በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ አሁንም በየ እስር ቤቱ የሚማቅቁ ወገኖች እንዲፈቱ ጠየቁ
_____
ዶከተር ፍቅሩ ማሩ
ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓም
ለሚመለከተው ሁሉ!
በፖለቲካና በ”ሽብርተኝነት” ተከሰው ጉዳያቸው በሂደት ላይ ያሉትም ሆነ፣ ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙትን እስረኞች መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እፈታለሁ ካለ 2 ወራት አልፈወል። እስካሁን በ እስረኞች ተፈትተዋል። ነገር ግን ጉዳያቸው ከተፈቱት ጋር በአንድ ፈርጅ የሚጠቃለሉ አሁንም በእየስር ቤቱ ይማቅቃሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት፣ በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እየወሰዱ ያሉት ሰብአዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች የሚመሰገኑ ብቻ ሳይሆኑ እንከን የማይወጣላቸውም አሉ ማለት ይቻላል።
በጎረቤት ሀገሮች የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን ማስፈታት፣ የሚፈልጉትን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ በእጅጉ የሚደገፍ እርምጃ ነው! ሆኖም በፈጠራ ክስ፣ በሀሰት ምስክርና በተበላሸ የፍትሕ ስርዓት እየተሰቃዩ ያሉ ውድ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ሰቆቃ እንዲወጡ ማድረግ ምንም ጊዜና ምክንያት የሚሰጠው አይደለም።
እኔ ለአምስት አመት የግፍ እስረኛ ሆኜ ከወጣሁ በኋላ አሁን የነፃነት አየር እየተነፈስኩ ብገኝ፣ ቆሜ ብሄድም የዛ የሰቆቃ ጊዜ ገና ከአእምሮዬ አልወጣም። በእኔም ላይ የደረሰው በደል የደረሰባቸው፣ ከእኔም በላይ በደል የደረሰባቸው ሁኔታቸው ባልተቀየረ አሰቃቂ ሁኔታ ላይ የሚገኙ እንደ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ያሉት በእስር ቤት እየኖሩ፣ ለአንድም ደቂቃ ቢሆን የተሟላ ነፃነት ከተውንም ሊሰማኝ አልቻለም።
በእርግጥ የኢትዮጵያ ፍትሕ ስርዓት ስርነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው ሁሉም የሚያምነው ነው። ነገር ግን በግፍና በሀሰት የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን መፍታት ህግን የመቀየርና የማሻሻል ቅድመ ሁኔተ ሊሆን አይገባውም።
ይህንን ሕዝብና ሀገር የሚጠቅም፣ በበለጠ ደግሞ የተጎጅዎችን ሰብአዊ መብት የሚያከብር፣ ሁሉንም የግፍ እስረኞች የመፍታት እርምጃ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ሰብአዊና ኢትዮጵያዊ ስሜቴ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!
ኢትዮጵያዊ ኩራታችን የተግባራችን መገለጫ እናድርገው!