የኢንጅነር ሙሉጌታ ዘርፉ ውዱ አጭር የሕይወት ታሪክ

የኢንጅነር ሙሉጌታ ዘርፉ ውዱ አጭር የሕይወት ታሪክ

ኢንጅነር ሙሉጌታ ዘርፉ ውዱ፣ ሰኔ ፳፩ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. – መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. June 28, 1962 – April 4, 2018

ኢንጅነር ሙሉጌታ ውዱ
መልካሙን ገድል ተጋድዬኣለሁ፤ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄኣለሁ። 2ኛ ጢሞ 4:7

ኢ/ር ሙሉጌታ ዘርፉ ውዱ ተመራማሪ፣ ጸሐፊ፣ ለሃይማኖትና ለሃገር ክብር ተሟጋች ሰው ነበሩ። ኃይለ ሚካኤል (ሙሉጌታ) ከኣብያተ ክርስቲያናቱ በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኗ ኣገልግሎቷ እንዲሰፋና መንፈሳዊ ማኅበራትንና ግለሰቦችን በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ። ኣቶ ሙሉጌታ በ2012 (እ.ኤ.ኣ.) በዋልድባ ገዳሞችንና መነኮሳት በኣባቶችና እናቶች ላይ የደረሰውን ችግር ምዕመናንን በማስተባበር መፍትሔ ለመፈለግ “ዋልድባን እንታደግ” በሚል ቀዳሚ ቃል ማኅበር በማቋቋም ብዙ ጥረት ኣድርገዋል።

በሰብአዊ መብት፣ በሃይማኖትና በጠቅላላ በሕይወት ዘመናቸው የፈጸሟቸውን ተግባራትና የነበራቸውን ረጅም ዕቅድ ለመዘርዘር በዝች ኣጭር መርሀ ግብር ማካተት ባይቻልም የዘመኑን ድረገጾች በመቃኘት በርካታ በፅሁፍ በስማቸው ያበረከቷቸውን ሀሳቦች ማንበብና መመርመር ይቻላል። ለሀገር፣ ለወገን፣ ለሃይማኖት፣ እድገትና ልማት ረጅም ኣስበው በኣጭር የተቀጩት ኣቶ ሙሉጌታ ዘርፉ ውዱ በኣደረባቸው ሕመም ሳን ሆዜ በሚገኘው ካይዘር ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ 55 ዓመታቸው ዕረቡ፣ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. (April 4, 2018) ከዚህ ዓለም ተለዩ።

ኢ/ር ሙሉጌታ ዘርፉ ውዱ ከኣባታቸ ከባላምባራስ ዘርፉ ውዱና ከእናታቸው ከወይዘሮ ተጓዴ ዓይንሸት ሰኔ 21 ቀን 1954 ዓ.ም. (እ.ኢ.አ.) በጎንደር ከተማ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በጭልጋ አውራጃ፣ ኣይከል ከተማ በኣይከል ኣንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምርታቸውን ጀምረው፤ ወላጆቻቸው በሥራ ዝውውር ወደ ጎንደር ከተማ ስለሔዱ በጎንደር ከተማ በሚገኘው የጻድቁ ዮሃንስ የ፩ኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ትምሕርታቸውን ተከታትለው ጨረሰውዋል።

የመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ጎንደር በሚገኘው የፋሲለደስ ኣጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ተከታትለው በከፍተኛ ማዕረግ ኣጠናቀዋል ። በ1966 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኣብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕኣፓ) በመደራጀት ከድርጅታቸው በተሰጣቸው ተልዕኮ በደብረታቦር ኣውራጃ ከፍተኛ የፖለቲካ ኣስተዋጽኦ በሚያደርጉበት ጊዜ በመንግሥት ተከሰው ጎንደር ከተማ ወህኒ ቤት ለበርካታ ወራት ታሥረው ተለቀዋል።

ኢ/ር ሙሉጌታ ከእሥር እንደተለቀቁ ወደ ኣዲስ ኣበባ በመሔድ በኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርስቲ በምሕንድስና ትምህርት ተመርቀዋል። ከዚያም በሙገር የስሚንቶ ፋብሪካ በሲቪል መሐንዲስነት ከሠሩ በኋላ በዓለም ሕንፃ ተቋራጭ ድርጅትና በሌሎች ድርጅቶች በፕሮጀክት ኃላፊነት በኣዲስ ኣበባና በኣሰብ ከተሞች ኣገልግሎት ሰጥተዋል።

ኢ/ር ሙሉጌታ ግንቦት 13 ቀን 1984 ዓ.ም. (1992) ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ሻሼወርቅ ኣቡኔ ጋር በኣዲስ ኣበባ ከተማ በሕግ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በመፈጸም እስከ እለተ የሕይወት እልፈታቸው ድረስ ኣብረው ኖረዋል። ኣቶ ሙሉጌታ እ.ኢ.ኣ. በ1985 (1993) ዓ.ም. ከባለቤታቸው ጋር ወደ ኣሜሪካ በመምጣት በካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት በሳን ሆዜ ከተማ የሕይወት ኑሯቸውን በመመሥረት ከባለቤታቸው ጋር 1ኛ ቃልኪዳን ሙሉጌታ 2ኛ ልብነ ድንግል ሙሉጌታ 3ኛ ሳምሶን ሙሉጌታ የተባሉ ልጆችን ኣፍርተው በሀይማኖትና በኢትዮጵያዊነት ባህል ኣንፀው በማሳደግ ለከፍተኛ ደረጃ ኣብቅተዋል።

ኢ/ር ሙሉጌታ በኣሜሪካ የሥራ ዘመናቸው 1ኛ ናሽዋ (Nashwa Magnetic Storage)፣ 2ኛ ዌስተርን ዲጅታል (Western Digital) በሃርድዌር ኢንጅኒርነት 3ኛ በማክስቶር ኤም-ኤም-ሲ ቴክኖሎጂስ (Maxtor MMC Technologies) በሥታፍ ኢንጂነርነት 4ኛ ሚያ-ሶሌ (MiaSolé) እየተባለ በሚታወቀው ድርጅት በሲኔየር ፕሮሠሥ ኢንጂነርነት በመጨረሻም በሲስኮ ሲስተም (Cisco Systems) ኩባንያ በተለያዩ የሀላፊነት እርከን ለምሳሌ የኣቅርቦት ሰንሰለት ኣስተዳደር Managing supply chain, Big Data Analyst, and Statistician በመሆን ኣገልግለዋል።

በቀጣይነትም በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነውም ሙያቸውን ለማሳደግ፣ ለማዳበርና ለማሻሻል በሳንታክላራ ዩኒቨርስቲ Magnetic Recording በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በMBA ትምህርቶችን በብቃት ኣጠናቀዋል።

ኢ/ር ሙሉጌታ ዘርፉ በኣሜሪካ የሥራ ዘመናቸው በሰሩባቻው ኩባንያወች በፈጠራ ችሎታ ኣሉ ከሚባሉት ባለሙያወች በተርታ ለመቆማቸው በሃርድዌርና በሶላር ቴክኒዎሎጂ የፈጠራና ኣዲስ ግኝት በስማቸው የተመዘገበ ስምንት (Patent) የግል ባለቤትነት ማረጋገጫዎች ኣግኝተዋል። ምሳሌ (https://patents.google.com/patent/

US5942279A/en?oq=5%2c942%2c279)። ይህ ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ሲሊኮን ቫሊ ውስጥ ለሚገኙ በዚህ ሙያ ለተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ኣርዓያ ሆኗልም።

ኢ/ር ሙሉጌታ በሠሩባቸው ቦታዎች ሁሉ በቀጣሪ ድርጅቶቻቸውና በሥራ ባልደረቦቻቸው በሥራ አክብሮታቸው፣ በከፍተኛ የሥራ ውጤታቸውና ኣብሮ በመሥራትና ባላቸው መልካም ሥነ-ምግባር የታወቁና የተመሰገኑ ነበሩ።

ሙሉጌታ ዘርፉ ተመራማሪ፣ ጸሐፊ፣ ለሃይማኖትና ለሃገራቸው ክብር ተሟጋች ሰው ነበሩ። ኣቶ ሙሉጌታ ሦስት መፃህፍትን ኣሳትመው ለንባብ ያበቁ ሲሆን በማህበራዊ ድረገፆች በርካታ ሀይማኖታዊ፣ ኣገራዊና ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸው ፅሁፎችን ኣቅርበዋል። ለኣብነት በamazon.com ላይ ገበያ ላይ የዋለውን The woman of Folly Why Science Must be Stopped፣ በኢትዮጵያ የወጣቱን የፈጠራ አቅም ለማጎልበት የሚረዳ “መጽሐፈ ብልሃት” የተሰኘ መፅሀፍ ታትሞ እንዲሰራጭ ኣድርገዋል።

በተጨማሪም “መለኮት ኢትዮጵያን ያናገረበት ቋንቋ” የሚልም መፅሀፍም ኣሳትመው ለኣንባቢያን ኣበርክተዋል።
በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኣማኝ ሲሆኑ ለእምነታቸውና ለእግዚአብሔር ቤት በከፍተኛ ደረጃ ቀናኢ ነበሩ። በሳንሆዜ የራማ ቅዱስ ገብርኤል፣ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ገብርኤል፣ የሳክራሜንቶ ተክለ ሃይማኖትና የሳንፍራንሲስኮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያናት ከተጠቃሾቹ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በተለይ ለመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ካቴደራል ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ በሊቀመንበርነት፣ በገንዝብ ልገሳቸው አንዲሁም በእውቀታቸው ያበረከቱት ኣግልግሎቶች በቀዳሚነት ይታወሳል።

በሕመማቸው ጊዜ በኣካል ተገኝታችሁ ለጠየቃችሁ፣ በሞታቸው በኣካል ቀርባችሁ፣ በሩቅም በስልክ፣ በኢሜልና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ላጽናናችሁን ሁሉ ምሥጋናችን ከፍ ያለ ነው።

ባለቤታቸውና ልጆቻቸው

ማሳሰቢያ፣
ኢ/ር ሙሉጌታ ቀደም ሲል ለአቶ ገዱ ለጻፍነው ደብዳቤ ትልቅ ድጋፍ የሰጡና የሰነዱም ፈራሚ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

LEAVE A REPLY