(የኢትዮሚዲያ ድህረ ገፅ መስራችና ኤዲተር)
– እኔ የምለው ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍሎ ማዳከም የጠላት (ህወሃት) ፖሊሲ ነው።
ወያኔ ወልቃይትን ወደ ትግራይ ሲያካልል፣ የትግራይ ህዝብ ወልቃይትን ስጡኝኮ አላለም። ማናባቱ አዘዘው? ግን እንዳልኩት፣ የጠላት መሰሪ አላማው ገና ከጥንት ከጥዋቱ አንድ ሆኖ የኖረውን የጎንደር እና የትግራይ ህዝብን በይገባኛል ጥያቄ በማያባራ ግጭት ከቶ ሲያናቁር ለመኖር ነው።
የትግራይ ህዝብ መብት ቢኖርውማ የሚጠይቀው ነገር ቢኖር የነ አሉላ አባነጋ ያከበሩትን የቀይ-ባህር ዳርቻችንን ከወደባችን አሰብ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የሚል ይሆን ነበር። ጠላት ግን ቀይ-ባህር ቀርቶ አሰብ ወደብ ይገባናል ስንል ስንቱን በሰይፍ እንዳስተናገደ ያደባባይ ሚስጥር ነው።
በኔ አስተያየት መፍትሄው – ሁሉም ቦታዎች ወያኔ ስልጣን ከመያዙ በፊት ወደ ነበሩበት አስተዳደር መመለስ አለባቸው። ስለዚህ ወልቃይትም ወደ ነበረበት ወደ ጎንደር አስተዳደር ይመለሳል። አስተውሉ – ወልቃይት ለሱዳን ወይም ለኤርትራ ይሰጥ እያልኩኝ አይደለም ያለሁት። እሱ የባንዳ ሥራ ነው።
ራያስ ቢሆን?
ሰፊና ለም መሬት ላይ የኖረው የራያ ህዝብ የራሱ የሆነ ታሪክ፣ ወግና ማዕረግ ያለው ህዝብ ነው። ራያ ኢትዮጵያዊነቱን ለድርድር የማያቀርብ፣ አገራችን ከጠላት ለመታደግ በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ አኩሪ የተጋድሎ ታሪክ ያስመዘገበ ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ ችግር ላይ የወደቀው ወንበዴው ስልጣን ከያዘ በኋላ ነው።
አይበገሬ የራያ ህዝብን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ስልጣን ላይ የኖረው የጠላት ቡዳን መጠነ-ሰፊ የሆነ ወንጀል በህዝቡ ላይ ፈጽሟል። አንቱታን ያተረፉ የአገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በተራ የወንበዴ ዞምቢዎች በጠራራ ጸሃይ እየተገመገሙ ( እየተዋረዱ) የአ እምሮ በሽተኞች ሁነው ቀርተዋል።
የራያ ህዝብ የማያውቀውን ቋንቋ ጭኖበታል። በብሄራዊ ቋንቋችን በአማርኛ ሲማር የነበረውን ወጣት ትውልድ በአንድ ጀምበር በአካባቢው በማይነገር ትግርኛ እንዲማር አስገድዶታል። 27 አመት ቢያልፍም፣ ወጣቱ ግን ጊዜ እየጠበቀ ነው፣ የራሱን ቋንቋ ለማስመለስ።
ራያ እንደ ወልቃይት ህዝብ ብዙ ብዙ ስቃይ የተሸከመ ህዝብ ነው። ለም መሬቱን ካድሬዎቹ ስለሚፈልጉት፣ ቤት መስራት አቅሙ ከሌሎችሁ ልቀቁ እያሉ በከተማ ልማት ስም የራያን ህዝብ ለስደት እና ለድህነት ዳርገውት ይኖራሉ። እንደኔ አመለካከት፣ የራያ ህዝብ የራሱ የሆነ ልዩ መስተዳደር ተፈጥሮለት፣ ህዝቡ በመረጠው ቋንቋ እየተዳደረ ቢኖር እመርጣለሁ። ወጣቱ ወንድሜ ዶ/ር ተበጀ እንዳለው፣ “የራያ ህዝብ ዝቅ ቢል ራያ፣ ከፍ ቢል ኢትዮጵያዊነትን” እንጂ በሌላ ልትፈርጀው የማይገባ ፍቅር የሆነ ህዝብ ነው።
ወደ አሜሪካ ከመምጣቴ በፊት፣ ቤተሰቦቼን ራያ ውስጥ ተሰናብቼ ስሄድ፣ መኾኒ እና ኮረም ላይ የራያ ልጅ ጋዜጠኛ መሆኔን አውቀው፣ በሰልፍ ሚስጥራቸውን አካፍለውኛል። ራያዎች እንዲህ ብለው ነበር ያጠቃለሉት፤
“እድሜ ልካችን ደርግን ስንዋጋ አሳለፍነው፣ በስተእርጅናችን ግን ወያኔ የሚሉት ክፉ ጠላት ደረሰብን!”
ልብ የሚነካ አባባል።
ለራሴም ቃል-ኪዳን ገባሁኝ። እስከመጨረሻው ድረስ በመለስ ዜናዊ የሚመራውን የጠላት ቡድን አቅሜ እስከፈቀደልኝ ድረስ ተዋግቶ ለመጣል።
መጨረሻው ደግሞ እግዚአብሄር ያሳየን!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
ሞት ለባንዳዎች!
[ከሙሉነህ /አስናቀው አበበ/ ገጽ የተወሰደ]