የሰማያዊ ፓርቲና የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ አግባው ሰጠኝ በእስር ቤት ስለደረሰባቸው ስቃይና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ከአዲስ አድማስ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ተከታተሉት።
———-
ከሦስት ዓመት ከስድስት ወር እስር በኋላ ሰሞኑን ክሳቸው ተቋርጦ ከተፈቱት መካከል የቀድሞ የፓርላማ አባል የነበሩትን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩን አቶ አግባው ሰጠኝን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፤ ቃለምልልሱ እንደሚከተለው ተቀናብሯል እነሆ፡-
የፖለቲካ እንቅስቃሴ
አግባው ሰጠኝ እባላለሁ፡፡ በ1996 የኢዴፓ- መድህን አባል ነበርኩ… በ1997 ምርጫ ቅንጅትን ወክዬ በመተማ እና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አሸንፌ የፓርላማ አባል ነበርኩ፡፡ አንድነት ፓርቲን ከመሠረቱት አንዱ ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላም ከአንድነት ወጥተን ሠማያዊን መሰረትን፡፡ የሠማያዊ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሠሜን ጎንደር ዞን የፓርቲው ሰብሳቢ ነበርኩ፡፡
የታሰሩበት ምክንያት- የቂልንጦ ቃጠሎ
በተያዝኩበት ወቅት ምክንያቱ አልተነገረኝም ነበር፤ በኋላ ግን የቀረበብኝ ክስ የሱዳን መሬት በህገ ወጥ መንገድ ለሱዳን ተሰጥቷል የሚል የሃሠት ወሬ ነዝቷል የሚል መነሻ ያለው ነው፡፡ የሰውም ሆነ የሠነድ ማስረጃ ግን አላቀረቡብኝም፡፡ በተደጋጋሚ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ መሬት ለምን ለሱዳን ተሰጠ ብለን የማጋለጥ ስራ እንሰራ ነበር፡፡ መንግስት የኢትዮጵያን ሉአላዊ ልማት ከህዝብ እውቅና ውጪ አሳልፎ እየሰጠ ነው በማለት እንቅስቃሴዎችን እናደርግ ነበር፡፡ በተለይ በጋዜጦች ላይ ፅሁፍ እናወጣ ነበር፡፡ በኋላም በጉዳዩ ላይ ሠማያዊ ፓርቲ በጎንደር የጠራውን ሠልፍ አስተባባሪ ነበርኩ፡፡ ለሚዲያዎችም በጉዳዩ ላይ ገለፃ እናደርግ ነበር፡፡ ቀጥሎም ጎንደር ላይ ለ2007 ምርጫ፣ ሠፊ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡
እኔ ለፍ/ቤቱ “በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሠጥቻለሁ፤ ተጨባጭ ማስረጃ አለኝ” ብዬ ነበር የተከራከርኩት። በኋላም የሠው ምስክሮችን አቅርቤ ተከላክዬ፣ ፍ/ቤቱ በዚህ ክስ ነፃ አሰናብቶኛል፡፡ በዚህ ክርክር ላይ እያለን የቂልንጦ ማረሚያ ቤት ተቃጠለ፡፡ ከቃጠሎው ጋር በተገናኘ ተጠርጣሪ ሆኜ ክስ ተመሰረተብኝ፡፡ እኔ ከምንም በላይ የማዝነው ክቡር የሆነውን የሠው ህይወት በጥይትና በቃጠሎ ካጠፉ በኋላ እኛን በመወንጀላቸው ነው፡፡ በእኛ ላይ የበቀል እርምጃ ነው የተወሠደብን እንጂ ፈፅሞ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የለንም ነበር፡፡
የእስር ቤት በደልና ስቃይ
መጀመርያ ጎንደር በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አይናችን በማዳበርያ ተሸፍኖ፣ ባዶ መሬት ላይ እንድንተኛ ተደርገናል፡፡ እየተደበደብን ነው ከጎንደር አዲስ አበባ የደረስነው፡፡ በኋላም በማዕከላዊ እየተደበደብን፣ ከባድ ስነልቦና ጉዳት የሚያደርስ የዘረኝነት ስድብና ጥቃት ተፈፅሞብናል፡፡ ለ7 ቀን የረሃብ አድማ ያደረግንበት ሁኔታ ነበር… ጥቃቱን በመቃወም፡፡ በኋላም ወደ ሸዋ ሮቢት ተወስደን ተገልብጠን ተገርፈናል፤ ራቁታችንን ተገርፈናል። ከብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠል… ያልተፈፀመብን የስቃይ አይነት የለም በወቅቱ፡፡ ቂልንጦ ማረሚያ ቤት እያለሁም በአጠና ጣውላ ሲደበድቡኝ አጠናው ላይ የነበረው ሚስማር ጉልበቴ አካባቢ ተሠንቅሮብኝ በብዙ ስቃይ ነው የዳንኩት፡፡
በወቅቱ እኔ ነኝ በራሴ የተወጋሁት ብለህ ፈርምና እናሣክምህ ብለውኝ ነበር፡፡ “እምቢ ፈጣሪ ያደረገኝን ያድርገኝ” ብዬ ነው የተውኩት፡፡ በኋላም በፈጣሪ እርዳታ ድኛለሁ፡፡ ሸዋ ሮቢት በርካታ ስቃይ ተፈፅሞብናል፡፡ አስራ ሁለት ሰዎች ከአልጋ ጋር እጃችን ወደ ላይ ተደርጎ ለ42 ቀናት ታስረን እንድንሰቃይ ተደርገናል፡፡ ቂሊንጦም ከመጣን በኋላ 7 ሰዎች ለብቻ በር ተዘግቶብን፣ “እናንተ በቀጥታ እርምጃ የሚወሰድባችሁ ናችሁ” ተብለን ስነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ተፈፅሞብናል። ሌላው የሚያሣዝነው ዳኞች አቤቱታችንን መስማት አለመፈለጋቸው ነው፡፡ እንደውም በዚህ ምክንያት የተፈጠረን ውዝግብ ተከትሎ 37 ተጠርጣሪዎችን በጣም በጠባብ ቤት ውስጥ ለ3 ወር አስረውን፣ ከሠው በታች አድርገው አሠቃይተውናል፡፡
ሽንት ቤት ስንቀመጥ አንዱ ሣይጨርስ እያስነሡ ሌላውን በማስገባት፣ እጅግ ክብራችን ተነክቶ ተሠቃይተናል፡፡
ብዙ የሠብአዊ መብት ጥሰት፣ አሠቃቂ ጥቃት ሲካሄድ መንግስት አያውቅም ማለት አልችልም፡፡ ያውቃል፡፡ ማረሚያ ቤቶች አሁን እንኳ ተፀፅትው ከድርጊታቸው መቆጠብ አልቻሉም፡፡ ሰሞኑን እንኳ ጓደኞቻችንን አሠቃይተዋቸዋል፡፡ በተለይ ብሄርን መሠረት አድርጎ የሚደርስ ጥቃት የሠላማዊውን ዜጋ አዕምሮ የሚበርዝ ነው፡፡ ይሄን ለምን ታደርጋላችሁ? ስንል፣ ደብዳቢዎቹ “በቃ ታዘን ነው የሚል ነው” ምላሻቸው፡፡
ከእስር መፈታት
እውነት ለመናገር የፍቺ ግማሽ ነው የሆነብኝ፡፡ ክሣችን የተቋረጠው 26 ብንሆንም የተፈታነው ጥቂቶች ነን፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? የተፈታነው እኔ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እና ጋሽ ካሳዬ ጨመዳ ነን፡፡ ሌሎች እነ ፍቅረማርያም አስማማውን ጨምሮ አልተፈቱም፡፡ ግን በሚዲያ የተነገረው በኛ መዝገብ የተሰበሰበ 26 ሰው ይፈታል ተብሎ ነው፡፡ እስካሁን አራታችን ብቻ ነን የተፈታነው። ይህ ለምን እንደተደረገ አልገባኝም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የጠቅላይ አቃቤ ህጉ ትዕዛዝ እንዴት በሁሉም ላይ አልተፈፀመም? ይህን ሁሉ ግፍ አብረውን የተቀበሉ ወንድሞቻችን መንግስት በገባው ቃል መሰረት እንዲፈታ እንፈልጋለን፡፡ በተለይ እስካሁን ከአማራ ክልል ጎንደር አካባቢ በርካታ ታዳጊዎች ሳይቀሩ “የግንቦት 7” አባል እየተባሉ የታሠሩ አሉ እውነተኛ ብሄራዊ መግባባት ከተባለ፣ እነዚህ ወጣቶች መፈታት አለባቸው፡፡ እኛ እንድንፈታ ከፍተኛ ጥረት ላደረገልን ህዝብ እጅግ አመሠግናለሁ፡፡