ፌስ ቡክ አዳዲስ መመሪያዎች ማውጣቱን ገለጸ

ፌስ ቡክ አዳዲስ መመሪያዎች ማውጣቱን ገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ፌስ ቡክ ከሰሞኑ የደረሰበትን ከፍተኛ ወቀሳ ተከትሎ አዳዲስ መመሪያዎች ማውጣቱን ገለጸ።የፌስ ቡክ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ ያወጣው “ካምብሪጅ አናሊቲካ” ለሚባል የፖለቲካ አማካሪ ድርጅት የደንበኞችን ግላዊ መረጃ ያላግባብ አሳልፎ ሰጥቷል ተብሎ ከፍተኛ ወቀሳ ከደረሰበት በኋላ መሆኑን ታውቋል፡፡

አዲሱ የፌስቡክ የአጠቃቀም መመሪያም በዋናነት ደንበኞች በማህበራዊ ሚዲያው መጠቀም የሌለባቸውን ይዘቶች የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡ይሁንና የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ይህን ህግ ተላልፈው ሲገኙ ከማህበራዊ ሚዲያው እንዲወገዱ ይደረጋሉ ከፍ ሲልም በህግ እንደሚከሰሱ ተገልጿል፡፡

ከባድ ዛቻ፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ሽብርተኝነትን ማበረታታትና ለመጥፋት አደጋ ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎችን ማደን የመሳሰሉ ድርጊቶች በማህበራዊ ሚዲያው ማስተላለፍ ለቅጣት የሚዳርግ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ፌስቡክ ለደንበኞቹ የአንድን ማህበረሰቡ እሴት አልያም አናኗር ላይ ጥላሸት የሚቀቡ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎችና ጽሑፎች ከማህበራዊ ገጹ እንዲወገዱ የማድረግ መብት በአዲሱ መመሪያ ተካቷል ተብሏል፡፡

አንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ፌስቡክ ላይ የጫነው ይዘት ከተወገደበት ፌስቡክ እርምጃውን ለደንበኛው በመጠቆም ተጠቃሚው በ24 ሰዓት ውስጥ ቅሬታ አቅርቦ ተቀባይነት ካገኘ ከማህበራዊ ሚዲያው የተወገደው ይዘት መልሶ እንዲጫን እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡

የፌስ ቡክ መስራችና ስራ አስኪያጅ ማርክ ዙከርበርግ በአሜሪካ ህግ መወሰኛ ም/ቤት ከሁለት ሳምንታት በፊት ቀርቦ ከ10 ሚሊዮን በላይ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎችን የግላዊ መረጃ ለሦስተኛ ወገን ስለ መስጠቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን የተጠየቀ ሲሆን በድርጊቱ እንደተፀፀተና ይቅርታም መጠየቁ የሚታወስ ነው።

LEAVE A REPLY