ኢትዮጵያ ግንቦት ሰባት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባትን እንድታይ ላደረጉ በሙሉ ክብር ይገባል፡፡ መለስ ዜናዊ እና ጓዶቻቸውም ቅደመ ምርጫ በነበራቸው ሱታፌ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
አመሻሹ ላይ ጣት አንቆርጣለን ብለው እስኪያፈርሱት ድረስ፡፡ ከዚያ በኋላ ይሄ ክፉ የሆነ ህዝብም ክፉ ሞት ተመኘላቸው፡፡ ደንግጠው አይሆኑ ሆነው ሞቱ፡፡ በተራው ህዝቡም ደንግጦ አለቀሰላቸው፡፡
ብዙዎች ግን እስካሁን የግንቦት ሰባት ህልም እና ተስፋ ባጨናገፉት ቂም እንደቋጠሩ አሉ፡፡ ከእያንዳንዱ ልሂቅ ዝምታ እና ለሀገራዊ ጉዳዮች ካለው ባይተዋርነት ጀርባ ያኛው የታፈነ ቅሬታ ይሰማኛል፡፡ አዲሱ አስተዳደር ይህንን ያመረቀዘ ቁስል የምር ለመሻር ቁርጠኝነት ካለው ብዙ ስራዎች ይጠብቁታል፡፡
ሥራዎቹ ከፊሉ ምልክታዊ(symbolic) ሲሆኑ ከፊሉ ደግሞ መዋቅራዊ ናቸው፡፡ መዋቅራዊ ስራዎቹ ህገ መንግስቱን ማሻሻል እና ከፓርቲ ጣልቃ ገብነት ፈጽሞ የጸዱ ተቋማትን መገንባትን ይጠይቃሉ፡፡ ህገ መንግስቱ የማንነት ድንበርን ከአስተዳደር ክልል በጉልህ ለይቶ እንዲያሰፍር ማስተካከያዎች ሊደረጉለት ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶች እና ምርጫ ቦርድ ከየትኛውም ተቋማት በፊት መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አገልግሎታቸው በጊዜ የተገደበ በመሆኑ እና የእነርሱ ድህነት በሌሎች የሀገሪቱ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ ስለሚፈጥር በቅድሚያ እና በፍጥነት ባለሙያ ተመድቦላቸው ሪፎረም ሊጀመርላቸው ይገባል፡፡
ምልክታዊው ደግሞ በጊዜ ሂደት የሚፈጸም አንዳርጋቸውን በመፍታት የሚጀመር ነው፡፡ ተጨማሪ ቤተ መዘክር ወይም አውደ ርዕይ መገንባት አስፈላጊ መስሎ ባይታየኝም በሂደቱ ሰለባ የነበሩ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸውን ማስብ ያስፈልጋል፡፡ መስቀል አደባባይ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ለዚህ ሁነኛ መዘከሪያ መድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህንጻውን በማስፋፋት ሁሉንም ሰማዕታት መዘከር እንችላለን፡፡ በቀይ ሽብር፣ በነጭ ሽብር ለወደቁት፣ የደርግን አምባገነን ስርዓት ለታገሉ ሰማዕታት፣ የኢህአዴግን ጨቋኝ ስርዓት ሲቃወሙ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች፣ በዘውጌ ፌደራሊዝም ሰበብነት በአርባጉጉ፣ በደኖ፣ በጎንደር አደባባይ፣ በኢትዮ ሶማሌ ክልል ለተሰው ወገኖቻችን፣ በሰኔ አንድ እና ሁለት 1997 በጥቅምት 20 እና 21 1998 ዓ.ም. ለተገደሉ የዲሞክራሲ ሰማአታት፣ በአምቦ፣ በነቀምት፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር በቢሾፍቱ ኢሬቻ በዓል ለወደቁት፣ በወልዲያ ጥምቀት በጥይት ለተገደሉት አሁን የምናያትን ትንሽ ጭላንጭል ላበሩልን ሻማዎች መዘከሪያ መሆን ይገባዋል፡፡ እነ አክሊሉ ሀብተወልድን፣ አነ አማን አምዶምን፣ እነ ሀይሌ ፊዳን፣ እነ ብርሃነ መስቀል ረዳን፣ እነ መለስ ዜናዊን፣ እነ ሀየሎም አርኣያን እነ ማሞ መዘመርን በአንድነት የያዘ ዝርዝር የታሪክ ማስረጃዎች ያሉት ዲጂታል ላይብራሪ ያለው፣ የእያንዳንዳቸውን አወንታዊ እና አሉታዊ አበርክቶ በስፋት የምንከራከርበት አዳራሽ ያለው ኮምፕሌክስ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ከሁሉም የሚያጓጓኝ እና ምልክታዊ እርባናው ትልቅ እንደሆነ የማምንበት ግን በዚያው ዕለት በግንቦት ሰባት ነጻ እና ፍትሓዊ የሆነ ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ ጊዜው እየፈጠነ ነው ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በግንቦት ሰባት፣ 2012 ዓ.ም. ይካሄድ ቢባል ቀሪው ሁለት አመት ብቻ ነው፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ነጻ እና ፍትሓዊ ምርጫ ለማካሄድ በቂ ግዜ ይኖረን ይሆን? የዶ/ር አብይ መንግሰት አስፈላጊውን ሪፎርም አድርጎ ሀገሪቱን ለዚያች ዕለት ያደርሳት ይሆን? እኔ ጊዜው አጥሮ ስራው በዝቶ አሳስቦኛል፡፡ ከሰሞኑ የምንሰማቸው ዜናዎች ግን ተሰፋ ማድረግን እንዳንተው የሚገፉ ናቸው፡፡ ተስፋ ማድረግ አይከፋም፡፡