የባድሜ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ

የባድሜ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል ያሳለፈው ውሳኔ “የሀገር ክህደት ነው” በሚል መሪ ቃል በባድሜ ከተማ ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ ከ18 ዓመታት በፊት በአልጀርስ የተፈረመው የሁለቱ ሀገራት ውል ባድሜን ጨምሮ 17 የድንበር ወረዳዎችን ለኤርትራ አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

በተቃውሞ ሰልፉ ላይም ጎላ ብለው ከተሰሙት መፈክሮች መካከል፤ “የእራሳችን ኣንሰጥም የሌላ ኣንፈልግም፣ የኢህኣዴግ ውሳኔ የሀገር ክህደት ነው፣ ህይወት የተከፈለበትን መሬት አሳልፈን አንሰጥም” የሚሉና ሌሎች ድምፆችም መፀባረቃቸውን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ባለፈው አርብም ኢሮብ ወረዳ ነዋሪዎች ውሳኔውን በመቃወም ሰልፍ ሰልፍ አካሂደዋል። የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ለኢቲቪ በሰጡት አስተያየትም  ስምምነቱ የኢሮብን ሕዝብ ለሁለት የሚከፍል በመሆኑ እንደሚቃወሙት ተናግረዋል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ መቀበሉን ተከትሎ፤ ህወሓት ባወጣው መግለጫ “በኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ ኢህአዴግ ያስተላለፈው ውሳኔ የሀገሪቱን ሠላም በተለይም የትግራይ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት ሲያነሳው የነበረውን ጥያቄ በመመለስ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ወደነበረበት ወንድማማችነት ለመመለስ ያለመ ነው። ”በማለት የደገፈ ቢሆንም በክልሉ የህዝብ ተቃውሞ ሲበረታበት “የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴን አስቸኳይ ስብሰባ” በመጥራት ከትናንት ጀምሮ በጉዳዩ ላይ እየመከረ መሆኑን ገልፀጿል።

አረና ትግራይ (ፓርቲ) የኢህአዴግን ውሳኔ በመቃወም መግለጫ ያወጣ ሲሆን በሚቀጥለው ቅዳሜም በመቀሌ ከተማ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል።

ኢትዮጵያ በጦር አውድ አሸናፊ የነበረችበትንና በጠላት የጣሊያን ጊዜ ተፈርሞ በራሱ በጣሊያን የተሻረውን ውል በመቀበል የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የሰጡት አቶ መለስ ዜናዊ እና ስዩም መስፍን በአልጀርሱ ስምምነት ላይ የፈጸሙት ክህደት ለዚህ ውዝግብ ዋነኛ ተጠያቂዎች መሆናቸው ይታወቃል።

LEAVE A REPLY