/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዛሬ ረፋድ አካባቢ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ከተማሪዎች ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።
የሰልፉ ዋና ምንክንያትም የአካባቢው ማህበረሰብ አካል የሆኑ ወጣቶች ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ዘልቆ በመግባት ሴት ተማሪዎች ላይ የሚፈፀም ፆታዊ ጥቃትን በመቃውም መሆኑን ተማሪዎች አክለው ገልጸዋል።እንደ ተማሪዎች ገለፃ፤ በሴት እህቶቻቸው ላይ ከሚፈጸም ፆታዊ ጥቃት በተጨማሪ ላፕቶፖቻቸውና የእጅ ስልኮቻቸውም እንደሚዘረፉ አስረድተዋል።
የሚዛን ተፈሪ ካምፓስ ተማሪዎች የሚደርስባቸውን በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለፅ ወደ አደባባይ ቢወጡም የከተማው አስተዳደር በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።ለአካባቢው ማህበረሰብም ተማሪዎች ሰልፍ የሚወጡት የእናንተን ስም ለማጥፋት ነው በማለት በተማሪዎች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም እንደሚገፋፉም ተገልጿል።በመሆኑም የአካባቢው ወጣቶች ገጀራና ጦር በማያዝ ተማሪዎቹን ለማጥቃት ሞክረው በጸጥታ ሀይሎች መበተናቸውን ተማሪዎች ገልጸዋል።
የተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ ከሰዓት በሗላ የተበተነ ሲሆን ነገ ከዩኒቨርሲቲውና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ስብሰባ ለማድረግ ቃል እንደተገባላቸው ገልጸዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ “ግብርና ኮሌጅ” የነበረ ሲሆን በ1998ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ማደጉ ይታወሳል።