የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የሚከተለውን መግለጫ ሰጡ

የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የሚከተለውን መግለጫ ሰጡ

የአማራ ተወላጆች ከምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ በህገ-ወጥ መንገድ መፈናቀላቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው። የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የሚከተለውን መግለጫ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስቀምጠዋል።

————–

“ ግንቦት 13/2010

የዳኖ ወረዳ እዉነታ

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አጂላ እና አዋዲ ጉሉፋ በተባሉ ቀበሌዎች የአማራ ተወላጅ ወንድሞቻችን እንደተፈናቀሉ እና የመብት ጥሰት እንደተፈፀመባቸዉ ተደርጎ ሲዘገብ ቆይቷል። ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ስለ ጉዳዩ የተጣራ መረጃ እንድናደርሳቸዉ ጠይቀዋል። በዳኖ ወረዳ አጂላ ቀበሌ 366፥ በአዋዲ ጉሉፋ ቀበሌ ደግሞ 355 የሚሆኑ የአማራ ተወላጅ አባወራዎች ይኖራሉ። እነዚህ አባወራ አርሶ አደሮች ከወንድም የኦሮሞ አርሶ አደሮች ጋር በእኩልነት፥ በወንድማማችነት፥ በፍቅር አብረዉ የሚኖሩ ናቸዉ። እነዚህ ዜጎቻችን እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰርቶ የመኖር መብታቸዉ ይከበር ዘንድ በቀበሌዎቹ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የወረዳዉ መስተዳድር ለእያንዳንዱ አባወራ 2 ሄክታር የእርሻ መሬት ይዞታ በህጋዊ መንገድ እንዲያገኙ አድርጓል። በዚህም መሰረት አርሶ አደሮቹ በህጋዊ ይዞታቸው ላይ የግብርና ስራቸዉን እየሰሩ ህይወታችዉን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዳኖ ወረዳ በርካታ ቀበሌዎች ስፋት ያለዉ መሬት በህገ ወጥ መንገድ እየተያዘ መሆኑን፥ አልፎ አልፎም የቀበሌ መዋቅራችን ጭምር ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲል ያታልረሱ እና የደን መሬቶችን በህገወጥ መንገድ በሽያጭ ለአካባቢዉ አርሶ አደሮች ሲያስተላልፉ እንደነበር ተረጋግጧል። ከዚህም የተነሳ በወረዳዉ በህጋዊ መንገድ ለአርሶ አደሮች ከተሰጠ ይዞታ በላይ ከ17 እስከ 40 ሄክታር መሬት በህገወጥ መንገድ በአርሶ አደሮች መያዙ ተረጋግጧል። የወረዳዉ መስተዳድርም ይህን ህገወጥ የመሬት ዝርፊያ ለመቆጣጠር ብሄር እና ሀይማኖት ሳይለይ፥ በህጋዊ መንገድ የተሰጠዉን ይዞታ ከህገወጡ በመለየት ስርዓት ለማስያዝ የይዞታ ልኬት ይጀምራል።

  በዚህ ጊዜ በህገወጥ መንገድ መሬት የያዙ ግለሰቦች ህግ የማስከበር ሂደቱ ያለአግባብ ሲያገኙ የነበረዉን ጥቅም እንደሚያሳጣቸዉ ስለተገነዝቡ ብሄር ላይ ያተኮረ ጥቃት እና በቀበሌዎቹ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆች ከመሬት የማፈናቀል ስራ እየተሰራ አስመስለዉ በማስወራት በዚህ ህገወጥ ድርጊት ዉስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላችዉን አርሶ አደሮች ጭምር በመቀስቀስ 100 የሚሆኑ የኢጂላ እና የዋዲ ጉሉፋ ቀበሌ የማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች ወደ ፊንፊኔ መጥተዉ የተሳሳተ መግለጫ እንዲሰጡ አድርገዋል። ሚዲያዎችም በወረዳዉም ሆነ በቀበሌዎቹ መስተዳድሮች በኩል ስለጉዳዩ ያለዉን እዉነታ ሳይጠይቁ የመረጃውን እዉነትነት ሳያጣሩ በማሰራጨታችዉ በጉዳዩ ላይ ብዙዎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዙ አድርገዋል።

 እዉነታዉ ግን በወረዳዉ አንዳችም የመብት ጥሰት እንዳልተፈፀመ፥ የተደረገዉ የመሬት ልኬትም ህገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እንጂ ብሄር ለይቶ ለማፈናቀል እንዳልሆነ የወረዳዉ ህዝቦችም በፍቅር እና በወንድማማችነት እየኖሩ መሆኑን የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችም ጭምር በአካል ወረዳዉ ድረስ በመሄድ አረጋግጠዋል። በተሳሳተ ቅስቀሳ ፊንፊኔ መጥተዉ የነበሩ አርሶ አደሮችም ወደ ቄያቸዉ ተመልሰዉ መደበኛ ኑሮአችዉን ቀጥለዋል።

 በኦሮሚያ ክልል የሚኖር ማንኛዉም ዜጋ በብሄር፥ በሀይማኖት ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ምንም አይነት አድልኦ ሳይፈፀምበት በእኩልነት፥ በወንድማማችነት፥ በነፃነት እና በፍትህ ህግን አክብሮ በሰላም የመኖር ተፈጥሮአዊ መብቶቹ እንዲከበሩ ኦህዴድ በፅናት ያምናል። እነዚህን መብቶች ለማስከበርም ጠንክሮ ይሰራል። በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ ዝንባሌዎች እንዲታረሙ የሚፈጠሩ ችግሮችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ኦህዴድ ከምዕላተ ህዝቡ፥ ከእህት ድርጅቶች እና ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን ይቀጥላል።

የህዝቦች ወንድማማችነት ለዘለዓለም ይኑር!”

1 COMMENT

  1. I didn’t take this as truth, as it will not take a week to disclose this and the governmental media should address such thing on time properly.

LEAVE A REPLY