እርግጥ ነው አንዳርጋቸው ጽጌ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ አሲረዋል፤ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ በማድረጉ ብቻ በእስር ሊንገላታ አይገባውም፡፡ ክርክሬን አስረዳለኹ፡፡
አስረጅ አንድ
እውነት እውነቱን መነጋገራችንን እንቀጥል፡፡ ሕገ መንግስቱ ለማይሸራረፈው ትንሹ አሐድ ግለስብ ዕውቅና ያልሰጠ ውስጡ በብዙ ተቃርኖዎች የተሞላ ነው፡፡ የማንነት ወሰን/ ድንበርን በአስተዳደር ክልል ስም ያሰፈነ ነው፡፡ ሐረሪን፣ ጋንምቤላን፣ ቤኒሻንጉልን ክልል አድርጎ ብዙ ሚሊዮኖች ወረዳ እና ዞን ያደረገ ነው፡፡ ደቡብ የተባለ ሌሎች ክልሎች በጆኦግራፊ ሳይከለሉ ብቻውን ብቅ ያለ ማጎሪያን የፈጠረ ነው፡፡ ዘውጋዊ ማንነት እንደ ዐለት በማደደር ተፋጥሮአዊ የመወራረስ፣ የመለወጥ እና የማደግ ባህሪውን የገደበ ነው፡፡ መሬትን በመንግስት እጅ አድርጎ ባለስልጣናት ሲያሻቸው በሽልማት ለወደዱት የሚሰጡት ሲፈልጉ እንደሸቀጥ ነግደው የሚከብሩበት ያደረገ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ከየብሔሩ ሁለት ሁለት ሆነው ለተመረጡ የፖለቲካ ታማኝነት ላላቸው የሰጠ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በአብዛኛው ስልጣኑን በደፈናው ለፍርድ ቤቶች ሲሰጡ የተወሰኑት ደግሞ ብቻውን ያለ የህገ መንግስት ፍርድ ቤት ያቆማሉ፡፡ የኛው ህገመንግስት ራሱን የሚያስተረጉመው በቀላጤ ፖለቲከኞች ነው፡፡ ባጠቃላይ ስለዚህ መሠረታዊ የመዋቅር ችግር ሳለለበት ህገ መንግስት ብዙ ማለት ቢቻልም አሊ ማዝሩይ ያለው ሀገረቱን ወደ ትራይባሊዝም የመለሰ ነው የሚለውን ጠቀሶ ማቆም መርጫለኹ፡፡ ስለዚህ ይህ ህገ መንግስት ተጣሰ ተብሎ ሰው እስር ቤት መወርወር የለበትም፡፡
አስረጅ ሁለት
እውነት ለመናገር ምስጋና እንደ ክፍሌ ወዳጆ ላሉ ሰዎች ይግባና ሕገ መንግስቱ ሙሉ በሙሉ የሚነቀፍ አይደለም፡፡ ሀገሪቱ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያመጣ፣ ሳንሱር የለም ብሎ ያወጀ በጣም ተራማጅ የሚባሉ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያካተተ ነው፡፡ ሀገሪቱ ለፈረመቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ ድንጋጌዎች ተገዢ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ዋጋውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ የማዕከላዊ መንግስትን ስልጣን ከፍሎ ወደህዝብ የቀረበ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግቷል፡፡ ለእነዚህ መልካም ገጽታዎቹ በማለት እና የሀገር ግንባታ ሂደት ውስብስብ እና ሆደ ሰፊነት የሚጠይቅ መሆኑን የተረዱ ብዙዎች ሕገ መንግስቱን ከነህጸጹ እንደመነሻ ዶክመንት ተቀብለው ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ግን ከማንም በፊት ነበር ሀገሪቱ ነጻነትን በማያውቁ ነጻ አውጮዎች መያዟን የተገነዘበው፡፡ ብዙዎች ግን አንድ ባንድ የሕገ መንግስቱን አንቀጾች እስኪጥስ እና በጥላቻ የተሞላ ከፋፍለ ግዛ ፖሊሲውን እስኪ ዘረጋ ድረስ በተስፋ ሲጠብቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ስርዓቱ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 15 የሰፈረውን መሠረታዊ የሚባለውን የመኖር መብት እንኳን ሊያከብር አልቻልም፡፡ ፍርድ ቤቱን፣ መድብለ ፓርቲ ስርዓቱን፣ ፌደራሊዝሙን፣ መሠረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያልተጣሰ ምን ቀረ? በነጻ አውጪዎች የተመሰረተው መንግስት ራሱ አርቅቆ ራሱ ያጸደቀውን ሕገ መንግስት ራሱ ንዶ ጨረሰው፡፡ በዚህ ምክንያት የእስካሁኑ ኢህአዴግ ማንንም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ የመክሰስ የሞራል የበላይነት የለውም፡፡ ከመኖር ጀምሮ ያሉትን መብቶች በመግፈፍ ዜጎቹን ሲያሸብር የነበረ መንግስት ከምቾት ቤቱ ወጥቶ የወገኖቹ መንገላታት አሳስቦት በረሃ የከተመን ሰው ለማሰር፣በሽብረኝነት ለመከሰስ እና ሞት ለመፍረድ አይችልም፡፡ የህግ የበላይነት ቢኖር ሌላው ቢቀር ባለፉት አራት አመታት የተገደሉት ዜጎች ደም የገዢው ፓርቲ አባላትን ከላይ እስከ ታች ወደ ፍርድ አደባባይ ባቀረበ ነበር፡፡
ብዙዎች ተዓምራዊ ሊሉት በሚደፍሩት ሁኔታ ሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ በመጀመር እና ባለመጀመር መሀል ትገኛለች፡፡ እዚህ እንድንደርስ ብዙዎች ህይወታቸውን ገብረዋል፡፡ በስደት እና በእስር ተንገላተዋል፡፡ አሁንም እየተንገላቱ ነው፡፡ በመከፋፈል ፖሊሲው ምክንያት ሀገሪቱ ወደ እርስ በርስ መተላለቅ የመግባት ዕድሏ በግልጽ መታየት ጀምሮ ነበር፡፡ ይህ በአንዲህ እንዳለ ግን ጥቂት የፓርቲው ሰዎች ወደፊት ገፍተው የመፍትሔ አካል ለመሆን ሞከሩ፡፡ በዚህ ሂደት ገዢው ፓርቲ “መስዋዕትነት ለከፈሉ መብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞች እና በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊዎች ወጣቶች፣ ለስነ ልቦናዊ እና አካላዊ ቀውስ ለተጋለጡ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች”ን ይቅርታ የሚጠይቅ ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ ቃል የሚገባ ሰው ወደመሪነት በማምጣቱ ይቅር ባዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተገደበ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል፡፡ ይህም ብዙዎቻችን ተስፋ እንድናደርግ፣ ይቅር እንድንል አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን የሚቋቋም ወንጀል ያለባቸውን ወደፍርድ ማቀረብ፣ ተገቢውን ቅጣት ካገኙ በኋላ መንግስት ህዝብ ከሚወክሉ የመብት ተከራካሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና እውነተኛ የሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆኑን አግባበው ያለው የሀገር ባህል እና እሴትን የተከተለ የማስተራረቅ ስራ ከሰራ በኋላ ብሔራዊው ችግር ቢወገድም ሁሉም ሰው የሚያደላው በይቅር ባይነት ነገን ማስተካከል ላይ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ ቃል በገቡት መሰረት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ብዬ እገመታለኹ፡፡ ከድርጅታቸው ጋር መደራደርን ቢያዘገዩት እንኳን አንዳርጋቸው ጽጌን ለመፍታት ከአሁን በኋላ ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት የዘለለ ጊዜ መፍጀት እንደሌለባቸው ይሰማኛል፡፡ አንዳርጋቸውን መፍታት እስካሁን የፈሰሰው ደም ይብቃ ማለት ነው፡፡ አንዳርጋቸውን መፍታት ይቅር መባባልን መጋበዝ ነው፡፡ አንዳርጋቸውን መፍታት በቀል በሀገሪቱ እንዳይነግስ ማደረግ ነው፡፡ ለሀገሪቷ ብሎም ለራሳችኹ ፍቱት እና ወደ ልጆቹ ይሂድ!!!