አብይ ወደ ግብጽ እየሄዱ ነው- ሲመለሱ ሰልፍ አለ?! /በደረጀ ደስታ/

አብይ ወደ ግብጽ እየሄዱ ነው- ሲመለሱ ሰልፍ አለ?! /በደረጀ ደስታ/

በሱዳን እሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ ትልቁን የአባይ ግድብ በጋራ ይመርቃሉ ሲሉ ተናግረዋል። ምን ማለት ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሳዑዲ አረብያን ጎብኝተዋል። የሳዑዲ ልዑኮችም ኢትዮጵያ ወርደዋል። ሳዑዲም አል አሙዲን ለመፍታት ቃል ከመግባት ጋር፣ ሞቅ ያለ ገንዘብ ለኢትዮጵያ መስጠቷ ተሰምቷል። የሳዑዲ ፍላጎት ደግሞ እርሻና የኤሌክትሪክ ኃይል መሆኑ ተነግሯል። ኢትዮጵያም የኢሌክትሪክ ኃይሉን ወደ ሳዑዲ ልታሰተላልፍ ከስምምነት ተደርሷል። እድገቷን አንሰራርታ ማስወንጨፍ ያቀደችው ሳዑዲም የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ ፈላጊ ናት።

ዶ/ር አብይ ወደ ግብጽ እየሄዱ ነው። አብይና የአባይ ጉዳይ በግብጽ ይወራሉ። የአደፈጠችው ኤርትራም መነሳቷ አይቀርም። ከግብጹ መሪ ሲሲ ጋር ለመነጋገር ካይሮ እየገቡ ያሉት ጠ/ሚ ወይ ሰላም አወርደው ወይ ጠብ ጭረው መመለሳቸው እሚገመት ነው። ነገሮች ባሉበት መቀጠል አለመቻላቸው ግን እየታየ ይመስላል። የኤርትራ ሁኔታ መልክ መያዝ አለበት። የአባይ ግድብ ወይ መቆም ወይ መቀጠል ይኖርበታል። ግድቡ ያለገንዘብ አይሆንም። ገንዘብ ደግሞ የለም። ሳዑዲ የሰጠችው፣ እንግሊዝ የለቀቀችው፣ አሜሪካ ቃል የገባችው ተደማምሮ ለምኑም አይበቃም። እንኳን ለግድቡ ለስንዴም ገና ነው። በዚያ ላይ ቻይናም አንዳንድ ብድሮችን ቀጥ እያደረገች መሆኑ እየተሰማ ነው። ያለ አቅሟ የተንጠራራቸው ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶቿ ማለቂያ የላቸውም። በዚያ ላይ ብድር በወንፊት እምትቀበል መስላለች። ወንፊቱን የያዙት ባለሥልጣኖቿ ገና እየተደረጃጁ ነው ። የገንዘብ እጥረቱ ግን ጊዜ አልሰጥ ብሏል። ለነገሩ የኢኮኖሚው ድቀት ገብቶ ኢትዮጵያን ጠብሽ ከመታት ዓመታት አልፈዋል።

በተለይ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ጀምሮ የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር ኃ/ማር ያም ደሳለኝና አማካሪያቸው አቶ አርከበ ዕቁባይ ኢትዮጵያ ዛሬ ለሙሉና ከፊል ሽያጭ ያቀረበቻቸውን ተቋማት እንድትሽጥ ሀሳብ ማቅረባቸው ይታወቃል። በወቅቱ ኃይለማርያም ከፓርቲው ባለሥልጣናት ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸው ሀሳቡ ውድቅ ተደርጓል። ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ያ ሀሳብ ዛሬ እንደገና ተነስቷል። እነዚያው የተቃወሙት ሰዎች መልሰው አጽድቀውታል። ባዶ ካዝና የተረከቡት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም መሳቢያውንም ቢከፍቱት ቤሳ ቢስቲን የለችም። ሌላ አማራጭ ያላቸው አልመሰሉም።

የሆነ ሆኖ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷን ሊበላ የደረሰውን የፖለቲካ ቀውስ ማብረድ ቢችሉም ለኢኮኖሚው ቀውስ ግን ገና ናቸው። ኢትዮጵያ እሚላስ እሚቀመስ ሲጠፋ የጣት ቀለበቷን አውጥታ እንደምሸጥ እናት ሆናለች። ቢሆንም ቢሆንም ከዚህ ሁሉ ሊያወጣን ተነስቷል ካለችው አዲሱ መሪዋ ደግሞ ፍቅር የወደቀች መስላለች። እሳቸውና ድርጅታቸው ግን አሁንም ኩሩ ለማኝ ይመስል እሚሰጡት መግለጫ ችግሩን አፍርጦ ያብራራ አይመስልም። ይሄ ፎቅ ስለሚያስጠላ ይህን አፍርሼ ከዚህ ያማረ ቆንጆ ፎቅ መስራት እፈልጋለሁ ዓይነት መዘባነን አስመስሎብቸዋል።

ኢኮኖሚው ስላሽቆለቆለ ሳይሆን እድገቱን የበለጠ “ለማስቀጠል” እሚለው መግለጫቸው እንዲህ ይላል
“እነዚህ ተቋማት በዚህ መልኩ ወደ ግል ይዞታነት እንዲተላለፉ የተወሰነው ለመንግስት ከፍተኛ የፋይናስ አቅም ለመፍጠር፣የኢኮኖሚውን እድገት ለማስቀጠል፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ በማሰብ ነው። …እንዲሁም ሀገሪቱ ካጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመውጣት እሚል ነው።”
እድገትን ቁልቁል በምታሰላ አገር ክርክሩ ብዙ ፋይዳ ባይኖረውም ፖለቲካውን አፍረጥረጠው መናገር የሞከሩት ጠቅላይ ምኒስትር ያለንበትንም ችግር ሳይቀባቡ አፍረጥርጠውና ዘርዝረው ቢነገሩን “አገር መሸጥ መለወጥ” እሚለው ክስ ይቀራል። በተለይ አገር ሸጠዋል የተባሉ ሰዎች ራሳቸው መልሰው ደግሞ ሌላውን በአገር ሻጭነት ሲከሱ እሚሰማው ንትርክ ይደብራል። ለነገሩ የባድመን እንኳ ነገሩን ለኔ ተውት ብሎ ህወሓት በመግለጫ ኃላፊነቱን ወስዷል።

እንደሚሰማው ይህም ሆኖ ጠቅላይ ምኒስትሩን በቀውስ ጠልፎ ለመጣል እሚደረገው ሤራ ደርቷል። አሁን ግብጽ ደርሰው ፣ በሊብያ በአይሲስ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን አስክሬን ይዘው ለመመለስ ያቀዱት ጠቅላይ ምኒስትር፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ አቀባበል እንዲጠብቃቸው ውስጥ ውስጡን ዝግጅት መኖሩ እየተሰማ ነው። እንደሚባለው ክውስጥ ተቃሚዎቻቸው ያለውን ሤራ ለማክሸፍ እንዲረዳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ህዝባዊ ድጋፍ ለማሳየት የታቀደ “ቅዱስ” ሤራ መሆኑ ይገመታል። “ህዝበኝነት!” ይሉታል “ድርጅተኝነቶቹ!”

እውር ምን ይሻላል ቢሉት – ማየት- አለ አሉ ማየት ነው።

LEAVE A REPLY