የትግራይ ህዝብና Activistoቹ /ሞሐመድ አሊ ሞሃመድ/

የትግራይ ህዝብና Activistoቹ /ሞሐመድ አሊ ሞሃመድ/

“የትግራይ Activists” ነን ባዮች በቁጥር ምን ያህል ይሆናሉ? ከነዚህ ውስጥስ “የዘረኝነት መርዛቸውን የሚረጩት” ምን ያህሉ ናቸው? እነዚህ የህዝቡን ምን ያህል ፐርሰንት ሊወክሉ ይችላሉ? ምናልባት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ወይም የፕሮፓጋንዳው ሰለባ የሆኑ በነዚህ አክቲቪስቶች ሊወከሉ ይችሉ ይሆናል።

በነገራችን ላይ ዘርን መሠረት ያደረገ ፕሮፓጋንዳ ህዝብን በቀላሉ መቀስቀስ የሚያስችል ቀላልና; ግን ደግሞ አደገኛ መንገድ ነው። በተለይ አንድን ማህበረሰብ በማንነቱና በህልውናው ላይ አደጋ እንዳንዣበበ ደጋግመህ ከነገርከው ስጋት ሊገባውና መጠጊያና መሰባሰቢያ ሊፈልግ ይችላል። ይኸ ደግሞ ተፈጥሯዊም ይመስላል። ከዚህ አንፃር ላለፉት አራት አሥርተ-ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ ሆን ተብሎና ታቅዶ የተሠራው ፕሮፓጋንዳ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖ በአንክሮ ማየትና መረዳት ያስፈልጋል።

ይህም ሆኖ ግን ሥርዓቱ የትግራይን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሊያረጋግጥ እንደማይችል የሚረዱ ልሂቃን የሉም ማለት አይቻልም። ምናልባት የነዚህ ድምፅ ሥርዓቱ በፈጠረው አንፃራዊ ገዥ አስተሳሰብና በባለጊዜዎች ጩኸት ተውጦ ሊሆን እንደሚችልም መገመት ስህተት አይሆንም። በተጨባጭ እንደሚታዬውና እንደሚታወቀው ደግሞ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ተቀዳሚ ተግባር ከነሱ የተለዬ አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖች; አፍ ማስዘጋት; አንገት ማስደፋትና; እንዳስፈላጊነቱም ማስወገድ ነው። ይህን አለመረዳት በራሱ ትልቅ አደጋ አለው።

በዚህ ረገድ የትግራይ ነፃ አውጭ ቡድን ከጠባብ ብሔርተኝነት ወጣ ያለ አስተሳሰብ ያላቸውን የትግራይ ልሂቃን አፋኝና ገዳይ ቡድን በማሰማራት ለቅሞ እንዳጠፋቸው/እንዳስወገዳቸው ከድርጅቱ ያፈነገጡ ነባር ታጋዮች ከሚናገሯቸውና ለንባብ ካበቋቸው ድርሳናት መረዳት ይቻላል። እንጅማ ከወያኔ ዘመነ-መንግሥት ቀደም ባለው ጊዜ የትግራይ ህዝብ በመላው ኢትዮጵያ ተሰራጭቶና በላቡ/ጥሮ ግሮ ሀብት አፍርቶና ከሌላው ወንድሙ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ጨዋ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል። የህዝቡ ዘላቂ ጥቅም ያለውም ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተግባብቶ; ተስማምቶና ዝምድናውን አጠናክሮ መኖር መሆኑን ለማወቅ የግድ የትግራይ ተወላጅ መሆን አያስፈልግም።

በተጨባጭም አንዳንዶቻችን በመኖሪያ አካባቢ; በሥራ ቦታ/አጋጣሚ; በትምህርት ተቋማት; በዕድር; በጋብቻና በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች በየፊናችን የምናውቃቸውና ሥርዓቱ የፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳስባቸው የትግራይ ተወላጆች ሳያጋጥሙን አይቀሩም። ይህን ለመረዳት ግን ቀረብና ደፈር ብሎ መነጋገር; ብሎም የመጠራጠርና የዝምታ ድባቡን መስበር ያስፈልጋል። ከዚህ በላይ ግን ተራው የትግራይ ህዝብ ያለበትን የኑሮ ሁኔታ; በየትኛው የሀገሪቱ ክፍል ያለሥጋት ተንቀሳቅሶ ለመሥራትና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ተግባብቶ; ተስማምቶና ተዛምዶ ለመኖር ያለውን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ነገሮችን በዚህ መንገድ ለማየትና ለመረዳት አለመሞከር በራሱ ሌላ ችግርና የመፍትሔውን ቀዳዳ የሚያጠብብ መሆን አስረግጦ መናገር ይቻላል።

በርግጥ አንዳንድ ሥርዓቱ “ያባለጋቸው” ባለጊዜ ሰዎችና “Activist” ነን ባዮች የሚያራምዱትን አቋምና “አደገኛ” አስተሳሰብ ካየን ግንዛቤያችንም ሆነ ድምዳሜያችን ከተገቢው መንገድ ያፈነገጠ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ትክክለኛውና የሚበጀው መንገድ ህዝቡን; ሥርዓቱንና “Activist” ነን ባዮችን ለያይቶ ማዬት መቻል ነው።

አላህ ልቦና ይስጠን!!!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

LEAVE A REPLY