”ቢቢሲ ሃርድ ቶክ” ቆይታ ህወሓት እና “የብሄራዊ ጥቅም” /ነአምን ዘለቀ/

”ቢቢሲ ሃርድ ቶክ” ቆይታ ህወሓት እና “የብሄራዊ ጥቅም” /ነአምን ዘለቀ/

በቅድሚያ ምስጋና፦
ባለፈው ሳምንት በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆነው የቢቢሲ ሃርድ ቶክ/BBC Hardtalk ጋር ቆይታ ማድረጌ ይታወቃል። የፕሮግራሙ ይዘት ጠንከር ያሉ ሙግቶችን ተሞርኩዞ ምላሽ የሚሰጥበት በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚደፈር አለመሆኑም ይተወቃል። ወደ ኋላ ሔዶ ለማስታወስ ያህል የፕሮግራሙ አዘጋጆች ከወያኔ ቁንጮ ከነበረው ሟቹ መለስ ዜናዊና የቅንጅት ሊ/መንበር ከነበሩት ኢንጂነር ሐይሉ ሻወል ጋር እንደዚህ አይነት ፖለቲካዊ ሙግት ያደረገው የዛሬ 12 አመት በምርጫ 97 ማግስት ነበር። ከዛ ወዲህ በአገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚዲያው ቀርቦ ሙግት የገጠመው ኢትዮጵያዊ አላስታወስም።

ይህን በመመልከት ይመስላል የንቅናቄያችን አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች፤ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶት ውስጥ ያላችሁ አመራሮችና አባላት፤ የስርአት ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያንና በርካታ ምሁራ ስሜታችሁን ገልጻችሁልኛል። በአካል፣ በስልክ በማህበራዊ ድረ-ገጽና አስተያየቶች ደርሰውኛል። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሚሰጡ ድረ-ገጾች እንዲሁም እንደ ኢሳት ያሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት “የቢቢሲ ሃርድ ቶክ” ፕሮግራሙን ተመስርተው ውይይትም በማድርግ በተለያየ ምልከታዎችን እንዳይ ስላደረጋችሁኝ በድጋሚ ለድረ-ገጾቹም ሆነ ለሚዲያ ተቋማቱ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ለሰጣችሁኝ አበረታች ግብረ-መልስ ላቅ ያለ ምስጋናዬን ከወዲሁ ማቅረብ እወዳለሁ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አክብሮታችሁን የላካችሁልኝ የንቅናቄያችን አባላትም ሆነ የተቀራችሁ ኢትዮጵያውያን አንድ ነገር አስምሬ ልነግራችሁ የምፈልገው ጉዳይ አለኝ። ኣኔ ብዙሃን ወደማይደፍሩት የቢቢሲ ሞጋች ፕሮግራም ላይ ለመቅረብ ፍቃደኛ የሆንኩት ዋነኛ ምክንያት በመኖሩ ነው። ይኸውም አመራር የሆንኩት አርበኞች ግንቦት ሰባት ነድፎ የሚታገልባቸው የማታገያ ነጥቦች መዳረሻ ግልጽ ስለሆኑ ነው። ለሁሉም ግልጽ ኣንደሆነው ንቅናቄያችን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ አንድነት፣ እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅም ለድርድር የሚያቀርብ አይደለም።

ንቅናቄያችን የኢትዮጵያ መኖር ከማንኛውም ጉዳይ በላይ ወሳኝ መሆኑን በማመን የንቅናቄያችን ታጋዮች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፣እየከፈሉም ይገኛሉ። ንቅናቄያችን አገር ለማዳን በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ከሌሎች የነጻነትና የዴሞክራሲ ሐይሎች ጋር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከዘለቄታው ሃገራዊ ጥቅም ጋር ለማስከበር በጋራ መርሆዎች ላይ በመተባበር በጽናት የሚሰራ ነው። በንቅናቄያችን ውስጥ ያለን አመራሮችም ሆነ አባላት የጥንካሬ ምንጭ የሚቀዳው ከዚህ እውነታ ነው። አይደለም በአገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ታዋቂ በሆኑ በሚሊዮኖች በሚከተሏቸው የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ፊት ለፊት ወጥተን መሟገት የቻልነው ንቅናቄያችን ትክክለኛ አላማና ግብ በማንገቡ ነው። የምንከተለው የትግል ስትራቴጂና ስልትም መዳረሻችንን እንደ መስታወት አቅርቦ የሚያሳየን ነው።

ህወሓት፣ እና “የብሄራዊ ጥቅም”-

በሌላ በኩል የቢቢሲ ሞጋች ፕሮግራም መቅረቤን ተከትሎ የትግራይ ነጻ አውጪ አባላትና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው የተለመደና የነተበ የቅጥፈት ፕሮፖጋዳ ዘመቻቸውን በአዲስ መልኩ ጀምረዋል። ለጠባብና ዘረኛ ቡድናቸው የፖለቲካ ማስጠበቂያ ይሆናል የሚሉትን በተዛባ ሁኔታ በመውሰድ አይናቸውን በጨው አጥበው መጥተዋል። ትላንት ለጋራ ጥቅምና ፍላጎት በቂ ውይይትና ድርድር ማድረግ ተስኗቸው የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ መጣላቸው የተረሳ ይመስላቸዋል፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም “national interest” ፍላጎት ዋና አስጠባቂ ለመምሰል የቀበሮ ባህታዊ ሆነዋል።

እነዚህ ጠባብ የትግራይ ጎጠኞች ጸረ-ኢትዮጵያዊ ባንዳነታቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ የረሳላቸው መስሎአቸው የሰሩት ታሪክ፣ “ሚኒሊክ በሳንጃ የሰበሰባትን እኛ ለመጠበቅ ሃላፊነት የለብንም” በማለት ኢትዮጵያን የወጉ ናቸው። ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ወቅት ሙዋቹ መለስ ዜናዊና ሌሎቹ የወያኔ መሪዎች ከጠላት ጎን በመሰለፍ በሶማሊያ ፓስፓርት ሞቃድሾ በመመላለስ ኢትዮጵያ በባእድ ጦር ስትወረር ለመበታተን የተባበሩ ናቸው። ከውስጣቸው የመነጨው ዶክተር አብይ ምስጋና ይግባውና ትላንትና ከወራሪው ሱማሊያ ጦር ጋር ሲፋለም በካራማራ፣ ሀረርጌ ላይ ከሶማሌያው ሲያድ ባሬ ጦር ጋር ሲዋጋ የተሰዋውን ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች የቀድሞ ሰራዊት አባላትና እነ አሊ በርኬን የመሳሰልይ የላቁ ጀግኖች ያፈራውን የሚሊሽያ ሰራዊት ታሪክ እንዲታወስ አድርጓል።

የትግራይ ነጻ አውጪዎች በጠመንጃ ስልጣን ከያዙም በኋላ “አክሱም ለወላይታው ምኑ ነው? ላሊበላስ ለጉራጌው?” በማለት ከፋፋይና ዘረኛ ፖሊሲያቸውን በግልጭ ሲያራምዱ እንደነበር በአደባባይ የተሰጣ እውነት ነው። ለኤርትራም ከኤርትራውያን በላይ የተዋጋን፣ የታገልን ነን፣ እያሉ አረፋ እየደፈቁ ሲጎማለሉ የነበሩት የህወሓት የጡት አባት እነ ስብሀት ነጋ አይደሉም ወይ?

የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበረው አምባሳድር ሔርማን ኮሂን እንደመሰከረው አሰብ ከኤርትራውያን ጋር መደራደር ሲችል ፣ ኢትዮጵያን የባህር በር እና ወደብ አልባ ያደረገት ፣ በኋላም ይህን የወያኔዎች ስትራቴጂካዊ ድድብና የሚያረጋግጥ ግዙፍ ወንጀል ለመደበቅ ለኢትዮጵያ “ብሄራዊ ጥቅም “ወደብ ሸቀጥ ነው፣ ቀይ ባህርንም ግመሉን ያጠጣበት” በማለት ሲመጻደቅብን ከርሞ ህይወቱ ያለፈው የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊና ህወሓት ነበሩ።

የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ አከብራለሁ። የወያኔ ሰለባ ነው ብለን እናምናለን። ወያኔዎች እንደሚሰብኩት የትግራይ ህዝብና ወያኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታም እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ወያኔዎች ይህን በየጊዜው በመለፈፍ ሊያሳምኑ ቢሞክሩም። ሆኖም ወያኔዎች 60 ሺ የትግራይ ልጆች መስዋእትነት ከፈልን በማለት ነጋ ጠባ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያቅራሩትበት መነሻ አላማ ለትግራይ ሪፑብሊክ፣ ለ”አባይ ትግራይ” ግንጠላና ምስረታ እንጂ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የተከፈል መስዋእትነት አለመሆኑ ሊታወስ፣ ሊሰመርበትም ይገባል። ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለፍትህ ፣ ለመብት፣ ለእኩልነት ተሰውተው ቢሆን እንኳን እሰየው ባልን ነበር። እነሱ ግን እኛ ስለተሰዋን በእሳት የተፈተንን“ወርቅ ነን”፣ ስለዚህም ሌላው ኢትዮጵያዊ –ኦሮሞው፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ጋምቤላው፣ አፋሩ፣ ወዘተ– ጨርቅ ስለሆነ የወርቅ ዘውድ በመሆን አናቱ ላይ ተፈናጠን እያዋረድነው፣ እየዘረፍን፣ እየገደልን፣ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራና የበታችነት የህወሃት ትግራውያንን የበላይነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ እናስቀጥላላን ብለው 27 አመታት በላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የኢትዮጵያን ህዝብ ደምና አንጡራ ሃብት የሚመጠምጡ የህወሓት ትግራዮች ናቸው።

ይህን አስከፊና ዘግናኝ የሆነ ጸሃይ የሞቀውን የህወሓት ትግራዮች የበላይነት ካላስቀጠልን ደግሞ ኢትዮጵያን ብትፈራርስ ቁብም እንደማይሰጣቸው በአደባባይ የሚነግሩን አሁን እነሱ ናቸው። ኪዚያም አልፈው ኢትዮጵያን እናፈርሳለን በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ የአገር የመበታተን አደጋ ስጋት ወስጥ ለመጨመር ያለ ቅንጣት ሀፍረትና ይሉኝታ በአደባባይ እነአባይ ጸሃይና ስዩም መስፍንን ጨምሮ የሚናገሩ የነሱ መሪዎች ናቸው።

የጦር ፖሊሲን እንደ የውስጥ ጭቆና ማዳፈኛ የሚጠቀሙበት ህዉሃቶች 1998 በፈረንጆቹ አቆጣጠር “ሉዓላዊነትህ ተደፈረ፤ ሻዕቢያ ባድመን ወረረ” በሚል ሲያንኩዋስሱትና ሲያጥላሉት የነበሩትን የኢትዮጵያዊነት ካባ የለሀፍረት ደርበው ህዝቡን ቀሰቀሱት። 21ኛው ክፍለ-ዘመን ላይ ያለን በማይመስል መልኩ አለም ጉድ እስኪል ድረስ ወጣት ኢትዮጵያውያን የፈንጂ እራት ተደረጉ። በወቅቱ የኤታማጆር ሹም የነበረውን ጄ/ል ጻድቃን ወ/ተንሳይን እንባ አውጥቶ ያሰለቀሰ በደናቁርት የህወሓት ትግራይ ጀነራሎች አዝማችነት በተደረጉ በርካታ የመጀመሪያ ዙር ውጊያዎች በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ልጆች ህወታቸው ተቀጠፈ። ፈንጂ ረጋጭ ያደረጉት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች- የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የጉራጌ፣ የጋምቤላ የሌሎች ብሄር ልጆች– እንዲሁም ለውርደትና ለልመና የዳረጉትን የቅድሞ ሰራዊት አባላትና ጀነራሎች በአስርቱ ሺዎች በድረሱልን ልመና አምጥተው አዘመቱ።

እናም በ11ኛ ሰአትም በቀድሞዎቹ የሰራዊት አባላት፣ አዛዦችና የኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ብርታትና መስዋእትነት ውጤቱ ወደ ኢትዮጵያ ሊያዘም ቻለ። በወቅቱ ውያኔ ከኤርትራ ጋር ባደረገው ጦርነት ከ96 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ የጦርነት አላማ፣ “ባድመ” የማን ለማንስ “ብሄራዊ ጥቅም” መሆኑን በማያውቁት ጦርነት ህይወታቸውን ገበሩ፣ እካለ ጎዶሎም ሆኑ። ለዚያውም ከጦርነቱ በሁኋላ ሟቹ የውያኔ መሪ “ ኣባታቸውን የሞተባቸውን ማን ያመጣቸው” በማለት የቀድሞ ሰራዊት አባላትና የወታደራዊ አዛዦች በድጋሚ እንዲባረሩ ማድረጉ ይታወሳል። ይህን ዳግም የተፈጸመ ክህደትና ጭካኔ ለማይረሱ ፣ የወጋ ቢረሳ… ነውና ።

በሌላ በኩል የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት እልባት ለመስጠት የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሜሪካ መንግስት…… ወዘተ ባደረጉት ጥረት የባድመን የባለቤትነት ጉዳይ ለመዳኘት ወደ አለም አቀፍ ፍርድቤት ለመሄድ ስምምነት ተደረሰ። የትግራይ ነጻ አውጪ መንግስት መሪዎች የአለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ከኤርትራ መንግስት ጋር ተፈራረሙ። እናም በሔግ በተደረገው ክርክርና ብይን ባድመ ለኤርትራ ተብላ በድንበር ኮሚሽኑ ተወሰነች። ወያኔዎች በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበረው ስዩም መስፍን በአደባባይ ነጭ ውሸት የኢትዮጵያን ህዝብ አሳስቶ “የጦርነቱ ድል በፍርድ ቤትም ተደገመ” በሚል በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እስከማስወጣት ደረሰ። በውሸታሞች እውነት ተደብቃ አትቀርምና የትግራይ ነጻ አውጪ ቅጥፈት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጋለጠ። እንግዲህ ሐቁ ይሄ ነው።

ሁላችንም በቅርበት እንደተከታተልነው የኤርትራ መንግስት በሁለቱ አገሮች መካከል ውይይትም ሆነ ድርድር የሚጀመረው “የሕግ የበላይነት” ሲከበር ብቻ እንደሆነ ደጋግሞ አሳውቋል። ይግባኝ በሌለበት የአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የተወሰነው ውሳኔ ወደ ተግባር እንዲቀየር የአለም መንግስታትን አሳስቧል። እኔም በቢቢሲው ሞጋች ፕሮግራም የተናገርኩት ይሄንን ነበር። ታዲያ ወያኔዎችና የነሱ ጋሻ ጃግሬ ቱቦዎች የ”ኢትዮጵያ ብሂራዊ ጥቅም” ዘብ እና ዋና ጠበቃ ሆነው ለመቅረብ ያዙኝ ልቀቁኝ ይወራጫሉ።

የኢትዮጵያ “ብርሄራዊ ጥቅም” በእርግጠኝነት የሚጠበቀው በኢትዮጵያ ላይ የተጣበቀው የህወሓት ደም መጣጭ መዥገር ስንላቀቅ ብቻ ነው። ከጎንደር፣ ከወሎ መሬት የዘረፉ እነሱ፣ ለባእዳን ለህንዱ፡ ለአረቡ፣ ለሱዳን መሬት ቆርጠው የሚሰጡ፣ የሚቸበችቡ ፣ ህዝባችንን በማፈናቀል ደም እንባ በምድረ ኢትዮጵያ እንዲጎርፍ ያደረጉትም እንሱ ናቸው። እኛ እይደለንም። ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያን ህዝብ ሲረግጡ፣ ሲያደሙ፣ ሲዘርፉ፣ ሲደፍሩ፣ የንጹሃንን ደም እንደጎርፍ በምደረ ኢትዮጵያ ሲፈሱ የኖሩ ጉዶች ዛሬ ስለኢትዮጵያ “ብሄራዊ ጥቅም” ዋነኛ ጠበቃ ለመሆን ምንስ የሞራል፡ የታሪክና የፓለቲካ መነሻ ሊኖራቸው ይችላል? የውቅሮ ብልጣ ብልጦችና የነሱ ጋሻ ጃግሬዎች ቱሪስት መብላት ይቻላሉ።

LEAVE A REPLY