የአውሮፓ ህብረት በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት የተሰማውን ደስታ ገለጸ

የአውሮፓ ህብረት በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት የተሰማውን ደስታ ገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ህብረቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፤ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ፀሀፊ  አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር መፈታቱ እንዳስደሰተው አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት)፣ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ(ኦ ኤም ኤን)፣ በዶ/ ር ብርሀኑ ነጋና ጃዋር መሐመድ ላይ ቀደም ሲል ተመስርቶ የነበረው ክስ መቋረጡ መልካም ጅምር መሆኑን ገልጿል።

አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት  ከዚህ ቀደም ታስረው የነበሩ ሌሎች የፓለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፣ጋዜጠኞችንና የመብት ተሟጋቶችን  ከእስር መፍታቱ  ለሀገሪቱ ሰላምና የፓለቲካ ምህዳርን ለማስፋት ጠቃሚ እርምጃ እንደነበርም ጠቁሟል። በተጨማሪም መንግሥት ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦ ዴ ግ) ጋር ውጤታማ ድርድር መጀመሩን  አድንቆ፤ በቀጣይም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን፣ በስራ ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳትን፣ የጸረ-ሽብር፣ የምርጫ፣ የማህበራት፣ የሚድያ ህጎችንና ሌሎች ገዳቢ አዋጆችን  የማሻሻል ጉዳይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ህብረቱ አዲሱን የኢትዮጵያን መግስት አሳስቧል።

 የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ተስፋ ሰጭ ለውጦች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም ጨምሮ አስታውቋል።

 

LEAVE A REPLY