ዶ/ር ዓቢይ፥ የጫጉላው ጊዜ ይበቃል-ወደ ተግባር ይሸጋገሩ

ዶ/ር ዓቢይ፥ የጫጉላው ጊዜ ይበቃል-ወደ ተግባር ይሸጋገሩ

/አቢቹ ነጋ/

ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ለውጥ በደም ሳይሆን በሰላም ቢሆንለት ይመርጣል። የሰላሙ መንገድ ካልሰራ ህይወቱን መስዋእት አድርጎ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ከማብሰር ወደ ኋላ አይልም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰላማዊ መንገድ የኢሃዴግን መንግስት መግቢያ መውጫ አሳጥቶ የነበረውም ለዚህ ነው።

በዚህ ጊዜ የመንግስት ምላሽ ግድያ፤ አፈና፤ እስርና ዝርፊያ ነበሩ። መንግስት የሃይል መንገድ በተከተለ ቁጥር የሕዝብ ጉለበት እያየለ፤ ተቃውሞው እየጎለበት ይሄዳል። መንግስት የሚአደርገውን ያጣል። መፍተሄ ብሎ ያሰበው የህዝብን ቁጣ ለማብረድ በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል። ከአዋጁ በፊትም ሆነ በኋላ ያው ሞት ስለሆነ ሕዝቡ ተቃውሞውን ይገፋል። አሁንም መንግስት ማስተዳደር እያቃተው መሆኑ ይቀጥላል። ጉልቻም እየቀየር ሕይወቱን ለማቆየት ይሯሯጣል። በመሆኑም ሃገሪቱ ፖለቲካ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገባለች። መልስ ካልተሰጠ ወደ ከፋ ምስቅልቅል መግባት አይቀሬ ይሆናል። ኪራይ ሰብሳቢው፤ ነፈሰ ገዳዩ፤ ዘራፊ፤ ወንጀለኛው፤ ባለስልጣኑና ጋሻ ጃግሬው ጥቅሙ ሲነካበት መውጫ ቀዳዳ ይጠፋበታል። በዚህ ሁኔታ ላይ ነው በዘረኝነት የተገነባው የህውሃት መንግስት ብርክ የያዘው።

አገር በዚህ ቀውስ ውስጥ እያለች ዓማራውና ኦረሞው ከእሳትና ጭድነት ወጦ ሰምና ወርቅ ሆነ። አንለያይም እያለ በአንድነት ኢትዮጵያዊነትን ዘመረ። ይህን የማይፈልገው ህውሃት ብርኩ ጠናበት። ጎሳን ከጎስ በማጋጨት እና በመለያየት የተከተለው የጥፋት መንገድ እንደማያዋጣው ተገነዘበ። ከ70% በላይ የሚሆን ኢትዮጵያን የሕዝብ ብዛት የያዘው አማራና ኦሮሞ ህብረት አስጨነቀው። ኢትዮጵያዊነት ሱናሚ ሆኖ ከምድረገጽ የሚአጠፋው መሆኑን ህውሃት ተረዳው። በዚህ ውጥንቅት ውስጥ የሰላማዊ ስልጣን ሽግግር በሚል ከመሃላቸው አንዱ የሆነውን አንደበተ ርተኡን ዶ/ር ዓቢይን በጠቅላይ ሚንስትርነት ሳይወድ በግድ መርጦ ተቀበለ። ለሕውሃት መራራ ክኒን ነበር (bitter pill)።

ዓቢይ በብዓለ ሲመታቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀልብ የሳበ ንግግር አደረጉ። ስለኢትዮጵያዊነት፤ ስለፍትሕ፤ ስለሰላም፤ ስለአንድነት፤ ስለፍቅር፤ ስለነፃነት፤ ስለዴሞክራሲ በሰፊው ተናገሩ። ለ27 ዓመታት ይህን የተነፈገ ሕዝብ በድንገት ከአዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ሲሰማ ተደሰተ። ተስፋም አደረገ። ለምን አያጨብጭብ፤ ለምን አይደሰት። አኔም እንባ ተናንቆኝ አጨብጭቤአለሁ። ይህ ማጋነን እንዳይመስላችሁ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ምልኡ ኩልሄ በሆነ መልኩ ድጋፍ አገኙ። የሞተው ኢትዮጵያዊነት ተነሳ። ተስፋ የቆረጠው ሕዝብ ተስፋው ለመለመ። መልካም ቃል ልብን ታሸንፋለች እንዲሉ የዶ/ር ዓቢይ ንግግር ከሰማይ ሲጠበቅ የነበረ መና እንደወረደለት ሕዝቡ ተሰማው። ዓቢይ ልክ እንደ ኦባማ አንደበተ ርትኡ በመሆናቸው ተወደሱ። በኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም የዓለምም ሕዝብ አደነቋቸው። በተለይ ምእራቡ ዓለም ድጋፉን ሰጣቸው። ሕዝቡም ይህን ያማረ ንግግር ወደ ተግባር ከቀየሩት ኢትዮጵያ ወደ ጥሩ አቅጣጫ እንደምትሄድ ተስፋ ሰነቀ፤ አመነ። ያመነ ይድናል አይደል ሚለው የዓብዩ መጽሐፍ። በዓብይ ጾም ዓቢይ ነገር በማግኘቱ የዖርቶዶክስ እምነት ተከታዩ በጸሎቱ፤ በጾሙ ወቅት የኢትዮጵያን ትንሳዓኤ እንዳመጣ ተሰማው።

ሕዝብ ህውሃት ለ27 ዓመት የፈጠረው ጥፋት፤ የሸረበው ተንኮል፤ የዘረፈው ሃብት እና ንብረት መጠነ ሰፊ በመሆኑ አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር በተሾሙበ24 ስዓት ውስጥ መፍትሔ ይገኛል ብሎም አጉል ተስፋ አልሰነቀም። ይሁን እና በአስቸኳይ መደረግ የሚገባቸውን ጉዳዮች ሳይውል ሳያድር ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ግን ነበር። ከነዚህም ቀዳሚ ተግባራት የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፤

1. ከብዓለ ሲመታቸው እንደተመለሱ አዲስ ካቢኔን ያዋቅራሉ ፤
2. ማናቸውንም የፖለቲካ እስረኞችና ፍርደኞች በምህረትም ይሁን በሌላ ዘዴ በአዋጅ መፍታት እንደሚችሉ፤
3. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በካቢኔአቸው አስፈቅደው፤ በሕዝብ ምክርቤት አስጸድቀው ያስነሳሉ ተብሎ፤
4. ገለልተኛ የፍትሕ፤ የምርጫ ቦርድ ተቋማትን እንደ አዲስ አዋቅረው በአዋጅ እንዳዲስ ያቋቁማሉ፤
5. ሕዝቡ በነፃ ሃሳቡን እንዲገልጽ፤ ሰላማዊ የአደባባይ ሰልፎችን የማድረግ መብትና ነፃነትን ለሕዝብ ማወጅ፤
6. በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ማናቸውንም የተቃዋሚ የፖለቲክና የሲቢክ ማህበራት በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ፤ እንዲደራጁና እንዲአደራጁ ወዘት በአዋጅ ይፈቅዳሉ፤
7. ሃገራዊ መግባባት እንዲካሄደ በአዋጅ መፍቀድና ማቋቋምን፤
8. የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ፈቅደው በሃገሪቱ የተፈጸመውንና በመፈጽም ላይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲአጣሩ በአዋጅ ይፈቅዳሉ፤ ወዘተ..የሚል ተስፋ ተጠብቆ ነበር።

ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጠው ይንቀሳቀሱ ይሆናል የተባሉት ጠ/ሚ/ር አጀንዳቸውን ቀይረው የችግር ሳተጎሞራ ወዳአለባቸው ከተሞች ማለት ሶማሊ ክልል፤ አምቦ፤ መቀሌ፤ አዲስ አበባ ወዘተ እየተዘዋወሩ ንግግር ማድረግን አጀንድ ቅድሚያ አድርገው ተንቀሳቀሱ። መቸም በመጀመሪያ የሰላምና የፍቅር ዘምባባን ይዞ ከሕዝብ ጋር መነጋገር እና መመካከር ክፋት የለውም። ግን ችግሩ ያለው ሕዝብ ዘንድ ሳይሆን ከህውሃትና ከኢሃዴግ ውስጥ መሆኑን አለመረዳት ግን ችግር አለው። መፍትሔው እና ስራው መጀመር ያለበትም እዚህ ላይ ነው። እነዚህ አካሄዶችና ስልቶች የእሳት አደጋ ሰራተኛ (fire fighter) እንጅ የጠቅላይ ሚንስትሩ አይመስሉኝም። የአዲሱ መሪ ስራ መሆን ያለበት የመልካም አስተዳደር እና የስርዓት ለውጦችን ሊአፋጥኑ የሚችሉ ስልቶችን (system) ማዋቀር ነው። ለዚህም መፍተሄ የሚሆነው ከላይ በተራ ቁጥር ከ1 ከ እስከ 8 በተጠቀሱት ዓቢይ ጉዳይች ላይ ዓብይ እርምጃ ሲወሰድ ነው። ይህ ሲደረግ እና በነዚህ ላይ የአመራር ብቃት ሲታይ የስርዓት ዘዴዎች (system) ተዘረጉ ብለን ልናስብ እንችላለን። ስራውም ዘላቂነት (sustainability) ይኖረዋል። የእሳት አደጋ እና የሚሲዮን አሰራር ዘላቂ ሳይሆን ጊዚያዊ ማስታገሻ (ad hoc solution) ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም።

በሚቀጥለው ወደ ጎንደር፤ አዋሳ፤ ነቀምት ሄደው ሕዝብ የማረጋጋት ስራ ለመስራት ይሞክራሉ የሚል ግምት አለኝ። ይህ ሁሉ እርባና ያለው ስራ ሆኖ አይቆጠርም። ለምን ካሉ በነዚህ አካባቢዎች ያለውን ችግር እርስዎም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት በሚገባ ያውቁታል። ስለሆነም ቁስሉን እያከኩ እና እያስጨበጨቡ ሳይሆን ከካቢኔዎ ጋር ተዋውቀው ቋሚ መፍተሔ ቢሰጡ ይመረጣል። አልቃሽ ባሏ ሞት ላይ በሕይውት ሳለ ወይማ ሳለች ሲናቆሩ የነበሩ ባልትዳሮች አንዳኛው ሲሞት በሬሳው አጠገብ ተሁኖ የሃዝን ልብስ ለብሶ ስለ ሟቹ ደግነትና መልካም ስብእና ማንባትና ደረት መምታት ሟቹን አይመልሰውም። ስለመልካም ሰውነት ለሟች ቢንጎረጎር ሐዘንተኛ ከመታዘብ በቀር የሚመጣ ለውጥ የለም።

ስለዚህ ዶ/ር ዓቢይ እጅጌን ጠቅለል፤ ወገብን ጠብቅ፤ እውቀትን ሰብሰብ፤ ስልጣን ጨበጥ አርጎ መሬት ላይ የሚአርፍ ስራ ለመስራት ይነሳሱ። በሕውሃት በኩል የሚደርስብዎትን የሃይል፤ የተንኮል እና የእንቅፋት ጫና መጠን እናውቃለን። ሕዝብም በሚገባ ይረዳል። በተለይ መከላከያውንና ደህንነቱን የተቆጣጠሩት ሕውሃቶች እርስዎን ቀፍድደው መያዝ ብቻ አይደለም በሕይወትዎም ሊመጡ ይችላሉ። አድርባይ ሆኖ የማይሆን ስራ ከሚሰሩ እውነተኛ ስራ ሰርተው እንደክርስቶስ ለመሰቀልና ለመገረፍ ዝግጁ መሆን ይኖርብወታል። ይህን ካረጉ በሕዝብ ይወደሳሉ ሲዘከሩም ይኖራሉ። እኔና እርስዎ ስለመልካም ስራው በአካል የማናውቀውን ኢየሱሱስ ክርስቶስን ለ3000 ዘመን ስንዘምርለትና ስናወደስው እንኖር የለም እነዴ። መልካም ስራና መልካም ስም ከሽቶ የበለጠ ይወደዳል ይናፈቃልና። አንድ ነገር ግን ማወቅ አለብዎት። እነርሱ መሳሪያና ደህንነቱ ይኖራቸዋል። ግን በሃይል የሕዝብን ድጋፍ፤ ፍቅርና ሠላምን አላገኙትም፤ አያገኙትምም። በዚህ መንገድ በሄዱ ቁጥር የበለጠ ጥላቻን፤ ቀውስን፤ ሞትና ውድቀትን ይገዙባታል እንጅ። የርስዎ መከላከያ ሰራዊት እና ደህንነት አንድና አንድ ነው። ይኸውም የሕዝብ ሃይል፤ ድጋፍና ፍቅር። የሕዝብን ድጋፍና ፍቅር የተላበሰ መሪ በምንም መልኩ አይውድቅም።

እስካሁን ባደረጉት የእሳት አደጋ ስራ ተጠቃሚው ሕዝብ ሳይሆን ሕውሃት ብቻ ነው። ለምን ካሉ ህዝብ ለእርስዎ ጊዜ እንስጥ በሚል ተዘናግቶ አንፃራዊ ሰላም ስለሰፈነ። ሕውሃት የሚሸርበውን ተንኮል ለመሸረብ ጊዜ አግኝቶ የቤት ስራውን እንዲሰራ ረድቶታል። ሁለተኛ በሰበ አስባቡ ያሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲጓተት ቆይቶ ስድስት ወረ ሲሞላው ይነሳል። በዚህም ህውሃት በርስዎ ሃይል ሳይሆን በሱ ሃይል በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መሰረት ተነስቷል ይላል። በዚህም ሃይሉን ለውስጥም ለውጪም ያበስራል። ይህ ለሕዝቡ ትግልም ሆነ ለርስዎ የስልጣን ሽግግር ትልቅ ሽንፈት ነው። የጫጉላው ጊዜ አብቅቷልና ወደ እውነተኛ ተግባር ይመለሱ። አይ ካሉ ሕዝቡ በርስዎም ላይ ሊነሳ በቋፍ ላይ መሆኑን በጊዜ ቢረዱ መልካም ነው እላለሁ። ይወቁበት።

ነን ሶቤ

መጋቢት 18, 2018

LEAVE A REPLY