በሚለኒየም አዳራሽ ሸለለ።

የህወሃት ብሮድካስት ባለሥልጣኑ ዘርዓይ አስገዶም በባህር ዳር ሰማይ ስር በቴዎድሮስ ካሳሁን ስለገዘፈው ኢትዮጵያ ዜማና በሚሌኒየም አዳራሽ በሀጫሉ ስለተነገረው የጀግኖች ታሪክና የአራት ኪሎው ትንቢት ራሱን በጥብጦት በቴሌቪዥን ቀርቦ ሲደነፋ ዋለ። የሀጫሉ ሽለላ ግን ሽለላ ሆኖ አልቀረም። ኦቦ አብይ አህመድ ከምኒልክ መንበር ገብቷልና! የቴዲ አፍሮም ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ማዜም እነሆ በዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ውብና ምጡቅ ንግግር በምክር ቤቱ ውስጥ ኢትዮጵያ ተሞሽራ ክብረ በአሏ ሲታወጅ ህወሃትና ህወሃታውያን ሁሉ ቆሌያቸው ተገፎ ዋለ። አብይ ኢትዮጵያን በቃል ኪዳን ቃል ባረከ!! የኢትዮጵያ ህዝብም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ አብይን አለ። በ27 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትራቸው በአደባባይ ተወደሱ፤ ተከበሩ ተባረኩ።

የኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኒዮሎጂ ምኒስትር የነበረው አብይ አህመድ በእስራኤል ጉብኝቱ ከቤንጃሜን ናታንያሁ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ እስራኤል ተጠይቆ ሲመልስ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ዛሬ እስራኤል ያለችበትን ሁኔታ ስናይ ትላንት ተደምረው ነፃነታቸውን አውጀዋል። ዛሬም በመደመር፤ ዕውቀትን በመደመር፤ ሀብትን በመደመር፤ ሀሳብን በመደመር የላቀ ሀገር ሆነው ማስተማር ችለዋል። እኛ ሰው አለን። መሬት አለን። ውሃ አለን። ያጣነው ጥበብን መሻት፤ ጥበብን መፈለግ፤ ጥበብን መደመርና መዋደድ፤ በአንድ ልብ ሀገርን ማልማት ነው። እሱን ማምጣት ከቻልን ተዓምራዊ የሆነ ነገር ተፈጥሮ ኢትዮጵያ የብዙ ሀገራት መሰብሰቢያ ትሆናለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ደግሞም (ሆኖ) እናየዋለን።

ኢትዮጵያ በመደመር ተአምር የሚታይባት ሀገር ትሆናለች ያለው አብይ ለካስ አፋዊ ጀብደኝነት አልነበረም። አብይ መልሶ ሰልሶ ይናገር የነበረው የመደመር ራዕያዊ ግብ ሁሉ በራሱ ጊዜ ዕውን ሆኖ እነሆ ይታይ ዘንድ ልጓሙን ጨብጧል። መደመርን የሚደምር መሪና ድርጅት በህወሃት ቀለበት ውስጥ ሌላ ቀለበት ሆኖ ተፈጥሮ ገዝፏል። የለማ መገርሳና የገዱ አንዳርጋቸው ጥምረት በምታ ነጋሪት ንፋ መለከት አዋጅ የመጣ አለመሆኑን አደብ ገዝቶ መመልከትና መስማትም ተገቢ ነው።

በቀደመው ጊዜ እምብዛም የማይታወቀው የቲም ለማ አካል ነገር ግን የህወሃት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኮማንድ ፖስቱ ጁንታ በሞያሌ ንፁሀን ዜጎች ላይ በጠራራ ፀሀይ ያደረገውን ጭፍጨፋ በአለም ፊት አጋልጦ በመናገሩ በህወሃት ኮማንድ ፖስት ለእስር የተዳረገው የኦህዴዱ የፍትህ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ባለሥልጣን ኦቦ ታዬ ደንድአ ከታሰረበት ሆኖ በአብይ መመረጥ እንዲህ ብሏል፤ እመኑኝ ኦሮሚያ መቼም ከአማራ ልጆች ተለይታ አትኖርም። አማራ ያለ ኦሮሞ፤ ኦሮሞም ያለ አማራ መኖር አይችልም። ይሄንንም በደንብ ከእዚህ በፊት በተለያየ መድረክ አሳይተናል። ይሄንንም በአብይ ምርጫ ላይ {እነ ገዱ} አሳይተዋል። ከእዚህ በፊት የተዘራብንን የሁለታችን የማራራቅ ተግባር በቅርብ ጊዜ አከርካሪውን ሰብረን አንድ እንደሆንን አሳይተናል። {ብአዴኖች} አብይን ቢመርጡ ቀድሞ ከተሠራው ሥራ አንፃር {እንጂ} ምንም የተለየ ነገር አይደለም። ገዱና ንጉሱ ጥላሁን ብአዴንን ማንቃታቸው ለአብይ ጥሩ ሆነለት። ገዱ አንዳርጋቸው ጠንካራ፤ ንጉሱ ጥላሁንም ሁለቱም ጎበዝ ናቸው። ከስር ደግሞ ያሉ ወጣቶች ከምታስቡት በላይ ጎበዝ ናቸው። እድሉን ሲያገኙ {ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ} ታዩታላችሁ። ገዱ ይሄን እንደሚሠራ አልጠራጠርም ነበር። ግባቸውን መተዋል፤ በማለት በልበ ሙሉነት ቃሉን ሰጥቷል በጎልማሳ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ኦቦ ታዬ።

ዛሬ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለእኒህ በህወሃት ቀለበት ውስጥ ድምፃቸውን አጥፍተው ሲሰሩ በመኖር አብይን ለምኒልክ ቤተ መንግሥት ያበቁትን ሩቅ ዓላሚዎች ጊዜ ሰጥቶ ሊሰማቸው፤ ሊያግዛቸውና ሊያበረታታቸው ደጀንም ሊሆናቸው ይገባል። በአብይ መንገድ ላይ ጉርጓድ የሚቆፍሩና አሜኬላ የሚያነጥፉ ብዙዎች ህወሃታውያን ሀይላት አሉ። ሁሉም ግን ከኢትዮጵያውያን ህብረትና ሀይል አይተካከሉምና የአብይ ፍኖተ ካርታ ይፋ እስከሚሆን ድረስ ጉርጓዶቹን ልንደፍን ከአሜኬላዎቹም ልንጠብቀውና ልናስጠነቅቀውም ግድ ይላል። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህወሃትንና ህወሃታውያንን ረቂቅ አሳቢዎች እያደረጉ የሚያቀርቡ የሴራ ተንታኞች ፅሁፎች በተለይ ዛሬ ላይ ፋይዳቸው የተለመደው ሟርት ብቻ ሳይሆን የህዝብንም ስሜት ጎጂ ነውና ሊታቀቡ ይገባል። ዕውቀቱና መረጃው ያላቸው ፀሀፍት ግን በአመክንዮ ሀሳባቸውን ይፋ ማድረጋቸው ትግሉን አጋዥ እንጂ ሟርት አይሆንም።

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ለዘመናት ሲያራምደው የቆየው ፅኑዕ አቋም፤- ሀገር በቀል ኮሎኒያሊስቱን ህወሃት ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ለማንሳት አስቀድሞ የተቀመጠባቸውን ሶስቱን ጉልቻዎች (ኦህዴድ፤ ብአዴን፤ ደህዴን) ማንኮታኮት ያስፈልጋል – የሚል ነበር። ከጣና ኬኛ ኢትዮጵያዊ ዘመቻ እና ከኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው መሪ ኮከብ ቃል ወዲህ ግን ናዚስት ህወሃትን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ለማስወገድ ጉልቻዎቹን ማፍረስ ሳይሆን መቀየር እንደሚያዋጣ በህወሃት አፍንጫ ስር የተካሄደው የኦህዴድና የብአዴን ጥምረት (ጉድለቶቹ እንዳሉ ሆነው) ውጤታማ ስለመሆኑ ሀተታ የማያስፈልገው ዕውነታ ነው። የእንቁላሉን ሼል ከውስጥ ሰብሮ እንደወጣ ጫጩት የሚመሰለው ይህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁን በደረሰበት ደረጃ መጠነ ሰፊ ጥፋትና የህይወት ዋጋ ሳያስከፍል ባለድርሻ አካላትን ሁሉ አቅፎ ወደ ተራራው ይወጣ ዘንድ ሁሉም ሊጥርና ዘብ ሊቆም ግድ ይላል። ችግሮቻችን ቁልል አሜኬላውም አሸን መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይቻልምና።

ዶ/ር አብይ አህመድን ከነደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከነበረከት ስምዖን ከነሽፈራው ሽጉጤና ከነአብዲ ኢሌ እኩይና ናዚስታዊ ሴራ መረብ በጥሰው ያወጡት አንድ መቶ ስምንቱ “የለውጥ ሃዋርያት” ለነገይቱ ኢትዮጵያ ትንሳዔ ያበረከቱት ኢትዮጵያዊ ድርሻ ቀላል አይደለምና አክብሮትና ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በተለይ የህወሃት ‘መጋለቢያ’ ከሚባለው ደህዴን ያፈነገጡትና ከነለማ መገርሳና ከነገዱ አንዳርጋቸው ጋር የወገኑት ህወሃታዊ ሥርዐቱን ከውስጥ ወደ ውጪ መናድ እንደሚቻል ያረጋገጡ ፈርጥ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

የህወሃትን የአስራ አንደኛ ሰአት ስሌት የሥልጣን ፕወዛ በማድረግ በቆረጣ የጣለው የለማ መገርሳ ኦህዴድ አርቆ አሳቢና በርግጥም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለውጥ ለማምጣት ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድም አሳይቷል። አብይን ስንፈልግ የምናገኘው በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ነው። ኦቦ ለማ መገርሳ ሥልጣኑን ለዶ/ር አብይ ሲያስረክብ ይታየው የነበረው የሀገር ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ብቻ ነበር። ለዚህም ነበር፤- የሀገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ከግለሰቦች ክብር በላይ ነው፤ ከባለ ሥልጣናት ክብር በላይ ነው፤ ከቡድኖች ክብር በላይ ነው- በማለት የተናገረው።

በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን የሥርዐት ችግር ከላይ ሆኖ ምንጩን ማድረቅ ይመኝ የነበረው አብይ አህመድ ከዚህ ጋር ባልተያያዘ የጥበብ አውድ ላይ ተገኝቶ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ንሥር አሞራ በሠማይ ካሉ አእዋፋት ሁሉ የተለየ ባህሪው ዝናብ ሲመጣ ሁሉም የአእዋፋት ዘር መጠለያ ይፈልጋሉ ይደበቃሉ፤ ንሥር አሞራ ግን ዝናብ ሲያይ ከዳመና ጥሶ ያልፋል። የዝናብን ምንጭ ወደታች ያያል። የችግርን ምንጭ ወደታች ማየት ያልቻለ ማህበረሰብ በፍፁም አይሸጋገርም። ዕውቀትና በጎ አመለካከት ሲደመሩ ማህበረሰብ መቀየር ይችላሉ። እነሆ ጠ/ሚኒስትር አብይን ፈልገን የምናገኘው በእኒህና እኒህን በመሳሰሉ አያሌ ንግግሮቹ ነው። ቃል ይተክላል፤ ቃል ይነቅላል፤ በቃል ውስጥ ሀገርም መስራት ይቻላል – እንዲል። እንግዲህ እንደ ንሥሩ አሞራ በኢህአዴግ አናት ላይ ይቆም ዘንድ አንድ መቶ ስምንቱ የህዝብ አጋሮች በትረ ሥልጣኑን ሰጥተውታል። ምክር ቤቱም በሀሴት አፅድቆ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተቀብሎታል። ሥልጣኑ የሙሴ በትር እንዲሆንለት ኢትዮጵያን የሚል ሁሉ ጊዜ ሊሰጠውና ሊደግፈው ያሻል።

በአብይ ፆም ሱባኤና ፀሎት የተገኘውን ‘ሙሴ’ የኢትዮጵያ ህዝብ ወዶታል። የ2010 ዓ/ም ትንሳኤም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብና የውዲቱ ኢትዮጵያ ትንሳኤን እንደሚያመጣ እንደሚሆንም ከዚህ በላይ ምልክት አይኖርም። ጠ/ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያን እናቶች ከአፅናፍ አፅናፍ በአንድ ጀንበር አጋምዶና ደምሮ ከጎኑ አሰልፏል። ጠ/ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያን ሴቶች ከአፅናፍ አፅናፍ በብሩህ ተስፋና በመደመር መርሁ የተልዕኮው ደጀንና ፊታውራሪ ሊሆኑ ተሰልፈዋል። 65 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ‘ኢትዮጵያ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ ተስፋ የምታስቆርጥ ሀገር አትሆንም’ የሚለውን የአብይን ቃል አንግቦ ለተልዕኮ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል። በአብይ የመደመር ተልዕኮ ውስጥ ጋሬጣ ለመሆን የሚቆም እነሆ ልብ ካለው ልብ ይበል!!

አባቶች መካሪ አታሳጣኝ ይላሉ። በበኩሌ ዶ/ር አብይን ለመምከር የወረደውን የፀሀፊና የምክር ሊስት መዐት ስመለከት ግን – ጌታ ሆይ መካሪ አታብዛብኝ – የሚል ፀሎት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ በአብይና አብይን ወደላይ ባወጡት ጓዶቹ ፍፁም ትጋትና ትግል ህዝብን በመደመር ወደ ብርሃን ዘመን ትሸጋገራለች የሚል የበረታ ተስፋና እምነት አለኝ። ይህ ባይሆን ግን ፍሬን የያዘው ህዝባዊ ትግል ፍሬንኑ በጥሶ በሙሉ ሀይል እንደሚምዘገዘግ የመጀመሪያው መስካሪ ራሱ አብይ እንደሚሆንም ያለ ይሉኝታ መናገር ይቻላል። ለዚህም ነው በዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ብርሃናዊ ሙቀት የሚሰጥ ተስፋ እንጂ ስጋት የሌለኝ። ስጋት የሚመነጨው ያልነበረ ነገር ይከሰታል ከሚል ፍርሃቻ ነውና። በዚህ ወቅት ከእነ ገዱ ካምፕ የዝምታ ድባብ መስፈኑ እኒህ ወገኖች በውስጣቸው የመሸጉትን በርካታ የቀበሮ ባህታውያን በአስተማማኝ መንገድ የሚያፀዱበትን በዝምታ እየሰሩ ያሉ በመሆናቸው ይመስላል። ለረዥም ዘመን የጥቃትና የዕልቂት ክንድ የሆኑትን ግልፅና ስውር ቀበሮዎችን ማፅዳት ይጠበቅባቸዋልና፤ በዝምታ ሥራቸውን መቀጠላቸው ሊደገፍ ይገባል። እናንት የደህዴን ባለውለታዎቻችንንም ‘ብዙ ተባዙ፤ ህዝባችሁንም ደምሩ’ እንላለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በፓርላማ ካደረገው እፁብ ንግግር በላይ ደግሞ ይህንን ፅሁፍ አቅራቢ የመሰጠውና የአብይን ታላቅነትና የመደመር ተልዕኮ ቁርጠኝነት ‘በእርግጠኝነት ለመመስከር’ ያነሳሳው ለአጭር ደቂቃ በምኒሊክ ቤተ መንግሥት ውስጥ በጠ/ሚኒስተር ቢሮ ግርማዊነታቸውን ባስታወሰኝ የእጅ ጣት ምልክት የሰጠው አክብሮታዊ ቃል ነው።

በምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ የመጀመሪያው ቃለ ምልልሱ የምኒልክን ታላቅ መሪነትና ዘመን ተሻጋሪ አስተዋፅኦዋቸውን በማወደስና በማመስገን ነበር። ኢያሱን አመስግኖ ግርማዊነታቸውንና ታላቅ ሥራቸውን ዘክሮና አክብሮ የደርግን ሥርዐትም በጎ ጎኖች አወድሶ አቶ መለስ ዜናዊን በተገቢው መንገድ ዘክሮ በአቶ ሀይለማርያም መልካም ሥራ ደምድሟል። እግዚአብሄር ይባርክህ! መምህር ማለት ይኸው አይደል ትርጉሙ?

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ሆይ! በቃልህ እንዳሳመንከን በቃልህ ደቀ መዝሙርህ እንዳደረግኸን በቃልህ እንደተከልከን ቃልህ ፍሬ ሆኖ ይበቃ ዘንድ ምኞታችንና ተስፋችን ብቻ ሳይሆን በመደመር ከጎንህ በመቆም ዕውን እንዲሆንም እንፈልጋለንና እግዚአብሄር ብርታቱን ለአንተና አንተን ለዚህ ላበቁህ ቅን የኢትዮጵያ ልጆችና መሪዎች ሁሉ ይሁን፤ አሜን!

እግዚአብሄር አትዮጵያን በጎ አሳቢ ልጆቿንና ቅን ዓላሚ መሪዎቿን ይጠብቅ!!

ተፃፈ መጋቢት 30/2010 ዓ/ም (April 2018)

ሲድኒ አውስትራሊያ

mmtessema@gmail.com

LEAVE A REPLY