ዛሬ ግንቦት 9/2010
ከቂሊንጦ ከሚመጡበት መኪና ወርደው ችሎት እስኪገቡ የሚቆዩበት ቤት (አንበሳ ቤት) ድረስ “እኛ አሸባሪዎች አይደለንም!” እና ተመሳሳይ መፈክሮችን በጋራ እያሰሙ ነው የሄዱት። [ይህ አይነት መፈክሮች ከዛሬ በፊት ባሉት ቀናቶችም በተደጋጋሚ በፍርድ ቤት ውስጥ ከቂሊንጦ በሚመጡ እስረኞች እየተሰማ ነው]
4ኛ ችሎት
★ ዳኞች 4:45 ላይ ነበር የተሰየሙት። በችሎቱ የነበሩት ተከሳሾች በአንድ መዝገብ የተከሰሱ ናቸው (በእነ ኮሚሽነር ያእቆብ ሼራተን መዝገብ)። አቃቤ ህግ እና ተከላካይ ጠበቃው የተከሳሾቹን ጉዳይ የሚከታተሉበትን መዝገብ መያዝ አለመያዛቸውን ዳኛው ጠይቋቸው ሁለቱም አለመያዛቸውን ሲነግሩት ከቢሯቸው እንዲያመጡ ታዘው የዘው ከመጡ በኋላ፤ መዝገቡ ብይን የተሰጠበት ቀን (መጋቢት 19/2009) የያዙትን ማስታወሻ ዳኞች ከተመለከቱ በኋላ ፍርዱን አንብበዋል።
በመዝገቡ የተከሰሱት 37 ሰዎች ሲሆኑ 4 ተከሳሾች በብይን ተሰናብተዋል። አንድ ተከሳሽ ደግሞ ብይን ሳይሰጥ በእስር ቤት እያለ ሞቷል። እንዲከላከሉ ከተበየነባቸው 32 ተከሳሾች ውስጥ አንደኛ ተከሳሽ የሆነው የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ያእቆብ ሼራተንን ጨምሮ 29 ተከሳሾች ተከላከሉ በተባሉበት አንቀፅ ጥፋተኛ ተብለዋል። 3 ተከሳሾች (አብረሃም ማይክል፣ ይስሃቅ አብረሃም እና መሃመድ ሽፋው) ተከላከሉ የተባሉበትን አንቀፅ በሚገባ በመከላከላቸው ነፃ ናችሁ ተብለዋል።
በፍርዱ ቅር በመሰኘቱን አስተያየቱን የሰጠው ኮሚሽነር ያእቆብ በመዝገቡ ላይ የዳኛ መቀያየሩ ችግር ለዚህ እንዳበቃቸው ጠቅሶ “ችግር የለውም። ንፁህ ሰው ነኝ አውቃለው። ፈጣሪ ይፈርዳል።” ብሏል። አንድ ስሙን የማላውቀው ተከሳሽም ተከላከል ተብሎ የተከላከለበት አንቀፅ እና ጥፋተኛ የተባለበት አንቀፅ የተለያየ እንደሆነ ገልፇል። ዳኞችም የተከላካይ ጠበቃውን እና አቃቤ ህጉን መዝገብ ጠይቀው የነበረው ይህን ለማጣራት መሆኑን ገልፀው፤ ተከላከል የተባለው እና ጥፋተኛ የተባለበት አንቀፅ ተመሳሳይ ነው ሲሉ መልሰውለታል። በመጨረሻም ማቅለያ የሚያስገቡበትን ቀን ላይ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።
ከተከሳሾቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ ማቅለያቸውን ከጋምቤላ ለማስመጣት ረዘም ያለ ቀን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው የጠየቁም አሉ። በዚህ አለመግባባት ጭቅጭቅ ተፈጥሮ ታዳሚዎች ዳኞች ሳይወጡ ከችሎት እንድንወጣ ተደርገናል። ከወጣን በኋላም ማቅለያቸውን የሚያመጡት ለሰኔ 1/2010 ቀጠሮ የተያዘ መሆኑን እና በዛ ቀን ካልደረሰላቸውም ተጨማሪ ቀጠሮ እንደሚሰጣቸው እንደተነገራቸው ሰምቻለው። ይህ ሲሆን ከቀኑ 5:30 ሆኗል። ቀጣይ በእለቱ ቀጠሮ የተያዘላቸው በችሎቱ የሚታዩ መዝገቦች 3ት (እነ ክንዱ ዱቤ፣ እነ ጎይቶም ርስቀይ እና አስቻለው ደሴ) ናቸው። ተከሳሾች በፊት በችሎት ሲገቡ ሁሉም በችሎቱ ቀጠሮ ያላቸው ተከሳሾች ሁሉም አንድ ላይ ነበር የሚገቡት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተከሳሾች በየመዝገቡ ተነጣጥለው እንዲገቡ እየተደረጉ ነው። ዛሬም እነ ክንዱ ዱቤ፣ እነ ጎይቶም ርስቀይ እና አስቻለው ደሴ ለየብቻ እየተጠሩ እንዲገቡ በመደረጋቸው ተነጣጥለን አንገባም በማለታቸው፤ የሶስቱም መዝገብ ተከሳሾች ችሎት ሳይገቡ ዳኞች በቢሮ በኩል ቀጠሮ ሰጥተውባቸዋል።
#ሁሉምየፖለቲካእስረኞችይፈቱ
#FreeAllPoliticalPrisoners
#Ethiopia
#Qilinto